ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፥ "ፍሬያማ የሆነ ፍቅር"
ፍቅር ምንጊዜም ሕይወትን ይሰጣል። የጋብቻ ፍቅር “በባልና ሚስት አያበቃም… ባልና ሚስት፣ ራሳቸውን ለእርስ በርሳቸው ሲሰጣጡ የሚሰጣጡት ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን፣ የእነርሱ የፍቅር ሕያው መገለጫዎች፣ የጋብቻ አንድነታቸው ቋሚ ምልክትና አባትና እናት ለሚያደርጋቸው ሕያውና የማይነጣጠል ውህደት ምሳሌ የሚሆኑ ልጆች የማፍራት እውነታን ጭምር ነው”።
አዲስ ሕይወትን በደስታ መቀበል
ቤተሰብ አዲስ ሕይወት የሚወለድበት ብቻ ሳይሆን፣ ያንን አዲስ ሕይወት እንደ እግዚአብሔር ስጦታ የሚቀበሉበት ዐውድ ነው። እያንዳንዱ አዲስ ሕይወት “ሁሌም ያስገርመናል፤ ነጻ የሆነውን የፍቅር ገጽታንም እንድናደንቅ ያደርገናል። አስቀድሞ የመወደድ ድንቅ ውበት ነው፤ አዎን ሕጻናት ገና ከመወለዳቸው በፊት ይወደዳሉ። ስለሆነም እዚህ ላይ ምንጊዜም ቅድሚያ የሚሰጠውን የእግዚአብሔርን ቀዳሚ የፍቅር ነጸብራቅ እናያለን፤ ምክንያቱም ሕጻናት ‹‹ገና የሚወደዱበትን አንዳች ነገር ሳያደርጉ እንዲሁ ይወደዳሉና። ሆኖም፣ ‹‹ከሕይወታቸው የመጀመሪያ ሰዓታት አንሥቶ፣ ብዙ ልጆች ተቀባይነትን አያገኙም፣ ይጣላሉ፣ የልጅነትና የወደ ፊት ተስፋቸውን ይሰረቃሉ። አንዳንዶች የራሳቸውን ትክክለኛነት ለማሳየት ሲሉ፣ እነዚህን የመሰሉ ሕጻናት ወደዚህች ዓለም ማምጣት ስሕተት ነው በማለት በድፍረት የሚናገሩ ሰዎች አሉ። ይህ አሳፋሪ ነው! …በጎልማሶች ስሕተት ሕጻናትን እንዲህ የምንቀጣ ከሆነ፣ ሰብአዊ መብቶችንና የሕጻናትን መብቶች ስለማክበር እንዴት መለፈፍ እንችላለን” (179)።
አንድ ሕጻን በማይፈለጉ ሁኔታዎች ወደዚህች ዓለም ሲመጣ ወላጆችና ሌሎች የቤተሰብ አባላት ያንን ሕጻን እንደ እግዚአብሔር ስጦታ አድርገው ለመቀበል የሚቻለውን ሁሉ ማድረግና እርሱንም/እርስዋንም በሙሉ ልብና በፍቅር የመቀበል ኃላፊነት መውሰድ ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም “ወደዚህች ዓለም ስለሚመጡ ሕጻናት ሲነገር፣ ሕጻኑ በስሕተት የተወለደ፣ ወይም ዋጋ ቢስ እንደ ሆነ ወይም ለአራቱም ነፋሳትና ለሰው ልጅ እብሪት የተተወ መስሎ እንዳይሰማው ከተፈለገ፣ የጎልማሶች መሥዋዕትነት በወጪም በመጠንን እጅግ የበዛ ነው ተብሎ ሊታሰብ አይገባም። ጌታ ለአባትና ለእናት የሚሰጠው የአዲስ ልጅ ስጦታ የሚጀምረው በመቀበል ሲሆን፣ የዕድሜ ልክ ጥበቃ በማድረግ ይቀጥላል፣ የመጨረሻ ግቡም የዘላለማዊ ሕይወት ደስታ ነው። የእያንዳንዱን ሰው የመጨረሻ ስኬት በጽናት በማሰላሰል፣ ወላጆች ስለ ተሰጣቸው ክቡር ስጦታ ይበልጥ ግንዛቤ ይኖራቸዋል። ምክንያቱም እግዚአብሔር ራሱ ልጃቸው ለዘላለም የሚጠራበትን ስም እንዲመርጡለት ለወላጆች ዕድሉን ይሰጣቸዋል። “የሰው ሕይወትና እርሱንም የማስተላለፍ ትርጉሙ በዚህ የሕይወት አድማስ ብቻ የተገደቡ እውነታዎች አይደለም፤ የዚህንም እውነተኛ ግምገማና ሙሉ ትርጉም መረዳት የሚቻለው ከዘላለማዊ ዕጣ ፈንታችን አንጻር ብቻ ነው።” ብዙ አባላት ያሏቸው ቤተሰቦች ለቤተክርስቲያን ደስታና የፍቅር ፍሬያማነት መገለጫ ናቸው። ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በትክክል እንዳብራሩት፥ “ኃላፊነት የሚሰማው ወላጅነት ማለት ያልተገደበ ተዋልዶ ወይም ልጆችን በማሳደግ ረገድ ያለውን እውነታ አለመረዳት ሳይሆን፣ ባልና ሚስት የማይጣስ ነጻነታቸውን በማስተዋልና ኃላፊነት በሚሰማው መንገድ እንዲጠቀሙ፣ ማኅበራዊና የሕዝብ ብዛት እውነታዎችን እንዲሁም የራሳቸውን ሁኔታና ተገቢ ምኞቶች ግምት ውስጥ እንዲያስገቡ ማብቃት ነው።”
ፍቅር እና እርግዝና
እርግዝና አስቸጋሪ፣ ነገር ግን፣ ድንቅ ጊዜ ነው። አንዲት እናት የአዲስ ሕጻን ተአምር ለማሳየት ከእግዚአብሔር ጋር ትተባበራለች። እናትነት ‹‹የሴት አካል ለአዲስ ሰው ጽንሰትና ልደት የታለመ ልዩ የፈጠራ እምቅ ኃይል›› ውጤት ነው። እያንዳንድዋ ሴት ‹‹በእያንዳንዱ ልደት በሚታደስ የፍጥረት ምሥጢር›› ትሳተፋለች። መዝሙረኛው “በእናቴ ማሕፀን ውስጥ አበጃጅተህ ሠራኸኝ›› (መዝ. 139፡13) ይላል። በእናቱ ማሕፀን ውስጥ የሚያድግ እያንዳንዱ ሕጻን፥ “በማሕፀን ሳልሠራህ አወቅሁህ፤ ከመወለድህ በፊት ለየሁህ›› (ኤር. 1፡5) የሚለው የእግዚአብሔር አብ የዘላለማዊ ዕቅድ አካል ነው። እያንዳንዱ ሕጻን ከጥንት ጀምሮ በእግዚአብሔር ልብ ውስጥ ቦታ አለው፤ እርሱ ወይም እርስዋ አንዴ ከተፀነሱ፣ የፈጣሪ ዘላለማዊ ሕልም እውን ይሆናል። ስለዚህ ከጽንሰት ጀምሮ ያለውን የዚያን ፅንስ ታላቅ ዋጋ እናስብ። እርሱንም ምንጊዜም ከመልክ ባሻገር በሚመለከተው በእግዚአብሔር ዐይን እንመልከተው። እርጉዝ ሴት ስለ ልጅዋ እያለመች በእግዚአብሔር ዕቅድ ትሳተፋለች። “ለዘጠኝ ወራት እያንዳንድዋ እናትና እያንዳንዱ አባት ስለ ልጃቸው ያልማሉ… ያለ ሕልም ቤተሰብ ሊኖራችሁ አይችልም። አንድ ቤተሰብ ማለም ካልቻለ፣ ሕጻናት አያድጉም፣ ፍቅር አያድግም፣ ሕይወትም ይደርቅና ይሞታል።” ለክርስቲያን ባለትዳሮች፣ ጥምቀት የዚያ ሕልም አካል መስሎ መታየቱ ተገቢ ነው። ምክንያቱም ወላጆች በጸሎት ለጥምቀት ይዘጋጃሉ፣ ገና ከመወለዱ በፊት ሕጻን ልጃቸውን ለኢየሱስ አደራ ይሰጣሉ።
