የላውሬና "ካ ሉሪንግ" ፍራንኮ ፎቶ የላውሬና "ካ ሉሪንግ" ፍራንኮ ፎቶ  

የፊሊፒንስ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለአንዲት ካቴኪስት የቅድስና ክብር የሚያሰጥ ሥራዋን እያጠናቀረች እንደሆነ ተገለጸ

በፊሊፒንስ የምትገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዘመናቸውን በሙሉ ድሆችን በማገልገል እና ሃይማኖታቸውን በመጠበቅ ህይወታቸውን ለመንፈሳዊ ተግባር የሰጡትን ላውሬና “ካ ሉሪንግ” ፍራንኮ ለተባሉ ብጽእት ካቴኪስት የቅድስና ማዕረግ እንዲሰጣቸው የሚያስችል ሂደት በይፋ ጀምራለች።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የሎሬና “ካ ሉሪንግ” ፍራንኮን የቅድስና ሂደትን ለመጀመር መደበኛ የሆኑ ሂደቶች በፓሲጅ ሃገረስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ማይሎ ሁበርት ቬርጋራ በቅድስት አኔ ባዚሊካ ውስጥ በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ተጀምሯል።

ብጹእነታቸው የፍራንኮን ሰፊ የጽሁፍ ስራዎችን እና ለቤተክርስትያን ያበረከቱትን አስተዋጾ የመመርመር ሃላፊነት ያለው ‘ታሪካዊ ኮሚሽን’ መቋቋሙን አስታውቀዋል።

የአንድን ለቅድስና የታጨ ሰው መሰረታዊ እውነታውን የሚያጠኑት አቶ ኤሪክሰን ጃቪየር በመርሃ ግብሩ ወቅት የፍራንኮን የህይወት ታሪክ በዝርዝር በመግለጽ እና ፍራንኮ እንደ ካቴኪስት የነበራቸውን በጎ ተግባር በማጉላት “ሱፕሌክስ ሊቤሉስ” የተባለ የእጩነት ሰነድ ለብጹእ አቡነ ቬርጋራ አቅርበዋል።

ብጹእ አቡነ ቬርጋራ ለዝግጅት አቀራረቡ ምላሽ ሲሰጡ እንደተናገሩት ለፍራንኮ እንደ አንድ የእግዚአብሔር አገልጋይ እውቅና የመስጠቱን አስፈላጊነት በማጉላት፥ ለቅድስና እና ለቀኖናዊነት ጥረቶች ያላቸውን ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ገልፀዋል።

በ 2003 ዓ.ም. በ75 ዓመታቸ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ፍሊፒናዊቷ ፍራንኮ፣ “ካ ሉሪንግ” በመባል በብዙዎች ዘንድ የሚታወሱ ሲሆን፥ ይህም በማህበረሰባቸው እና በቤተክርስቲያኒቷ ውስጥ ያላቸውን ስር የሰደደ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳይ ነው ተብሏል።

ሰኔ 27 ቀን 1928 ዓ.ም. በፍሊፒንስ ሃገር፣ ሃጎኖይ ክልል፣ ታጊግ ከተማ ውስጥ መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ካላቸው ቤተሰብ የተወለዱት ፍራንኮ ከስምንት እህትማማቾች መካከል የመጀመሪያዋ ነበሩ። ቤተሰባቸው ለጸሎት ያላቸው ቁርጠኝነት ለፍራንኮ ጠንካራ መንፈሳዊ መሰረት የጣለ ሲሆን፥ ይህም በወጣትነት ዘመናቸው የቅድስት ማርያም የሌጌዎን ደናግላን ማህበር እንዲቀላቀሉ እና ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ያላቸውን ታማኝነት እንዲያጠናክሩ አድርጓቸዋል።

መንፈሳዊ ጉዞዋቸው በብዙ ሽልማቶች የታጀበ እንደነበር እና ከነዚህም ውስጥ የካልካታ እማሆይ ቴሬዛ ሽልማትን በ 1994 ዓ.ም. ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንዲሁም በ1982 ዓ.ም. ጳጳሳዊ ሽልማትን በመውሰድ ከፍተኛ አድናቆትን አግኝተዋል።

ፍራንኮ በ 1960 ዎቹ ውስጥ ከፊሊፒንስ አየር ኃይል የኦፕሬተር ሠራተኝነት ወደ የሙሉ ጊዜ ካቴኪስትነት በመሸጋገር ለእምነታቸው እና ለማህበረሰቡ ያላቸውንን ቁርጠኝነት የበለጠ አሳይተዋል። በተለይም በማኒላ ሃገረስብከት ውስጥ ቅዱስ ቁርባንን ለምዕመናን የመስጠት ስልጣን ከተሰጣቸው የመጀመሪያዎቹ ምዕመናን መካከል አንዷ ነበሩ።

ፍራንኮ ከሚታወቁበት በርካታ ነገሮች ውስጥ ለተቸገሩት የማያወላውል አገልግሎት በመስጠት እንዲሁም ቀላል የሆነ የህይወት ዘይቤ፣ ነገር ግን ጥልቅ በሆነ መንፈሳዊ ህይወታቸው ይታወቃሉ።
 

27 August 2024, 17:01