ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፤ ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፤  

ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፤ "የአንድ እናትና የአንድ አባት ፍቅር"

ልጆች አንዴ ከተወለዱ ከምግብና ከእንክብካቤ በተጨማሪ፣ መወደዳቸውን በእርግጠኝነት የማወቅ መንፈሳዊ ስጦታንም መቀበል ይጀምራሉ። ይህንንም ፍቅር ለእነርሱ ማሳየት የሚቻለው የግል ስም በማውጣት፣ በመጋራት፣ በፍቅር ዐይን በመተያየትና ብሩህ ፈገግታ በማሳየት ነው። በዚህ ዐይነት፣ የሰብአዊ ግንኙነቶች ውበት ነፍሳችንን እንደሚማርክ፣ ነጻነታችንን እንደሚሻ፣ የሌሎችን ልዩነት እንደሚቀበል፣ በውይይትም ላይ እነርሱን እንደሚያውቅና እንደ አጋር እንደሚቀበል ሕጻናት ይማራሉ… ፍቅር ማለት እንዲህ ነው፣ የእግዚአብሔርን የፍቅር ፍንጣቂ የያዘ ነው። እያንዳንዱ ሕጻን ከእናቱና ከአባቱ ፍቅርን የማግኘት መብት አለው፤ ሁለቱም ለሕጻኑ የተቀናጀና ኅብር ላለው እድገት አስፈላጊ ናቸው።

የአውስትራሊያ ጳጳሳት እንዳመለከቱት፣ እያንዳንዱ ወላጅ “ለልጁ ዕድገት ልዩ አስተዋጽኦ ያበረክታል። የልጅን ክብር መጠበቅ ማለት የእርሱን ወይም የእርስዋን እናትና አባት የማግኘት ፍላጎትና የተፈጥሮ መብት ማረጋገጥ ነው። የምንናገረው በተናጠል ስለ አባትና ስለ እናት ፍቅር ሳይሆን፣ የሰው ሕይወት ምንጭና የቤተሰብ ጠንካራ መሠረት ተደርጎ ስለሚታሰበው ስለ ጋራ ፍቅራቸው ጭምር ነው። ይህ የጋራ ፍቅር ከሌለ፣ አንድ ሕጻን ተራ መጫወቻ ይሆናል። ባልና ሚስት፣ አባትና እናት፣ ሁለቱም ‹‹ከፈጣሪ እግዚአብሔር ፍቅር ጋር ይተባበራሉ፣ በልዩ መንገድ የእርሱ አስተርጓሚዎችም ናቸው። ለልጆቻቸው የጌታን እናታዊና አባታዊ ፊት ያሳያሉ። በጋራ ሆነው አጸፋ የመመለስን፣ ልዩነቶችን የማክበርን እንዲሁም የመስጠትና የመቀበል ችሎታ የማዳበርን ጥቅም ያስተምሩአቸዋል። በአይቀሬ ምክንያት አንድ ወላጅ ባይኖር፣ ስለ ሕጻኑ ጤናማ የወደፊት እድገት ሲባል ለዚህ ጉድለት የሚሆን ማካካሻ መፈለግ ያስፈልጋል።

ብዙ ልጆችንና ወጣቶችን የሚጎዳው የወላጅ አልባነት ስሜት ዛሬ ከምናስበው በላይ ሥር የሰደደ ሆኖአል። ዛሬ ሴቶች ያላቸው የመማር፣ የመሥራት፣ ክህሎታቸውን የማዳበርና የግል ግብ የማስቀመጥ ፍላጎት ተገቢና በእርግጥም አስፈላጊ እንደ ሆነ እናውቃለን። በተመሳሳይ፣ በተለይ በመጀመሪያዎቹ የሕይወት ወራት የእናትን መኖር የሚሹ ሕጻናትን ፍላጎት ችላ ማለት አንችልም። በእርግጥ፣ ‹‹በውስጥዋ የተፀነሰውና እያደገ ያለው የአዲስ ሰብአዊ ሕይወት ባለቤት የሆነችው ሴት፣ እንደ እናትነትዋ ከወንድ ትቀድማለች። የዚህ እናታዊ መገኘት ከሴትነት ባሕርዩ ጭምር መዳከም ለዓለማችን ከባድ ሥጋት ፈጥሮአል። ተመሳሳይነትን ለማይጠይቅ ወይም እናትነትን ለማያቃልል ለሴቶች የጾታ እኩልነት አስተሳሰብ በእርግጥ ዋጋ እሰጣለሁ። ምክንያቱም የሴቶች ታላቅነት ከማይገሰስ ሰብአዊ ክብራቸው ብቻ ሳይሆን፣ ለኅብረተሰብ አስፈላጊ ከሆነው የሴትነት ተሰጧአቸው የመነጩ መብቶችን ሁሉ የያዘ ነው። በተለይ የእነርሱ እንስታዊ ችሎታዎች፣ በተለይ እናትነት፣ ኃላፊነትንም ያዘለ ነው፤ ምክንያቱም ሴትነት በዚህ ዓለም ላይ ልዩ ተልእኮ ያለው ሲሆን፣ ይህንንም ተልእኮ ኅብረተሰቡ ለሁሉም የጋራ ጥቅም ሲል ሊጠብቀውና ሊንከባከበው ይገባል።

