የሪሚኒ ስብሰባ የሪሚኒ ስብሰባ 

የእስራኤላውያን እና ፍልስጤማውያን የወደፊት ህይወት 'እርስ በርስ በመከባበር ላይ የተመሰረተ ነው' ተባለ

በሰሜን ጣሊያን በምትገኘው ሪሚኒ ከተማ ከ400 በላይ ተሳታፊዎች የተገኙበት 45ኛው የሕዝቦች የወዳጅነት ስብሰባ ወቅት እስራኤላዊው ራሚ ኤል-ሃናን እና ፍልስጤማዊው ባሳም አራሚን በቅድስት ሀገር ለአስርት ዓመታት በዘለቀው ግጭት ሴት ልጆቻቸውን ያጡበትን ታሪካቸውን በማካፈል፣ በእስራኤል እና በሃማስ መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ቆሞ እርቅ እንዲፈጠር ጠይቀዋል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ክርስቲያኖች በሕይወታቸው አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እንዲወያዩ በተጋበዙበት እና በርካታ ተሳታፊዎች የተገኙበት 45ኛው የሕዝቦች የወዳጅነት ስብሰባ መድረክ ላይ አቢር እና ስማዳር የሚባሉት የሁለቱ ሰዎች ሴት ልጆች ፎቶዎች የታዩ ሲሆን፥ እነዚህ ሁለት ሟች አፍላ ወጣት ልጃገረዶች በብዙ ነገር እንደሚመሳሰሉ ከምስላቸው ላይ ለመረዳት እንደሚቻልም ተገልጿል።

የ13 ዓመቷ እስራኤላዊት ስማዳር በማዕከላዊ እየሩሳሌም በፍልስጤማዊ አጥፍቶ ጠፊ የተገደለች ሲሆን፥ የ10 ዓመቷ ፍልስጤማዊት አቢር ከትምህርት ቤቷ አቅራቢያ እያለች በአንድ ወጣት እስራኤላዊ ወታደር በጥይት ተመትታ ሞታለች። የእነዚህ ወጣት ልጃገረዶች አሳዛኝ፣ ዘግናኝ እና ሊገለጽ የማይችል እጣ ፈንታ አስከፊውን የእስራኤል እና የፍልስጤም ግጭት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል ተብሏል።

የሁለቱም ልጆች ቤተሰቦች ልጆቻቸውን በማጣታቸው እንደሌሎቹ ሁሉ በከፍተኛ ሃዘን እና ስቃይ ውስጥ የነበሩ ቢሆንም፥ ዛሬ ግን ስለ ሰላምና እርቅ እየመሰከሩ ይገኛሉ።

ከሁለቱ ጎራ የሆኑት የሟች ሴት ልጆች አባቶች ራሚ ኤልሃናን እና ባሳም አራሚን እ.አ.አ. በ 1995 ዓ.ም. ኤሪክ የሚባል ወንድ ልጁ ከሃማስ ጋር ግንኙነት ባላቸው አሸባሪዎች ታፍኖ የተገደለበት አይዛክ ፍራንክንታል በተባለ ሰው የተመሰረተው ‘ዘ ፓረንት ሰርክል’ የሚባለው የወላጆች ማህበር አባል በመሆን ለዓመታት እንደቆዩም ተነግሯል።

አርብ ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም. የሟቾቹ ወላጆች ስለገጠማቸው ታሪክ የሚተርክ፣ አንዳቸው ለሌላኛው ህመም እውቅና የሚሰጡበት እና ለወደፊት የተሻለ ህይወት በጋራ ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት የገለጹበትን በኮሎም ማካን የተፃፈውን “አፔሮጎን” (Apeirogon) የተሰኘውን መጽሃፍ ለማስተዋወቅ በስብሰባው ወቅት ወደ መድረክ ወጥተው ነበር።

ከነሐሴ 14-19 ቀን 2016 ዓ. ም. ለአንድ ሳምንት በተካሄደው 45ኛው የሕዝቦች የኅብረት እና የነጻነት ዓመታዊ ጉባኤ ወቅት ከነበሩት 140 የሚሆኑ የውይይት ርዕሶች እና በርካታ አስተንትኖዎች፣ ንግግሮች እና ግኝቶች ከተገለጹበት መርሃግብሮች መካከል የአርብ ዕለቱ ክስተት በጣም ልብ የሚነካ እንደነበረ ተነግሯል።

ከጥላቻ ወደ ይቅርታ
ባሳም አራሚን የተባለው ፍልስጤማዊ በፊት የነበረው አመለካከት የተቀየረበትን ጊዜ በማስታወስ፥ “እስር ቤት በነበርኩበት ወቅት በርካታ እስራኤላዊያን የተጨፈጨፉበትን ታሪክ ስለሚተርከው የሆሎኮስት ፊልም በመመልከት ራሴን ለማስደሰት እፈልግ ነበር” ካለ በኋላ፥ “ለእኔ ይህ የበቀል አይነት ነበር፣ ሌሎች ሲሰቃዩ እና ሲገደሉ ማየት እፈልግ ነበር፥ ነገር ግን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እነዚህ የሚገደሉት ሰዎች ንፁሀን መሆናቸውን ሳስተውል ማልቀስ ጀመርኩ፥ ከ25 ዓመታት በኋላ ይህ ፊልም በአይሁድ ማህበረሰብ አስተሳሰብ ውስጥ ያለውን ስጋት ለመረዳት እና ስለ ሆሎኮስት ጥናታዊ ፅሁፌን እንድፅፍ ገፋፍቶኛል” ብሏል።

