ፈልግ

ጥቃት ተካሂዶባቸው ለስደት የተዳረጉ የያዚዲ ጎሳ አባላት ጥቃት ተካሂዶባቸው ለስደት የተዳረጉ የያዚዲ ጎሳ አባላት  

ብጹዕ ካርዲናል ሳኮ፥ የመካከለኛው ምሥራቅ ሕዝቦች ዛሬም በፍርሃት እና በስቃይ ውስጥ እንደሚገኙ ገለጹ

በባግዳድ የከለዳውያን ፓትርያርክ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ ራፋኤል ሳኮ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2014 በኢራቅ ከደረሰው አደጋ በኋላም መካከለኛው ምሥራቅ በስቃይ ውስጥ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ብጹዕነታቸው የእስላማዊ መንግሥት ታጣቂ ኃይል “አይ ኤስ ኤስ” ኢራቅን የተቆጣጠረበት 10ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የክርስትና፣ የሙስሊም እና የአይሁድ መሪዎች በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ ያለው ጦርነት የሚያቀጣጥለውን አክራሪነት እና ጥላቻ በመቃወም ድምጻቸውን እንዲያሰሙ ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ኢራቅ እስላማዊ መንግሥት እየተባለ የሚጠራው ቡድን በያዚዲ የዘር ማጥፋት ወንጀል የፈጸመበት 10ኛ ዓመት ስታከብር፥ የክርስትና እምነት ተከታዮች ከኢራቅ መሰደዳቸውንም በማስታወስ የባግዳድ ከተማ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ሉዊስ ራፋኤል ሳኮ የክርስቲያን፣ የሙስሊም እና የአይሁድ መሪዎች በአንድነት እንዲቆሙ አሳስበዋል።

የከለዳውያን ፓትርያርክ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ ራፋኤል ሳኮ መታሰቢያ ዕለቱን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት፥ “የክርስቲያን፣ የሙስሊም እና የአይሁድ መሪዎች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ማሰማት አለባቸው” ብለዋል።


መሣሪያ ታጣቂዎች በያዚዲ ጎሳ ላይ በፈጸሙት የዘር ማጥፋት ክርስቲያኖች ለስደት ተዳርገዋል
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2014 ዓ. ም. ነሐሴ መጀመሪያ ላይ እራሱን የኢራቅ እና የሶሪያ እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራው ቡድን በሁለቱ አገራት ውስጥ በሚገኙ አናሳ ክርስቲያኖች ላይ የዘር ጭፍጨፋ ዘመቻ መክፈቱ ይታወሳል።

የ “አይኤስ” ታጣቂዎች በመጀመሪያ የያዚዲ መሐል አገር ሲንጃርን አቋርጠው ወንዶችን በመግደል ሴቶችን እና ሕፃናትን አፍነው በባርነት ከወሰዱ በኋላ ቤትና ንግድ ቤቶችን በማውደም በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን መጉዳታቸው ይታወሳል።

በዚህ የጥቃት ዘመቻ ከ3,000 በላይ የያዚዲ ወንዶች፣ ሴቶች እና ህጻናት ሲገደሉ ቢያንስ 6,800 ተጨማሪ ሰዎች በአብዛኛው ሴቶች እና ህጻናት ታፍነዋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በነሐሴ 6/2014 ዓ. ም. ምሽት የኢራቅ ክርስቲያኖች ላይ በእስላማዊ መንግሥት ታጣቂዎች የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ 120,000 ሰዎች ወደ ሞሱል እና የነነዌ ሜዳ ለመሰደድ ተገድደዋል።

በቅድስት ሀገር የሚኖሩ ሰዎች በፍርሃት እና በተስፋ መቁረጥ ላይ ይገኛሉ
ከአሥር ዓመታት በኋላ “በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ ሕዝቦች ዛሬም ቢሆን በፍርሃት እና በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ይኖራሉ” ሲሉ የተናፈሩት ብጹዕ ፓትርያርክ ሳኮ፥ “እነዚህ ሕዝቦች ጦርነቱ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰባት በቅድስት አገር ውስጥ እንደሚኖሩ ጠቁመዋል።

የሺህዎችን ሕይወት እየቀጠፈ ያለውን ግጭት፣ ቤትን እና መሠረተ ልማቶችን እያወደመ ያለውን ግጭት ለማስቆም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አንድ ነገር እስካላደረገ ድረስ በክልሉ ያሉ ሕዝቦች በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚቀጥሉ አስጠንቅቀው፥ እያንዳንዱ ሰው ጦርነትን እንደሚቃወሚ ቢገልጽም ነገር ግን እራሱን የጦር መሣሪያ እንደሚያስታጥቅ ገልጸዋል።

በጦርነት ሁሉም ሰው ተሸናፊ ነው!
የከለዳውያን ፓትርያርክ በገለጻቸው፥ “ዛሬ ከመቼውም ጊዜ በላይ አሳዛኝ ሁኔታዎች እንዳይደገሙ ካለፈው ትምህርት መማር ይገባል፤ በጦርነት ሁሉም ወገን ተሸናፊ ይሆናል” በማለት አስረድተዋል። “ክፉውን በመልካም በማሸነፍ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት መስራት አለብን” ብለው፥ በውይይት እና በመግባባት ጦርነት በማስወገድ፣ የሰዎችን መብት በማክበር፣ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እና የዓለም አቀፍ ሕግን ማክበር ይገባል” በማለት አጽንዖት ሰጥተዋል።

“ሰዎች በፍርሃት እና በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ወድቀዋል” ያሉት ብጹዕ ፓትርያርክ ሉዊስ ራፋኤል ሳኮ፥ “እግዚአብሔር የፈጠረን በመከራ ወድቀን እንድንሞት ሳይሆን በሰላም፣ በፍቅርና በደስታ አብረን እንድንኖር ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

“የክርስትና፣ የሙስሊም እና የአይሁድ መሪዎች አንድ እንዲሆኑ ይገባል!”
የክርስትና፣ የሙስሊም እና የአይሁድ እምነት መሪዎች በበኩላቸው ኃይላቸውን በማስተባበር ጦርነቶችን በማነሳሳት ጥላቻን እና ጽንፈኝነትን የሚቀሰቅሱትን መዋጋት አለባቸው” ብለዋል።

ፓትርያርክ ሳኮ መልዕክታቸውን ሲያጠቃልሉ፥ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2025 ዓ. ም. በሚከበረ የኢዮቤልዩ በዓል ተስፋን እንዲመሰክሩ ጥሪ አቅርበዋል።በማከልም መስጊዶች እና አብያተ ክርስቲያናት ለሰላም ጸሎት ልዩ ዝግጅት እንዲያደርጉ የክርስትና እና የእስልምና እምነቶች ተከታዮችን ጋብዘዋል።

 

12 August 2024, 15:14