ብጹዕ አቡነ ጆሴፍ ሃ ቺ-ሺንግ በእንግሊዝ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ብጹዕ አቡነ ጆሴፍ ሃ ቺ-ሺንግ በእንግሊዝ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው  

አቡነ ጆሴፍ ሃ ቺ-ሺንግ ስደተኞች በእምነታቸው እንዲጸኑና ለሌሎችም እንዲያካፍሉ አሳሰቡ

የሆንግ ኮንግ ከተማ ረዳት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጆሴፍ ሃ ቺ-ሺንግ በእንግሊዝ ያደረጉትን የ10 ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት አጠናቅቀዋል። ብጹዕነታቸው በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ወደ አሥራ አንድ አካባቢዎች የሄዱ ሲሆን፥ በሄዱባቸው አካባቢዎች ከሆንግ ኮንግ ስደተኞች ጋር ተገናኝተው መንፈሳዊ ድጋፋቸውን ገልጸውላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕነታቸው ከሐምሌ 12-22/2016 ዓ. ም. ድረስ በእንግሊዝ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ዋና ዓላማ በስደተኞች መካከል ያለውን የአንድነት ስሜትን ለማዳበር እና በአስቸጋሪ ሁኔታዎች መካከል እምነታቸውን አጥብቀው እንዲይዙ ለማበረታታት እንደሆነ ታውቋል።

ለስደተኞቹ ባደረጉት ንግግርም “በእንግሊዝ ውስጥ የሚኖሩ የሆንግ ኮንግ ካቶሊክ ምዕመናን እምነታቸውን ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱት፣ ጌታን ለማየት እንደሚጓጉ እና በየጊዜው በሚለዋወጠው አስቸጋሪ የስደት ሕይወት የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች በመጋፈጥ ወደማይለወጠው አምላክ መቅረብ እንደቻሉ ይሰማኛል” ብለው፥ ይህም በእምነቴ ተነሳሳችነትን እና ብርታትን ሰጥቶኛል!” ብለዋል።

የአቡነ ጆሴፍ ሃ ቺ-ሺንግ ሐዋርያዊ ጉብኝት መርሃ ግብር ማንቸስተርን፣ ሊቨርፑልን፣ በርሚንግሃምን፣ ኖቲንግሃምን፣ ካምብሪጅን፣ ሚልተን ኬይንስን፣ ምሥራቅ ለንደንን፣ ብሪስቶልን፣ ምዕራብ ለንደንን፣ ኬንትን እና ሪዲንግን እንደሚያካትት ታውቋል።

ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት፣ በመንፈሳዊ ንግግሮች፣ በጸሎት፣ በአስተንትኖ እና በኅብረት በሚደረጉ ስብሰባዎች እና በኑዛዜ የታገዘ ሲሆን፥ በተለይም ቻይናውያን ስደተኞችን በማስተናገድ የተካሄደ እንደ ነበር ታውቋል።

አቡነ ጆሴፍ ሃ ቺ-ሺንግ የእንግሊዝ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ሐምሌ 12/2016 ዓ. ም. የጀመሩት በቅድሚያ ወደ ማንቸስተር በመጓዝ ከአካባቢው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጋር የተገናኙ ሲሆን፥ የሳልፎርድ ሀገረ ስብከት ለአካባቢ ጥበቃ ያለውን ቁርጠኝነት በማጉላት የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ማዕከልን ጎብኝተዋል።

ብጹዕነታቸው በተጨማሪም ከሰሜን እንግሊዝ፣ ከግላስጎው እና ከአየርላንድ ከመጡ ከ130 በላይ ምዕመናን ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር አምስት ቁልፍ ባህሪያት እንዳለው በዝርዝር ተናግረዋል።

ከ300 በላይ ምዕመናን በተካፈሉበት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባሰሙት ስብከትም ለእግዚአብሔር ትዕዛዝ የመገዛት አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥተዋል። “አስደናቂው አምላክ” በሚል ርዕሥ በበርሚንግሃም ሐምሌ 14/2016 ዓ. ም. ባሰሙት ስብከት በስደተኞች ዕለታዊ ፈተና ውስጥ የእግዚአብሔርን መገኘት አጉልተው አሳይተዋል።

