ብፁዕ ካርዲናል ዙፒ ይቅርታ እና ፍትህ የሰላም መንገድ ናቸው አሉ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በሰሜናዊ ጣሊያን በምትገኘው ሪሚኒ ከተማ በተካሄደው የህዝቦች የወዳጅነት ስብሰባ ቦታ ላይ የተቋቋመውን ጊዜያዊ የቫቲካን ዜና ስቱዲዮ በመጎብኘት ባደረጉት ቃለ ምልልስ ብጹእ ካርዲናል ማትዮ ዙፒ የይቅርታ እና የፍትህ አስፈላጊነት በማጉላት የሰላም ጎዳና መሆናቸውን አመልክተዋል።
የቦሎኛ ሊቀ ጳጳስ እና የኢጣሊያን ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ዙፒ ጎረቤቶቻችንን መልሶ ለማግኘት እና ወንድማማችነትን ለማጠናከር ብቸኛው መንገድ እርቅ ነው ሲሉ አሳስበዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ዙፒ ሃይማኖቶች ጥላቻን እና ጥቃትን በመዋጋት ረገድ ያላቸውን መሠረታዊ ሚና ጠቁመው፥ በድርድር ላይ የተመሰረተ እውነተኛ ተነሳሽነት እና ሰላምን ለማስፈን መስማማት አስፈላጊ እንደሆነ አስምረውበታል።
ትምህርት መሰረታዊ ነገር ነው
እንደ ብጹእ ካርዲናል ገለጻ ክርስቲያኖች ወደ ጦርነት፣ ግጭት፣ ጭፍን ጥላቻ፣ ቅሬታ እና ቂም በቀል የሚመራውን የተዛባ የፍትህ ስሜትን የሚያዳብረውን ደካማ የትምህርት ሥርዓት ለመቋቋም ብዙ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
በይቅርታ እና በፍትህ በኩል ሌላውን እንደ ወንድም በመገንዘብ ሰላምን ለማስተማር ብቸኛው መንገድ እርቅ ነው፥ ለዚህም ትምህርት በጣም አስፈላጊ ነገር ነው ያሉት ብጹእነታቸው፥ “ትምህርት በደመ ነፍስ እንዳንመራ የእግዚአብሔርን ምክር የምንከተልበት መንገድ ነው” ብለዋል።
ለመደራደር ድፍረቱ ሊኖር ይገባል
በቃለ ምልልሳቸው ወቅት ድርድር ወይም የእርቅ ሃሳብ የድፍረት ፍሬ ነው ያሉት ብጹእ ካርዲናል ማቲዮ ዙፒ፥ ድፍረት በውይይት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸው፥ “ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እውነተኛ ድፍረት እንዴት መደራደር እንዳለብን ማወቅ ነው ሲሉ ፍጹም ትክክል ናቸው” ካሉ በኋላ፥ “እውነተኛ ድፍረት የወደፊቱን ጊዜ የሚመለከት ስምምነትን እንዴት መምረጥ፣ መረዳት እና ማግኘት እንደሚቻል ማወቅ ነው” በማለት አጠቃለዋል።