ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ  (Vatican Media)

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በሲንጋፖር በሚያደርጉት ሥርዓተ ቅዳሴ ላይ ለመገኘት ፍላጎቱ ስለጨመረ ተጨማሪ ትኬቶች እንዲዘጋጁ ተወሰነ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ወደ ሲንጋፖር በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉዞ መርሃ ግብር ላይ መስከረም 2 ቀን 2017 ዓ.ም. በሃገሪቷ ሊካሄድ በታቀደው ጳጳሳዊ ሥርዓተ ቅዳሴ ላይ ለመገኘት ከተጠበቀው በላይ ፍላጎት ስለታየ አዘጋጆቹ ተጨማሪ ትኬቶችን እንዲዘጋጁ በድምጸ ውሳኔ ማጽደቃቸው ተነግሯል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ መጪው መስከረም ላይ በሲንጋፖር የሚያደርጉትን ሃዋሪያዊ ጉዞ ተከትሎ፥ የጉብኝቱ መርሃ ግብር የቲኬት አከፋፋይ ንዑስ ኮሚቴ ኃላፊ አቶ ላውረንስ ቻን በመጀመሪያ ዙር ከተመዘገቡት አስር ተመዝጋቢዎች ቢያንስ ስድስቱ መቀመጫ ያገኛሉ ብለዋል።

የመጀመሪያው የምርጫ ውጤት ከሃምሌ 29 ጀምሮ ‘myCatholicSG’ በተባለው ድረ-ገጽ ላይ እንደሚለቀቅ የገለጹት አቶ ሚቻን “በዚህ ዙር ያልተሳካላቸው ተመዝጋቢዎች ወደ ሁለተኛው ዙር ይተላለፋሉ” በማለት አስረድተዋል።

የሁለተኛው ዙር ምዝገባ ሃምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ከጥዋቱ 11፡10 ላይ ተጀምሮ ነሃሴ 12 ቀን 2016 ዓ.ም. ምሽት 5፡59 ላይ የሚያበቃ ሲሆን፥ ውጤቱም ነሃሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ ይሆናል ሲል የሲንጋፖር ሃገረ ስብከት ህጋዊ ጋዜጣ የሆነው ‘ካቶሊክ ኒውስ’ ዘግቧል።

እየታየ ላለው ከፍተኛ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት ሲባል አዘጋጆቹ ከብሔራዊ ስታዲየም ኃላፊዎች ጋር በመተባበር 6,000 ተጨማሪ መቀመጫዎችን በማዘጋጀት አጠቃላይ የማስተናገድ የአቅም መጠኑን ወደ 48,600 አሳድገዋል።

እነዚህ አዳዲስ መቀመጫዎች ሥርዓተ ቅዳሴው የሚከናወንበትን የመሠዊያ ሥፍራን እና መድረኩን ለማየት የማያስችሉ በመሆናቸው ምክንያት ተሳታፊዎቹ ሂደቱን በቪዲዮ ስክሪኖች ላይ መከታተል እንዲችሉ የተመቻቸ መሆኑን አዘጋጆቹ ገልጸዋል።

ከቤተሰብ እና ከጓደኞች ጋር ለመሳተፍ የሚፈልጉ ግለሰቦች በቡድን መመዝገብ እንዳለባቸው እና ማካተትን ለማረጋገጥ ወደ ቡድን የመቀላቀል ግብዣዎችን መቀበል እንደሚጠበቅባቸው ተገልጿል። በተጨማሪም የቡድን ተመዝጋቢዎች እንደ ግለሰብ አመልካቾች ትኬቶችን የማግኘት እኩል እድሎች እንዳላቸው አዘጋጆቹ አረጋግጠዋል።

አቶ ቻን ይሄንን በማስመልከት ሁሉም ተሳታፊዎች የምዝገባ ውጤቶችን ለማየት ሃምሌ 29 ወደ myCatholicSG አካውንታቸው እንዲገቡ በመምከር፥ “በተጨማሪም ሂደቱን ቀለል ስላደረግነው ትኬቱን በተሳካ ሁኔታ ያገኙ ሰዎች ተጨማሪ እርምጃ መውሰድ አያስፈልጋቸውም” ብለዋል።

ከዚህ ቀደም የተሳካላቸው አመልካቾች ቲኬቶቻቸውን በእጅ መቀበል አለባቸው፣ የማይፈልጉ ከሆነ ደግሞ ቀደም ብለው መሰረዝ ይጠበቅባቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ በተሻሻለው ሂደት መሰረት የሥርዓተ ቅዳሴ መግቢያ ትኬት ድልድል ወዲያውኑ ተቀባይነት ያገኛል ተብሏል።

በመጀመሪያው የምዝገባ ድምጽ ቲኬት ያገኙ፣ ነገር ግን መገኘት ያልቻሉ ግለሰቦች በሁለተኛው የድምጽ መስጫ ካርድ ላይ ሌሎች ተሳታፊዎች እድል እንዲኖራቸው ትኬታቸውን እስከ ነሃሴ 12 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ መመለስ አለባቸው።  ትኬቶች አንዴ ከተመለሱ ድጋሚ መልሶ ማግኘት ስለማይቻል፥ ሌላ መቀመጫ ለማግኘት እንደገና ለመመዝገብ ብቁ አይሆኑም። አንዳንድ የቡድን አባላት ቲኬታቸውን ቢመልሱ እንኳን ቡድኖቹ ምንም ሳይበተን እንደሚቆዩም ተገልጿል።

አቶ ቻን ቲኬት የሚመለስበትን አካሄድ ሲገልጹ፥ ወደ myCatholicSG አካውንት በመግባት ‘ውድቅ ለማድርግ’ የሚለውን አማራጭ መምረጥ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፥ ትኬቶች ለተወሰኑ ግለሰቦች ብቻ ስለተዘጋጁ ለሌላ ሰው ማስተላለፍ እንደማይቻል በአፅንኦት ተናግረዋል።

ሃገረስብከቱ መሳተፍ ለማይችሉ ሰዎች በህጋዊ የዩቲዩብ ቻናሉ በኩል በቀጥታ ስለሚያስተላልፍ፥ ይህም ከቤት ሆነው መከታተል እንዲችሉ ያደርጋል ተብሏል።

ተጨማሪ ትኬቶችን ማዘጋጀት የተፈለገበት እና ቀላል የሆነ የምዝገባ አካሄድ መከተል የተፈለገበት ዓላማ በተቻለ መጠን ብዙ ምዕመናን በዚህ ታሪካዊ ክስተት ላይ እንዲገኙ ለማረጋገጥ ያለመ ነው ተብሏል።
 

05 August 2024, 17:09