እናቶች ራስን ማእከል ላደረገ ግለሰባዊነት መስፋፋት ብርቱ ማርከሻ ናቸው።… የሕይወትን ውበት የሚመሰክሩት እነርሱ ናቸው። በእርግጥ ‹‹አንድ ኅብረተሰብ ያለ እናቶች ሰብአዊ ክብር አይኖረውም፣ ምክንያቱም እናቶች ሁልጊዜ፣ በክፉ ጊዜያት ጭምር፣ የርህኅራኄ፣ የቁርጠኝነትና የግብረ ገብ ጥንካሬ ምሥክሮች ናቸው። እናቶች ብዙውን ጊዜ ልጆቻቸው በሚማሩአቸው የመጀመሪያ ጸሎቶችና ሥራዎች አማካይነት የመንፈሳዊ ተሞክሮን ጥልቅ ትርጉም ያስተላልፋሉ።… ያለ እናቶች፣ አዲስ ምእመን አለመኖር ብቻ ሳይሆን እምነት ራሱ ቀላሉንና የመሠረታዊ ግለቱን ዋና ክፍል ያጣል። … ውድ እናቶች ሆይ፣ አመሰግናችኋለሁ። በቤተሰባችሁ ውስጥ ስለ ሆናችሁት ነገር፣ ለቤተክርስቲያንና ለዓለም ስለምትሰጡት ነገር አመሰግናችኋለሁ።

ልጅዋን በርኅራኄና በደግነት የምትንከባከብ እናት በራስ መተማመንን እንዲዳብርና ዓለም ጥሩና ማራኪ ቦታ መሆኑን እንዲያውቅ ትረዳለች። ይህም ልጁ በራስ በመተማመን እንዲያድግና በአንጻሩም ከሰው ጋር የመቀራረብና ለሰው የማዘን ችሎታውን እንዲያዳብር ይረዳዋል። አባት በበኩሉ፣ የሕይወትን ገደቦች እንዲመለከት፣ ለሰፊው ዓለም ተግዳሮቶች ዝግጁ እንዲሆንና የከባድ ሥራንና የብርቱ ልፋትን አስፈላጊነት እንዲያውቅ ልጁን ይረዳዋል። ግልጽና ሰላማዊ የወንድነት ባህርይ ያለው እንዲሁም ለሚስቱ ፍቅሩንና ክብካቤውን የሚያሳይ አባት የተንከባካቢ እናትን ያህል አስፈላጊ ነው። ከእያንዳንዱ ቤተሰብ ተጨባጭ ሁኔታዎች በመነሣት፣ በሥራ ድርሻዎችና ኃላፊነቶች ረገድ አንዳንድ ለውጦች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን፣ የሁለቱም የወንድና የሴት በግልጽና በታወቀ መንገድ መኖር ለልጁ የተሻለ ዕድገት አመቺ የሆነ ከባቢን ይፈጥራል።

