የካቶሊክ የሰላም ፎረም ከኒውክሌር ጦር መሳሪያ ነፃ የሆነ ዓለም እንዲገነባ በድጋሚ ጥሪውን አቀረበ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ፓክስ ክሪስቲ ኮሪያ ከዓለም አቀፉ ፓክስ ክሪስቲ እና የዩናይትድ ስቴትስ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የካቶሊክ ተማሪዎች ንቅናቄ ጋር በመተባበር ነሃሴ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. በጃፓን ሃገር የመጀመሪያውን የናጋሳኪ ካቶሊካዊ የሰላም ፎረም አስተናግዷል።
ከኮሪያ፣ ከጃፓን እና ከዩናይትድ ስቴትስ የተውጣጡ ወደ 40 የሚጠጉ ተሳታፊዎች የተሳተፉበት ይህ ዝግጅት የአቶሚክ ቦምብ ጥቃት የደረሰበትን 79ኛ ዓመት ‘ከኒውክሌር ጦር መሳሪያ ነፃ የሆነች ዓለም አጋርነት’ አንደኛ ዓመት ጋር በመገጣጠሙ በድምቀት ተከብሯል።
ከታዋቂዎቹ ታዳሚዎች መካከል የናጋሳኪ ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ፒተር ሚቺያኪ ናኩሙራ እና የሂሮሺማ ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ አሌክሲስ ሚትሱሩ ሺራሃማ፣ በዩናይትድ ስቴትስ የሲያትል ሊቀ ጳጳሳት ብጹእ አቡነ ፖል ዲ ኤቲየን እና የሳንታ ፌ ጆን ሲ ዌስተር ይገኙበታል።
የፓክስ ክሪስቲ ኮርያ ተባባሪ ፕሬዝዳንት የሆኑት አንሴልሞ ሊ መድረኩን የከፈቱት ታሪካዊ ዳራዎችን በማንሳት እና ከኢዮቤልዩ ዓመት እስከ 2027ቱ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ያለውን ፍኖተ ካርታ በመዘርዘር ነው።
ሊቀ ጳጳስ ናካሙራ ለሰላም እና የአቶሚክ ቦምብ ጥቃቱን ለማስታወስ የሚደረገውን የጋራ ጥረት አስፈላጊነትን በአጽንዖት ጠቅሰዋል። የውይይት መድረኩ ተናጋሪዎች የቅርብ ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን፣ የደቡብ ኮሪያን የሰላም እንቅስቃሴዎች እና የ2017 የኑክሌር ጦር መሳሪያ ክልከላ ስምምነትን የማስተዋወቅ ስልቶችን በማንሳት የተነጋገሩበት የተለያዩ ክፍለ ጊዜዎች ተካተዋል።
ከውይይቶቹ ውስጥ በጎረጎሳዊያኑ 2027 ላይ በሴኡል በሚከበረው የዓለም ወጣቶች ቀን እንዴት ሰላምን ማበረታታት እንደሚቻል በማንሳት ሰፊ ዳሰሳ አድርገዋል።
በፎረሙ ስለ ሰላም የሚሰሩ የካቶሊክ ድርጅቶች እና በወጣቶች መካከል የተጠናከረ ትብብር እንዲደረግ እና የኑክሌር ስምምነቱ ሰነድ መጽደቅን በመደገፍ የናጋሳኪ የሰላም ጥሪ በይፋ ተዋውቋል።
ይህ ሰነድ በነሃሴ ወር መጨረሻ ላይ በመደበኛነት ፀድቆ ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ መስከረም 10 ቀን 2017 ዓ.ም. የፓክስ ሮማና 100ኛ የምስረታ በዓል ላይ ይቀርብላቸዋል ተብሎም ይጠበቃል።