ዛሬ ያለው የሳይንስ ዕድገት የልጅን የጸጉር ቀለም ለመምረጥ ወይም ሊያጋጥሙት የሚችሉ የበሽታ ዐይነቶች ምን እንደ ሆኑ አስቀድመን እንድናውቅ ያስችለናል። ምክንያቱም ሥጋዊ ባህርያት ሁሉ ገና በጽንስ ደረጃ በሰው ዘረ - መል ቀመር ውስጥ ተጽፈው ይገኛሉና። ሆኖም ስለ ሕጻኑ ሙሉ በሙሉ የሚያውቀው ፈጣሪው እግዚአብሔር አብ ብቻ ነው። የሕጻኑን ውስጣዊ ማንነትና ዋጋ የሚያውቀው እርሱ ብቻ ነው። ነፍሰ ጡር እናቶች ልጆቻቸውን በጥልቀት ለማወቅና በማንነታቸው ለመቀበል የሚያስችላቸውን ጥበብ እንዲሰጣቸው እግዚአብሔርን መለመን ያስፈልጋቸዋል። አንዳንድ ወላጆች ልጃቸው በጥሩ ጊዜ እንዳልመጣ ይሰማቸዋል። እንዲፈውሳቸውና እንዲያበረታቸው እንዲሁም ልጃቸውን በሙሉ ልብ ለመቀበል እንዲረዳቸው እግዚአብሔርን መለመን ይኖርባቸዋል። ያም ሕጻን ተፈላጊ መሆኑ እንዲሰማው ማድረግ ጠቃሚ ነው። ሕጻኑ ተጨማሪ ዕቃ ወይም የሆነ የግል ፍላጎት ማርኪያ አይደለም። ሕጻን ልጅ ትልቅ ዋጋ ያለውና ለግል ጥቅም ሲባል ከቶ ሊገለገሉበት የማይገባ ሰብአዊ ፍጡር ነው። ስለዚህ፣ ይህ አዲስ ሕይወት ለእናንተ ምቹ ይሁን አይሁን፣ ወይም እናንተን የሚያስደስቱ ባሕርያት ይኑሩት አይኑሩት ወይም ከእናንተ ዕቅድና ምኞት ጋር ይስማማ አይስማማ እምብዛም አይገድም። ምክንያቱም “ሕጻናት ስጦታ ናቸው… እያንዳንዱም ልዩና ምትክ የሌለው ነው… ልጆቻችንን የምንወደው ውብ ስለ ሆኑ፣ እኛን ስለሚመስሉ ወይም እንደ እኛ ስለሚያስቡ ወይም የምኞታችን ተምሳሌት ስለ ሆኑ ሳይሆን፣ ልጆች ስለ ሆኑ ነው። የምንወዳቸው ልጆች ስለ ሆኑ ነው። ልጅ ልጅ ነው።” የወላጆች ፍቅር እግዚአብሔር አባታችን የራሱን ፍቅር የሚያሳይበት መንገድ ነው። እርሱ የእያንዳንዱን ሕጻን መወለድ በጉጉት ይጠባበቃል፣ ያንን ሕጻን ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ይቀበለዋል፣ በደስታና በነጻነትም ያስተናግደዋል።
እኔም የወደፊት እናቶችን ሁሉ በታላቅ ፍቅር እንዲህ በማለት አበረታታቸዋለሁ፡- ደስተኞች ሁኑ፣ ውስጣዊ የእናትነት ደስታችሁ እንዲወሰድባችሁ አትፍቀዱ። ልጃችሁ የእናንተ ደስታ ያስፈልገዋል። ፍርሃት፣ ጭንቀት፣ የሌሎች ሰዎች አስተያየት ወይም ማናቸውም ችግር አንድን አዲስ ሕይወት ወደዚህች ዓለም ለማምጣት የእግዚአብሔር መሣሪያ የመሆናችሁን ደስታ አይቀንስባችሁ። ለልጃችሁ ልደት ያለ ፍርሃት ተዘጋጁ፣ ‹‹ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፤ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ትደሰታለች፤ እርሱ የባሪያይቱንውን ውርደት ተመልክቶአልና›› (ሉቃ. 1፡ 46-48) በሚለው በማርያም የውዳሴ መዝሙር ተካፈሉ። ይህን ድንቅ ስሜት በብዙ ጭንቀቶቻችሁ መካከል ለመለማመድ ሞክሩ፣ ወደ ልጃችሁ ታስተላልፉ ዘንድ ጌታ ደስታችሁን እንዲጠብቅላችሁ ለምኑት።
ምንጭ፡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርእስ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 165-171 ላይ የተወሰደመሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።
አዘጋጅ አባ ዳንኤል ኃይለ