የሪሚኒ ስብሰባ የሪሚኒ ስብሰባ  

የሪሚኒ ስብሰባ ክርስቲያኖች በሚያስፈልጓቸው ጉዳዮች ላይ እንዲወያዩ የሚጋብዝ መሆኑ ተገለጸ

በሰሜን ጣሊያን ሪሚኒ ከተማ ከ400 በላይ ተሳታፊዎች የተገኙበት 45ኛው የሕዝቦች የወዳጅነት ስብሰባ ክርስቲያኖች በሕይወታቸው አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እንዲወያዩ የሚጋብዝ መሆኑ ተገልጿል። የዘንድሮው ስብሰባ “የሚያስፈልገንን ነገር ካልሆነ ሌላ ምን እንፈልጋለን?” በሚለው መሪ ሃሳብ መጀመሩ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሪሚኒ ከነሐሴ 14-19/2016 ዓ. ም. ለሚካሄደው 45ኛው የሕዝቦች የኅብረት እና የነጻነት ዓመታዊ ጉባኤ ያስተላለፉት መልዕክት መሪ እንደሚሆን ተነግሯል። “የሚያስፈልገንን ነገር ካልሆነ ሌላ ምን እንፈልጋለን?” የሚለው መሪ ሃሳብም ከታዋቂው አሜሪካዊ ደራሲ ኮርማክ ማካርቲ ሐረግ የተወሰደ እንደሆነ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለስብሰባው ተካፋዮች በላኩት መልዕክት፥ የማይቻል በሚመስል የሰላም ፈተና ውስጥ ተስፋን ሳይቆርጡ ይልቁንም በወንድማማችነት መንፈስ አዲስ ዓለምን ለመገንባት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።


“የሰላም መገኘት” የሚለው ማክሰኞ ነሐሴ 14/2016 ዓ. ም. የተከፈተው 45ኛው የሕዝቦች የወዳጅነት ጉባኤ ዋና ርዕሥ ሲሆን፥ የሪሚኒ ስብሰባ ፋውንዴሽን ፕሬዚዳንት ቤርናርድ ሾልስ ከተናገሩ በኋላ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል።

በቫቲካን ድረ-ገጽ በኩል በስርጭት ላይ የሚገኘው ይህ ጉባኤ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ሲሆን፥ ዝግጅቱ የጉባኤው ተሳታፊዎች የወቅቱ ባሕል ሊያስወግደው በሚፈልጋቸው የተስፋ ዕይታ፣ የሰው ልጅ ዕጣ ፈንታ እና የስቃይ ስሜት ላይ ጥያቄዎችን በማቅረብ የሚወያዩበት እንደሆነ ታውቋል።

ቅድስት ሀገር እና ማኅበራዊ እኩልነት
በመጀመሪያው የጉባኤው ቀን በቅድስት ሀገር የአንድነት እና የነጻነት ንቅናቄ መሪ የሆኑት ሁሳም አቡ ሲኒ የቀረበው ትዕይንት የኢየሩሳሌም ተግዳሮት በሚል ርዕሥ በኤሪክ-ኢማኑኤል ሽሚት ተጽፎ በኦቴሎ ሴንቺ የተተወነ እና “በቅድስት ከተማ ጎዳናዎች ላይ ሰላምን ስለመፈልግ የሚናገር በመሆኑ የበርካቶችን ትኩረትን መስቡ ተንግሯል።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ብራንኮ ሚላኖቪች እና የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት የነበሩት ጆሴ ማኑኤል ባሮሶ፥ ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ በተለያዩ አገራት በኢኮኖሚው ሥርዓቶች ምክንያት እየተፈጠረ ስላለው የእኩልነት አለመመጣጠን ላይ ተወያይተዋል።

ዝግጅቱ ከጣሊያን የሥነ-አእምሮ ሐኪም እና የአእምሮ ጤና ተሃድሶ ባለሞያ ፍራንኮ ባዛሊያ ልምድ አንፃር በአእምሮ ሕመም ላይ ትኩረት በማድረግ በመንግሥት ተቋማት እና በግል የውሃ ንግዶች ላይ ያደረጉትን ውይይት ያካትታል።

