2020.09.22 Eutanasia assistenza vita 2020.09.22 Eutanasia assistenza vita 

የስኮትላንድ ፓርላማ በአዲሱ በህክምና ባለሙያ እገዛ ህይወት የማቋረጥ ህግ ላይ እየተወያየ እንደሆነ ተነገረ

በስኮትላንድ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት መጨረሻ ደረጃ ለደረሱ ሕሙማን እና በአእምሮ ብቁ ለሆኑ አዋቂዎች ሞትን የሚያፋጥን ህክምና ሕጋዊ ለማድረግ የሚያስችል ለስኮትላንዱ ሆሊሩድ ፓርላማ የቀረበውን አዲሱን ህግ እንደሚቃወሙ ተነገረ።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የስኮትላንድ ፓርላማ በስኮትላንድ የታገዘ ሞትን ህጋዊ ለማድረግ የሚያስችለውን በአዲሱ አወዛጋቢ ህግ ላይ እየመከረ ይገኛል።

ይህ “መጨረሻ ደረጃ ላይ የሚገኙ ህሙማን ሞት የሚያፋጥን ህክምና ህግ (ስኮትላንድ)” የተሰኘ ስያሜ የተሰጠው ረቂቅ ህግ የስኮትላንድ ፓርላማ አባል በሆኑት የሊበራል ፓርቲ አቀንቃኝ ሊያም ማክአርተር ተዘጋጅቶ በዚህ ዓመት መጋቢት ወር ላይ እንደታተመ ተገልጿል።

ረቂቅ ህጉ በስኮትላንዱ ሆሊሩድ ፓርላማ ተቀባይነት ካገኘ፣ ስኮትላንድ የመጀመሪያዋ የዩናይትድ ኪንግደም ሀገር ትሆናለች ተብሏል። (መጨረሻ ደረጃ የደረሰ ተብሎ አንድ ታካሚ የሚገመተው በህይወት ለመቆየት የሚችለው ስድስት ወር ወይም ከዚያ በታች እንደሆነ ነው)

በህጉ ዙሪያ በድህረ-ገጽ የተደረገ ህዝባዊ ውይይት
በማህበራዊ ድህረ-ገጽ በተዘጋጀ የዌቢናር ውይይት እንደተመላከተው በረቂቅ ህጉ መሰረት ታካሚዎች ሕይወታቸውን ለማጥፋት የሕክምና ዕርዳታ ሊጠይቁ የሚችሉት የመጨረሻ ደረጃ ሕመም ካለባቸው እና ውሳኔውን በሁለት ዶክተሮች ከተረጋገጠ ብቻ እንድሆነ ለማወቅ ተችሏል። በተጨማሪም፣ ታካሚው እድሜው 16 እና ከዚያ በላይ የሆነ፣ ቢያንስ ለ12 ወራት በስኮትላንድ የኖረ መሆኑ ከተረጋገጠ ሞትን የሚያፋጥነው መድሃኒት ሊሰጠው እንደሚችል ተነግሯል።

በድህረ-ገጽ የተደረገው ክርክር በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ የስኮትላንድ ፓርላማ የጤና ኮሚቴ በጉዳዩ ላይ የህዝብ አመለካከቶችን ለመፈተሽ ነሀሴ 10 ቀን 2016 ዓ.ም. የሚያበቃ የዌቢናር ምክክር ማስጀመሩን ተከትሎ ነው።

የሕጉ ደጋፊዎች ታግዞ መሞትን ሕጋዊ ማድረግ መከራን እንደሚያቃልል በማንሳት ይከራከራሉ። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ የስኮትላንድ ቤተ ክርስቲያን እና የስኮትላንድ መስጊዶች ማኅበርን ጨምሮ ህጉን የሚቃወሙ አካላት በበኩላቸው አንዳንድ የመጨረሻ ደረጃ የደረሱ ታማሚዎች ሕይወታቸውን ያለጊዜው እንዲያጠፉ ግፊት እየተደረገባቸው እንደሆነ ሊሰማቸው ይችላል ብለው ይጨነቃሉ።

የካቶሊክ ብጹአን ጳጳሳት “ለመግደል ሳይሆን ለመንከባከብ ተጠርተዋል” ማለታቸው
የስኮትላንድ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት በመጋቢት ወር ባወጡት ጠንከር ያለ ሃዋሪያዊ ደብዳቤ “ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እንድንገድል መፍቀዱ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች እና ከአእምሮ ጤና ጋር የሚታገሉትን ጨምሮ በጣም ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰባችን አባላትን ሁል ጊዜ አደጋ ላይ በሚጥል ወደ አደገኛ ሁኔታ ይወስደናል” ብለዋል።

“ለመግደል ሳይሆን ለመንከባከብ ነው የተጠራነው” በሚል ርዕስ የቀረበው ይህ ደብዳቤ፣ መላው ካቶሊኮች የስኮትላንድ ፓርላማ አባላትን እንዲያነጋግሩ በመጋበዝ፥ የማስታገሻ ህክምናን ለማሻሻል በትብብር እንዲሰሩ እና የታገዘ ሞትን ህጋዊ ለማድረግ የቀረበውን አደገኛ ሀሳብ ውድቅ እንዲያደርጉ ያሳሰቡ ሲሆን፥ “ህጉ የሕይወትን ዋጋ የሚቀንስ እና በጣም ተጋላጭ በሆኑ ሰዎች ላይ ያለጊዜው ህይወታቸውን እንዲያጠፉ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል” ብለዋል።

ሁለት የቀድሞ ረቂቅ ህጎች ውድቅ መደረጋቸው
የስኮትላንድ ፓርላማ ጉዳዩን ሲመረምር ይህ ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን፣ እ.አ.አ. በ2010 ዓ.ም. የስኮትላንድ የፓርላማ አባላት በአቶ ማርጎ ማክዶናልድ የቀረበውን ሞትን የማፋጠን ህግን በ85 ለ16 በሆነ ድምፅ ውድቅ አድርገውታል። ሌላኛው በረዳት ራስን ማጥፋት ረቂቅ ህግ እ.አ.አ. በ2015 ዓ.ም. ቀርቦ በ82 የተቃውሞ ድምፅ እና በ36 የድጋፍ ድምጽ ውድቅ ተደርጓል።

የስኮትላንድ መንግስት ጉዳዩ የግለሰብ የህሊና ፍርድ ጉዳይ በመሆኑ ሚኒስትሮች እና የስኮትላንድ ብሄራዊ ፓርቲ የፓርላማ አባላት እንዴት እንደሚመርጡ መመሪያ ልንሰጣቸው አንችልም ያለ ሲሆን፥ ተቀዳሚ ሚኒስትር ሁምዛ የሱፍ አዋጁን በመቃወም ድምጽ ሊሰጡ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

በርከት ያሉ አገሮች የታገዘ ሞትን ሕጋዊ አድርገዋል። ከእነዚህም ውስጥ ስዊዘርላንድ፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ስፔን፣ ኮሎምቢያ እና በአሜሪካ ውስጥ የሚገኙ 11 ግዛቶች “በሐኪም እርዳታ መሞት” የሚቻሉባቸው ሃገራት በመባል ይታወቃሉ።
 

14 August 2024, 14:50