የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ 

የናይጄሪያ ብጹአን ጳጳሳት በሀገሪቱ ያለው ሁኔታ አስከፊ ወደሆነ ነገር ሊሸጋገር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል

የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ቦላ ቲኒቡ ያወጡትን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ በሃገሪቱ የተነሳው ኃይለኛ ተቃውሞ ተፋፍሞ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት፥ የናይጄሪያ ብጹአን ጳጳሳት በተቃዋሚዎች የተነሱትን ጉዳዮች በአስቸኳይ መፍታት እንደሚገባ አሳስበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የናይጄሪያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት መንግስት በሃገሪቷ ውስጥ የተንሰራፋውን ድህነት፣ ችግር እና የሙስና ጉዳዮች በጥሞና እስካልፈታ ድረስ ይህች አፍሪካዊት ሀገር በቅርብ ጊዜ ውስጥ ተጨማሪ ተቃውሞዎችን ልታስተናግድ እንደምትችል አስጠንቅቀዋል።

ብጹአን ጳጳሳቱ ማስጠንቀቂያውን ያስተላለፉት እሁድ ዕለት በተጀመረው የናይጄሪያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን በኢዶ ግዛት፣ በአውቺ ከተማ በጀመሩበት ወቅት ሲሆን፥ የማስጠንቀቂያውን መልዕክት ይፋ ያደረጉት የጳጳሳት ጉባኤው ፕሬዝዳንት የሆኑት የኦዌሪ ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ሉሲየስ ኡጎርጂ እንደሆኑም ተገልጿል።

በፕሬዚዳንት ቲኑቡ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ላይ የተነሱ ተቃውሞዎች
ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ናይጄሪያ እየጨመረ የመጣውን የዕዳ ጫና እና የበጀት ጉድለትን ለመቅረፍ በሚል በፕሬዚዳንት ቦላ ቲኑቡ ይፋ የተደረገውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ ሃገሪቷ ከፍተኛ አለመረጋጋት ውስጥ ገብታለች።

የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ቦላ ቲኑቡ ባለፈው ዓመት ይፋ ያደረጉት የኢኮኖሚ ማሻሻያ እቅድ፣ የነዳጅ ድጎማን ማስቀረቱ እና የኒያራ የምንዛሬ ዋጋ እንዲያሽቆለቁል ማድረጉ የኑሮ ውድነት ቀውስ አምጥቶብናል በማለት በርካታ ናይጄሪያዊያን ይወነጅላሉ፡፡ ይሄን ተከትሎ በነሀሴ ወር መጀመሪያ ላይ ‘#BadBadGovernance’ በሚል ሃሽታግ የተጀመሩት ህዝባዊ ተቃውሞዎች ወደ ተለያዩ የሃገሪቱ ግዛቶች ተንሰራፍቷል። እየተባባሰ የመጣውን የዋጋ ግሽበት፣ የሃገሪቷ ገንዘብ ዋጋ ማሽቆልቆል እና መንግስት ያነሳው የነዳጅ ድጎማዎች ሃገሪቷን የከፋ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ውስጥ ያስገባል በሚል በህዝቡ ዘንድ ብስጭት በመፈጠሩ እና እነዚህ ጉዳዮች ከፍተኛ የኑሮ ውድነትን አስከትለዋል በሚል እንደሆነም ተነግሯል።

በርካታ ናይጄሪያውያን እንደ ምግብ እና መጓጓዣ ያሉ መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለማግኘት ከባድ ፈተና እያጋጠማቸው እንደሆነ ይነገራል።

ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት የታቀዱት የፕሬዚዳንት ቲኑቡ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ ለበርካታ ናይጄሪያውያን ሁኔታውን እንዳባባሰባቸው እና ይህም በህዝቡ ዘንድ ሰፊ ቅሬታ እንዳስከተለ ዘገባዎች ያሳያሉ።
ይሁን እንጂ ተቃውሞው በአንዳንድ አካባቢዎች በተለይም እንደ ካዱና ባሉ በርካታ ተቃዋሚዎች የተገደሉበት ሰሜናዊ ግዛቶች ተቃውሞው ወደ ሁከት የተቀየረ ሲሆን፥ ሁከቱን ለማስቆም የካኖ እና ፕላቶ ግዛቶችን ጨምሮ በተለያዩ አከባቢዎች የሰዓት እላፊ ተጥሏል።