‘ጠላትህን ማወቅ ማለት እሱን መረዳት መጀመር ማለት ነው’ ያለው ባሳም፥ ይህም በጋራ ተቀምጠህ ለመነጋገር የሚያስችል የመጀመሪያው እርምጃ ነው በማለት አክሏል።

ፍልስጤማዊ መሆን፣ በተለይም በእስራኤል ግዞት ሥር ቀላል እንዳልሆነ በመጠቆም፥ ግድያውን ለማስቆም ይህ በፍጥነት ማብቃት አለበት ብሏል።

“ሀማስ የፍልስጤም ህዝብን አይወክልም፥ ነገር ግን የፍልስጤማውያን አካል ነው” ሲል ያስረዳው አራሚን፥ “ጭቆና ተቃውሞን ይፈጥራል፥ ይህ ሁኔታ ለብዙ አሥርተ ዓመታት አልተለወጠም፥ በመሆኑም የበለጠ ስቃይን እና የበለጠ ተጎጂዎችን ይፈጥራል፥ የእስራኤል መንግስት ለፍልስጤማዊያን እውቅና ሊሰጥ ይገባል፣ ፍልስጤማውያን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት አላቸው” በማለት መልዕክቱን አስተላልፏል።

በግድግዳው ላይ ያሉ ስንጥቆች
ራሚ ኤልሃናን የተባለው እስራኤላዊ የሟች ወላጅ በበኩሉ ወንድማማችነትን በማስመልከት ያብራራ ሲሆን፥
“ፍቅርን ለመግለጽ እና ለመረዳት አንድን ሰው በህይወት ማጣት አይኖርብንም፥ በእኛ ቦታ መሆንም አያስፈልግም” ካለ በኋላ፥ “እኛ ባሳለፍንበት ሁኔታ ያለፉ ብዙ ወላጆች በቀልን ይፈልጋሉ፥ በግጭቱ አዙሪት ውስጥ የቆዩ በርካታ የተናደዱ ሰዎች አሉ፥ ሌሎች ብቻቸውን ይሞታሉ፣ እኛ ግን አሁንም በህይወት አለን፣ እኛ እውነተኛ እና ተጨባጭ ምሳሌ ነን” በማለት ገልጿል።

ራሚ እና ባሳም በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የወዳጅነት እና የመከባበር መልእክታቸውን ሲያካፍሉ ብዙ የእስራኤላውያን እና የፍልስጤማዊያን ልጆች በጣም ይገረሙ እንደነበር በማስታወስ፥ “እኛ በምናወራበት ወቅት ተማሪዎቹ በመገረም ይመለከቱናል፣ መሬት እየተንቀጠቀጠ ያለ ይመስላል፣ ልክ ወደ እሳተ ገሞራ አፋፍ እንደመግባት ነው፥ ምክንያቱም በሁለቱ ህዝቦች መካከል የደም ወንዝ ይፈሳልና፥ ብዙ ጊዜ ወንድማማቾች ነን ማለታችንን ሲሰሙ ሁሉም ነገር ይለወጣል። እኔ በአረብኛ ጥቂት ቃላት ስናገር እና ባሳም በዕብራይስጥ የተወሰነ ቃል ሲናገር፥ የግድግዳው ስንጥቆች ተንደው የብርሃን ፍንጣቂ ሲገባ እንደማየት እና እንደመስማት ነው” በማለት ያለውን ስሜት ተናግሯል።

መከባበር አስፈላጊ ነው
ራሚ እና ባሳም መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም. በቫቲካን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር ያደረጉትን ቆይታ እና ብጹእነታቸው የሴት ልጆቻቸውን ፎቶዎች ሲመለከቱ የተሰማቸውን ስሜት በግልፅ እንደሚያስታውሱ ጭምር አንስተዋል።

ራሚ ኤልሃናን በሪሚኒ ከተማ የነበረውን ዝግጅት ሲያጠናቅቅ “ሀማስ ልጄን ገድሎብኛል” በማለት ሃማስን ለመውደድ ምንም ምክንያት እንደሌለው በመግለጽ፥ ሆኖም መስከረም 26 የተፈፀመው ጥቃት የእስራኤል እና የፍልስጤምን ጉዳይ የዓለም ትኩረት እንዲያገኝ አድርጓል በማለት በአፅንዖት ተናግሯል።

“መፍትሄውን ባላውቅም የወደፊት ህይወታችን ‘መከባበር!’ በሚለው በአንድ ቃል ላይ የተመሰረተ መሆኑን አውቃለሁ” የሚለው ራሚ፥ “አክብሮት ለፍልስጤም መንግስት እውቅና በመስጠት ይጀምራል፣ ወረራውን በማቆም በታሪካችን ውስጥ አዲስ ምዕራፍ መጀመር ያስፈልጋል” ብሏል።
 

26 August 2024, 14:35