አባ ፍራንችስኮስ ፓቶን ለሰላም እንዲጸልዩ የቀረበላቸውን ጥሪ ተቀበሉ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በቅድስት አገር የላቲን ሥርዓት የምትከተል ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በመላው ዓለም ሰላም እንዲሰፍን ጸሎት እንዲደረግ በማለት ነሐሴ 4/2016 ዓ. ም. ካቀረቡት ጥሪ ጋር አባ ፍራንችስኮስ ፓቶን በፍልሰታ ማርያም ክብረ በዓል ዕለት ሁሉም ሰው ለእርቅ እና ሰላም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አጥብቆ እንዲለምን አደራ ብለዋል።
በቅድስት አገር የሚኖሩት ፍራንችስካውያን ወንድሞች በክልሉ የሚገኙ ቅዱሳን ቦታዎችን በመጠበቅ ለማኅበረሰቡ ሐዋርያዊ እንክብካቤ እና ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም ማኅበራዊ እና ትምህርታዊ አገልግሎቶችን በማበርከት ላይ ይገኛሉ። በቅድስት አገር ውስጥ ለስምንት መቶ ዓመታት የኖሩት ፍራንችስካውያን ወንድሞች በአካባቢው አገልግሎታቸውን ማበርከት የጀመሩት የማኅበራቸው መሥራች ቅዱስ ፍራንችስኮስ በ13ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ መካከለኛውን ምሥራቅን በጎበኘበት ዘመን እንደ ነበር ይታወሳል።
ተስፋ ሰጪ ምልክት
“ለሰላም ጸሎት ማድረግ በሚያስፈልግበት አስቸጋሪ ጊዜ ላይ እንገኛለን” ያሉት አባ ፍራንችስኮስ “ተስፋ ሰጪ ምልክቶችን” በመጥቀስ በጀመሩት መልዕክታቸው፥ ተፋላሚ በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ፣ ታጋቾችን ነጻ ለማውጣት እና የፖለቲካ እስረኞችን ለመፍታት የተጀመረውን ድርድር ለመቀጠል መስማማታቸውን ገልጸው፥ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በስጋ እና በነፍስ ወደ ሰማይ የገባችበትን ቀን በምናከብርበት ቀን ይህ ለእኛ በምድር ላይ ለምንገኝ ምዕመናን እርግጠኛ የተስፋ እና የመጽናናት ምልክት ነው” ብለዋል።
ለሰላም የቀረበ ብርቱ ጸሎት
አባ ፍራንችስኮስ ለፍራንችስካውያን ወንድሞች ባስተላለፉት መልዕክታቸው የፍልሰታ ማርያም ዓልን በልዩ መንገድ በማክበር ለሰላም እንዲጸልዩ አደራ አብለዋል። በዮሐንስ ራዕይ ምዕ. 12:1 ላይ እንደተጠቀሰው፥“ለመውለድ የተቃረበች ሴት ምልክት በሰማይ በታየ ጊዜ ዘንዶ ተገልጦ በልጆቿ ላይ እንደ ተነሳ እናውቃለን ብለው፥ በሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል የሚመሩ የሰማይ ኃይሎች እንደተቃወሙት አስረድተዋል። በዚህ ምክንያት ይህ ቀን የጠንካራ ጸሎት ዖለት መሆን እንዳለበት እንዲሁም በኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ የሚጠቀሙበትን የጸሎት መንገድ በመከተል የሚከተለውን ጸሎት አቅርበዋል።
ወደ ሰማይ ለወጣች እመቤታችን ማርያም ዘንድ የቀረበ የሰላም ጸሎት
"የከበርሽ የእግዚአብሔር እናት ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ! ከሊቀ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል እና ከሰማይ መላእክት እና ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ሆነሽ ወደ ተወደደው ልጅሽ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ለምኚልን።ለቅድስት አገር እና በውስጧ ለሚኖሩት ልጆች በሙሉ የእርቅ እና የሰላም ስጦታ ተቀበዪልን።
ትንቢትሽም ይፈጸም ዘንድ፥ ትዕቢተኞች ከነአሳባቸው ተበታትነዋል። ታላላቅ ገዥዎች ከዙፋናቸው ወርደዋል። በመጨረሻም ትሑታን ይነሳሉ፤ የተራቡትም በመልካም ነገር ይጠግባሉ። ሰላማውያን የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸው ይታወቃል፤ የዋሆችም ምድርን በስጦታ ይቀበሏታል።
ዛሬ አንቺን በዝማሬ ከፍ ከሚያደርጉሽ መላእክት ጋር፣ የመንግሥቱን ዘውድ ከሚያጎናሽፍፉሽ ጋር በዘላለማዊ ግርማ ዙፋኑ ላይ አስቀምጦሻል። ለልጅሽ ለኢየሱስ ክርስቶስ ክብር እና ምስጋና ለዘላለም ይሁን። አሜን።"