ሐምሌ 16 እና 17 በካምብሪጅ ባደረጉት ቆይታ ወደ 120 የሚጠጉ ምዕመናን የተካፈሉበትን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና የእንግሊዛዊው ሰማዕታት ዓመታዊ በዓል መስዋዕተ ቅዳሴን መርተዋል። በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ ባሰሙት ስብከት የሆንግ ኮንግ ስደተኞች በእንግሊዝ ውስጥ ወንጌልን እንዲያሰራጩ አሳስበዋል።

አቡነ ጆሴፍ ሃ ቺ-ሺንግ በካምብሪጅ በሚገኘው የኪንግ ኮሌጅ ጉብኝት ለቻይና ገጣሚ ሹ ዢሞ በተዘጋጀው የመታሰቢያ በዓል ላይ የተገኙ ሲሆን፥ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ስደተኞቹን ያሳደጋቸው ያህል እንዳሳደጋቸው ገልጸዋል።

አቡነ ጆሴፍ ሃ ቺ-ሺንግ በምስራቅ ለንደን ባደረጉት ጉብኝታቸውም ጉባኤው ትሕትናን እና አገልግሎትን እንዲቀበል በመጠየቅ ታላቅነት ሌሎችን በማገልገል እንደሚገኝ በማስረዳት ስደተኞቹ ወንጌልን እንዲሰብኩ እና በአዲሱ የመኖሪያ አካባቢ እምነታቸውን ከሌሎች ጋር እንዲጋሩት አደራ ብለዋል።

ብጹዕነታቸው አዲሶቹ የሆንግ ኮንግ ስደተኞች እንግሊዝ ውስጥ በሚገኙ ቁምስናዎች በሚያደርጉት አዎንታዊ ተሳትፎ የድጋፍ ቡድኖችን በመመስረት ለቻይናውያን ማኅበረሰቦች የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ እንክብካቤ እና ዕርዳታን አወድሰዋል።

የብጹዕነታቸውን ጉዞ ያስተባበረው ቡድን አባል ወ/ሮ አንጀሊና የአካባቢው ደጋፊ ማኅበረሰብ በቤተ ክርስቲያን በመታቀፍ የተመቻቸ እና የተስተካከለ የዕቅድ ሂደት ተግባራዊ ማድረጉን ተናግረዋዋል።

የሆንግ ኮንግ ሀገረ ስብከትን በመወከል በእንግሊዝ የሚገኙ ስደተኛ ማኅበረሰቦችን የመርዳት ኃላፊነት የተሰጣቸው አባ ብሩኖ ሌፔ በሎጂስቲክስ አስተዳደር እና ከአቡነ ጆሴፍ ሃ ቺ-ሺንግ ጋር በማስተባበር ትልቅ ሚና መጫወታቸው ተገልጿል።

የአቡነ ጆሴፍ ሃ ቺ-ሺንግ ሐዋርያዊ ጉብኝት ብዙ የካንቶኒዝ ተናጋሪ ምዕመናንን የሳበ ሲሆን ይህም ቀደም ሲል በቋንቋ መሰናክሎች ወይም በርቀት ምክንያት በቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎች ብዙም ንቁ ያልነበሩ ሲሆን፥ ከብጹዕንታቸው እና ከማኅበረሰባቸው ጋር የመገናኘት ዕድል በስደተኞቹ አድናቆትን ማግኘቱ ታውቋል።

ወደ ሆንግ ኮንግ የተመለሱት ብጹዕ አቡነ ጆሴፍ ሃ ቺ-ሺንግ በእንግሊዝ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በሆንግ ኮንግ ካቶሊካዊ ስደተኞች እምነት እና አንድነት ላይ ዘላቂ ተጽእኖ ማሳደሩን ገልጸው፥ ይህም ከአዲሱ የሆንግ ኮንግ ማኅበረሰብ ጋር መዋሃድን እንዲቀጥሉ ማነሳሳቱን አስረድተዋል።


 

06 August 2024, 16:55