አባ ገብርኤል ሮማኔሊ የተኩስ አቁሙ ድርድር ወደ ሰላም እንዲያደርስ ያላቸውን ምኞት ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በጋዛ ብዙ ሰዎች እየሞቱ ባሉበት ወቅት በኳታር ዶሃ ሲካሄድ የቆየው የተኩስ አቁም ስምምነት ድርድር ማብቃቱ ታውቋል። ሐሙስ ነሐሴ 9/2016 ዓ. ም. በጃባሊያ እና ኑሴይራት የስደተኞች ካምፖች ላይ ከባድ የቦምብ ድብደባ መካሄዱ ሲታወስ ቀጣዩ ድርድርም በካይሮ እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
በአባ ገብርኤል ሮማኔሊ የሚመራው እና በጋዛ ሰርጥ የሚገኝ የቅድስት ቤተሰብ ቁምስና ክርስቲያን ማኅበረሰብ እነዚህን ንግግሮች በጸሎት እና በታላቅ ተስፋ እየተከታተለ እንደሚገኝ ታውቋል። የጎርጎሮሳውያኑን የቀን አቆጣጠር የሚከተሉ በጋዛ ሰርጥ የሚገኙ የቅድስት ቤተሰብ ቁምስና ካቶሊክ ምዕመናን የፍልሰታ ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓልን ነሐሴ 9/2016 ዓ. ም. በአጫጭር ኡደቶች አክብረው ውለዋል።
የቦምብ ጥቃቶች ቢቀጥሉም የሰላም ተስፋ ህያው ነው
አባ ገብርኤል ከቫቲካን መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ የሰላም ድርድር ፍሬው በሚቀጥለው ሳምንት ብሩህ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸው፥ “ምንም ይሁን ምን የቦምብ ፍንዳታው ቀጥሏል” ሲሉ ሐዘናቸውን ገልጸዋል። “ሐዘኑ የቀጠለ ቢሆንም የተኩስ አቁም እና ታጋቾችን የመፍታት ስምምነት ለዚህ ጦርነት ማብቃት የመጀመሪያ እርምጃ ከሆነ መልካም ዜና ነው” ብለዋል።
መከራ ውስጥ ቢሆንም የፍልሰታ በዓል በአስደናቂ ሁኔታ ተከበረ
የጎርጎሮሳውያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ ካቶሊክ ምዕምናን ዘንድ የፍልሰታ ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል ነሐሴ 9/2016 ዓ. ም. በድምቀት መከበሩን ያስታወሱት አባ ገብርኤል፥ የጋዛ ሰርጥ ምዕመናን “ሕመም እና ድካም ቢያጋጥማቸውም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ዓመታዊ ክብረ በዓል በአስደናቂ ሁኔታ ማክበር መቻላቸውን ተናግረዋል።
ምዕመናኑ በመከራ ውስጥ ሆነው የእመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያምን ዓመታዊ በዓል ለማክበር በመፈለጋቸው ምን ያህል አስደናቂ እንደሆኑ ገልጸው፣ የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና የቅዱስ ሚካኤልን አማላጅነት እንዲጸልዩ የጠየቁትን ጥያቄ በደስታ መቀበላቸውን አባ ገብርኤል አስታውሰዋል።
ለአንድ ሰዓት በፀጥታ ከጸለዩ እና በአረብኛ ቋንቋ ምስጋናን እና የመቁጠሪያ ጸሎትን ካደረሱ በኋላ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን መካፈላቸውን ተናግረው፥ መላው የጋዛ ሰርጥ ምዕመናን ከዚህ በፊት ለቅድስት ቤተሰብ ያቀረቡትን ጸሎት ማደሳቸውንም ገልጸዋል።
የሰላም አየር መንፈሱ የእመቤታችን ማርያም ተአምር ነው!
አባ ገብርኤል ሮማኔሊ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እያደገ የመጣውን የምዕመናኑን መንፈሳዊነት ሲገልጹ፥ “ከጥቂት ዓመታት በፊት ለሦስት ዓመታት መንፈሳዊ ጉዞ መዘጋጀታቸውን ገልጸው፥ የመጀመሪያው ዓመት ወደ ልበ ኢየሱስ፣ ሁለተኛው ዓመት ወደ ልበ ማርያም እና ሦስተኛው ወደ ቅዱስ ዮሴፍ ጸሎት የሚቀርብበት እንደሆነ ገልጸዋል።
በቅዱስ ቤተሰብ ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በተመረጡ ዝማሬዎች የታጀበውን ኡደት የጠቀሱት አባ ገብርኤል፥ ቀጥሎም የካቶሊክ እና የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ምዕመናን ያሳተፈ ስብሰባ ከተካሄደ በኋላ ምግብ እና የጽዳት ዕቃዎች ለታዳሚዎች መታደሉን ገልጸዋል።
በዕለቱ ሁሉም ምዕመናን ደስተኞች እንደ ነበሩ ያስታወሱት አባ ገብርኤል፥ “እመቤታችን እና ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስም ደስተኞች እንደ ነበሩ አስባለሁ” በማለት ተናግረው፥ “ይህ እየተሰማን ያለው የሰላም አየር የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተአምር እንደሆነ ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።