ብዙውን ጊዜ የእኛ “ኅብረተሰብ አባት አልባ›› ነው ሲበል እንሰማለን። በምዕራባውያን ባህል፣ የአባት ተምሳሌትነት የለም፣ ጎድሎአል ወይም ጠፍቶአል። እናትነት ራሱ ጥያቄ ውስጥ የገባ ይመስላል። ውጤቱም ያለ ጥርጥር አደናጋሪ ሆኖአል። በመጀመሪያ፣ ይህ እንደ ነጻነት ይቆጠር ነበር፤ እንደ ጌታ ከሚታየው አባት፣ ከውጭ የመጣ ሕግ አስከባሪ ተደርጎ ከሚታሰበው አባት፣ የልጆቹን ደስታ የመወሰን ሥልጣን ካለውና ለወጣቶች ነጻነትና ራስን መቻል እንቅፋት ከሆነ አባት እጅ አርነት እንደ መውጣት ይቆጠር ነበር። በመሆኑም፣ በአንዳንድ ቤቶች ውስጥ ፈላጭ ቆራጭነት ፣ አልፎ አልፎም ጭቆና ነግሦ ነበር። ሆኖም ብዙ ጊዜ እንደሚሆነው፣ ሰው ከአንዱ አጥናፍ ወደ ሌላው አጥናፍ ሊሄድ ይችላል። በዘመናችን፣ ችግሩ የአባት አለቅነት መሆኑ ቀርቶ የአባት በዚያ አለመገኘት፣ አለመኖር ይመስላል። አባቶች ብዙውን ጊዜ በራሳቸውና በሥራቸው እጅግ ስለሚጠመዱ፣ ቤተሰቦቻቸውን ችላ ይላሉ። ጨቅላዎችንና ለጋ ወጣቶችን ለብቻቸው ይተውአቸዋል። ለመገናኛና ለመዝናኛ የሚሰጠው ጊዜም በአባት መኖርና በአባት ሥልጣን ላይ ጫና አሳድሮአል። ዛሬ ሥልጣን አብዛኛውን ጊዜ እንደ ጥርጣሬ፣ የዐዋቂዎች አያያዝም እንደ ብልግና መታየት ጀምሮአል። እነርሱ ራሳቸው እርግጠኞች ስላልሆኑ፣ ለልጆቻቸው እርግጠኛና ጠንካራ አመራር መስጠት አይችሉም። የወላጆችና የልጆች ሚና መቀያየር ጤናማ አካሄድ አይደለም፤ ምክንያቱም ልጆች ሊለማመዱት የሚገባውን ትክክለኛ የዕድገት ሂደት ያደናቅፋል፣ ለመጎልመስ የሚያስፈልጋቸውን ፍቅርና አመራር ይነፍጋቸዋል።

እግዚአብሔር አባትን በቤተሰብ ውስጥ ያስቀመጠው በወንድነቱ “ለሚስቱ ቅርብ እንዲሆንና ሁሉንም ነገር፣ ደስታንና ሐዘንን፣ ተስፋና መከራን ሁሉ እንዲጋራ ነው። እንዲሁም ልጆቹ ሲያድጉ፣ ሲጫወቱና ሲሠሩ፣ ሲዝናኑና ሲደበሩ፣ ሲለፈልፉና ጸጥ ሲሉ፣ ሲደፍሩና ሲፈሩ፣ ሲቅበዘበዙና ወደ ትክክለኛው መንገድ ሲመለሱ ለእነርሱ ቅርብ እንዲሆን ነው። ሁልጊዜ የሚገኝ አባት እንዲሆን ነው። ‹መገኘት› ስል ‹መቆጣጠር› ማለቴ አይደለም። ቁጥጥር የሚያበዙ አባቶች ልጆቻቸውን ይጋርዳሉ፣ እንዲያድጉ አይፈቅዱላቸውም። አንዳንድ አባቶች ዋጋ ቢስ ነን ወይም አላስፈላጊ ነን ብለው ያስባሉ። እውነታው ግን ‹‹ልጆች ችግር ገጥሞአቸው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ የሚጠብቃቸው አባት የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ነው። ልጆች ችግሩን ላለመቀበልና ላለማሳየት ይጥራሉ፣ ነገር ግን አባት ያስፈልጋቸዋል። አባት ማጣትና ያለ ዕድሜአቸው ቀድሞ ማደግ ለልጆች ጥሩ አይደለም።

ምንጭ፡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርዕሥ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 172-178 ላይ የተወሰደ።

አዘጋጅ አባ ዳንኤል ኃይለ

24 August 2024, 13:53