ለድህነት እና ሙስና አፋጣኝ መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል
በናይጄሪያ ብጹአን ጳጳሳት ጉባዔ መክፈቻ ላይ ስለ እነዚህ ሁኔታዎች አስተያየታቸውን የሰጡት ሊቀ ጳጳስ ኡጎርጂ በአንዳንድ ሁከት ፈጣሪዎች የተፈፀመውን ጥቃት ካወገዙ በኋላ ተቃውሞ ያሰሙ ወጣቶች በጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውንም ጭምር ተናግረው “በሀገሪቷ የተንሰራፋው ድህነት፣ ችግርና ሙስና እስካልተቀረፈ ድረስ እና የሀገራችን ወጣቶች የወደፊት እጣ ፈንታ አስከፊ እስከሆነ ድረስ ተቃውሞ ማሰማታችንን እንቀጥላለን” ሲሉም ተናግረዋል።

በመሆኑም የፌደራል መንግስቱን ምላሽ በተለይም አንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናት “ችግሩን ከመፍታት ይልቅ” ኃላፊነታቸውን በሌሎች ላይ በማስተላለፍ “ሌሎቹን በሃሰት ለመወንጀል እየጣሩ” ነው ሲሉም ተችተዋል።

“ሰዓቱን ጠብቆ እንደሚፈነዳ ቦምብ”
ሊቀ ጳጳስ ኡጎርጂ እንዳሉት በአንዳንድ ተቃዋሚዎች ላይ የተወሰደው የኃይል እርምጃ እና እስራት፣ የዜጎችን ዲሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች ለመግፈፍ የሚደረግ ሙከራ ወይም በአገሪቱ ውስጥ ያለው ነገር ሁሉ ጥሩ እንደሆነ ለማስመሰል የሚደረገውን ጥረት በማውገዝ፣ “ይህ አሳሳች እና የሚወገዝ ነገር ነው” በማለት አገሪቱ ሰዓቱን ጠብቆ እንደሚፈነዳ ቦምብ በጊዜ መፍትሄ ካልተበጀለት “አስቸጋሪ ነገር ውስጥ ልትገባ ትችላለች” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

እንደ ጳጳሳቱ ገለጻ፣ ምንም እንኳን በአንዳንድ ዘርፎች መሻሻል ቢታይም፣ አሁን በሀገሪቱ ያለው ሁኔታ “አስከፊ” መሆኑን ጠቁመው፥ ናይጄሪያን እየተፈታተኑ ካሉት ችግሮች ውስጥ የጸጥታ ችግር አንዱ እንደሆነም ጭምር አንስተዋል።

ምንም እንኳን አለመረጋጋቶች ቢኖሩም የፕሬዚዳንት ቲኑቡ መንግስት ይፋ ያደረገው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ለረጅም ጊዜ እድገት አስፈላጊ መሆኑ እየተገለጸ ሲሆን፥ ይሁን እንጂ ብዙ ናይጄሪያውያን ከገጠማቸው የኢኮኖሚ ጫና አፋጣኝ እፎይታ ያስፈልጋቸዋል ተብሏል።

ተቃዋሚዎቹ የወጣው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ምንም ውጤት እንደሌለው አጥብቀው የሚከራከሩ ሲሆን፥ አንዳንዶች ትርጉም ያለው ውይይት እና የኢኮኖሚ ችግርን ሊቀርፉ የሚችሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች እንደሚያስፈልጉ ሲያምኑ፥ ሌሎች ደግሞ ብጥብጡ አገሪቱን የበለጠ ሊያናጋ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታውንም ሆነ ፖለቲካዊ መረጋጋትን ሊያባብስ ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።

በናይጄሪያ ባለፈው ዓመት የካቲት 18 ቀን 2015 ዓ.ም. በተደረገው እና በርካታ ናይጄሪያውያን በአፍሪካ ትልቁን ዲሞክራሲያዊ የአስተዳደር ለውጥ ያመጣል ብለው ተስፋ ባደረጉት አወዛጋቢ ምርጫ የገዢው ‘ኦል ፕሮግረሲቨ ኮንግረስ’ ፓርቲን ወክለው የተወዳደሩት ቦላ ቲኑቡ የቀድሞውን ፕረዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪን በማሸነፍ ስልጣን እንደያዙ ይታወሳል።
 

28 August 2024, 14:07