ሰፊ ዝግጅት ነው
የስብሰባው መርሃ ግብር በጠቅላላው 140 የውይይት ርዕሦች ያሉት፣ ከጣሊያን እና ከዓለም አቀፍ መድረኮች የተወጣጡ 450 ተናጋሪዎችን ያካተተ፣ ከእነዚህም መካከል አንድ መቶ ተናጋሪዎች ከውጭ አገር የተጋበዙ መሆናቸው የተነገረ ሲሆን በ7 ቋንቋዎች ለ 200 ሰዓታት በቀጥታ እንደሚሰራጭ ታውቋል።

በዘንድሮ ጉባኤ ላይ 3,000 የሚሆኑ በጎ ፈቃደኛ አገልግሎታቸው ያበረከቱት ሲሆን ከእነዚህ መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች የሆኑ እንደሆኑ ተገልጿል። ከበጎ ፈቃደኞቹ መካከል ከፍተኛ ውክልና ያላቸው ከስዊዘርላንድ፣ ከስፔንና ከፖርቱጋል ከብራዚል እና ከአርሜኒያ የመጡ ወጣቶች እንደሚገኙበት ታውቋል።

በጣሊያን የፋሽስት መንግሥት ውድቀት እና ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ የዝነኛው የጣሊያን መሪ እና የክርስቲያን ዴሞክራቲክ ፓርቲ መሥራች የነበረ የአልቺዴ ዴ ጋስፔሪ የሕይወት ታሪክ እና ሥራዎቹን ጨምሮ 16 ኤግዚቢሽኖች እንደተዘጋጁ ታውቋል።

ሌላው ኤግዚቢሽን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1914 ዓ. ም. በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የተካሄደውን የገና በዓል ወቅት ጦርነት የሚያሳይ እና በቅድስት ሀገር የደብረ ታቦር እና የጌቴሴማኒ ቤተ መቅደስ ግንባታን የሚያሳይ ኤግዚቢሽንም ቀርቧል። አንዳንድ ኤግዚቢሽኖችም በተዘዋዋሪ መንገድ ከመጭው መስከረም ወር ጀምሮ በተለያዩ የጣሊያን ከተሞች እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።

“ለዓለማችን ግዴለሽነት እራሳችንን አሳልፈን መስጠት የለብንም” ያሉት እና የሪሚኒ ስብሰባ ፋውንዴሽን ፕሬዚዳንት አቶ ሾልስ ከጉባኤው የመግለጫ ክፍል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ “ይህ ስብሰባ እጅግ አስገራሚ እና አሳዛኝ ዓለም አቀፋዊ ክስተቶችን ጨምሮ ታላቅ የቴክኖሎጂ እና የኢኮኖሚ ለውጦች በሚታዩበት፣ የማይገመቱ እና እርግጠኛ ያልሆኑ ሁኔታዎች እና በርካታ ግጭቶች በተከሰቱበት ታሪካዊ ወቅት ላይ የሚካሄድ መሆኑን አስረድተው፥ “በዚህ አስቸጋሪ ወቅት እንኳ ቢሆን የሰላም ተዋናዮች እንድንሆን የሚያስችለንን ነገር በኅብረት ለማወቅ እንፈልጋለን ብለው፥ በግዴለሽነት እና በሽንፈት መሸሸግ የለብንም” ብለዋል።

የሪሚኒ ስብሰባ ፋውንዴሽን ፕሬዝዳንት አቶ ሾልስ እንደተናገሩት፥ የዝግጅቱ ዋና ዓላማ “በዓለም ላይ በብዙ መልኩ ለወደፊቱ ብዙ ቦታ የማይሰጥ በሚመስለው ዓለም ውስጥ ምን ያህል መልካም ነገር እንዳለ ማወቅ ነው” ብለዋል።

“የዘንድሮ ስብሰባ መሪ ሃሳብ፥ ወደ ተወሰነ ደረጃ ላይ እንድንወጣ የሚጋብዝ፣ ጠቃሚ እና ጉልህ የሆነ ነገር እንዳለው እንድንናገር የሚጋብዝ፥ ይህም በሁሉም ሰው ዘንድ የሚቻሉ ታላላቅ ለውጦችን እንድንጋፈጥ፥ በኢኮኖሚ፣ በትምህርት ቤቶች፣ በፋብሪካዎች እና በፖለቲካ ጉዳዮች ሳይሸነፉ በግንባር ቀደምነት ለመገኘት ያስችለናል” ብለዋል።

 

21 August 2024, 15:52