የነሐሴ 5/2016 ዓ.ም የ17ኛው እለተ ሰንበት ንባባትና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የነሐሴ 5/2016 ዓ.ም የ17ኛው እለተ ሰንበት ንባባትና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ  

የነሐሴ 5/2016 ዓ.ም የ17ኛው እለተ ሰንበት ንባባትና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

"ካለን ከጥቂቱም፣ ምንም ከሌላቸው ሰዎች ጋር መካፈልን አንዘንጋ”!

የእለቱ ንባባት

1.      2ነገስት 4፡42-44

2.     መዝሙር 144

3.     ኤፊሶን 4፡1-6

4.    ዮሐንስ 6፡1-15

 

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ኢየሱስ አምስት ሺሕ ሕዝብ መገበ

ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ጥብርያዶስ የተባለውን የገሊላ ባሕር ተሻግሮ ራቅ ወዳለው የባሕሩ ዳርቻ ሄደ። ብዙ ሰዎችም በሽተኞችን በመፈወስ ያደረጋቸውን ታምራዊ ምልክቶች ስላዩ ተከተሉት። ከዚያም ኢየሱስ ወደ ተራራ ወጥቶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ። የአይሁድ የፋሲካ በዓልም ተቃርቦ ነበር።

ኢየሱስም ቀና ብሎ ሲመለከት፣ ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ ሲመጣ አየ፤ ፊልጶስንም፣ “እነዚህ ሰዎች እንዲበሉ እንጀራ ከየት እንግዛ?” አለው። ይህን የጠየቀው ሊፈትነው እንጂ ራሱ ሊያደርግ ያሰበውን ያውቅ ነበር። ፊልጶስም፣ “እያንዳንዱ ሰው ትንሽ ትንሽ እንዲቃመስ ለማድረግ፣ የሁለት መቶ ዲናር እንጀራ እንኳ አይበቃም” ሲል መለሰ።

ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፣ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስም፣ እንዲህ አለ፤ “አምስት ትንንሽ የገብስ እንጀራና ሁለት ትንንሽ ዓሣ የያዘ አንድ ልጅ እዚህ አለ፤ ይህ ግን ለዚህ ሁሉ ሕዝብ እንዴት ይዳረሳል?”

ኢየሱስም፣ “ሰዎቹ እንዲቀመጡ አድርጉ” አለ። በዚያ ቦታ ብዙ ሣር ነበረ፤ አምስት ሺሕ ያህል ወንዶችም ተቀመጡ። ኢየሱስ አምስቱን እንጀራ አንሥቶ አመሰገነ፤ ለተቀመጡትም የሚፈልጉትን ያህል ዐደለ፤ ዓሣውንም እንዲሁ። ሁሉም በልተው ከጠገቡ በኋላ፣ ደቀ መዛሙርቱን፣ “ከተረፈው ቍርስራሽ ምንም እንዳይባክን ሰብስቡ” አላቸው። እነርሱም፣ ከተበላው አምስት የገብስ እንጀራ የተረፈውን ቍርስራሽ ሰብስበው ዐሥራ ሁለት መሶብ ሞሉ።

ሰዎቹም ኢየሱስ ያደረገውን ታምራዊ ምልክት ካዩ በኋላ፣ “ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ በርግጥ ይህ ነው” አሉ። ኢየሱስም ሰዎቹ መጥተው በግድ ሊያነግሡት እንዳሰቡ ዐውቆ እንደ ገና ብቻውን ወደ ተራራ ገለል አለ።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው የእሑድ ዕለት መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ወቅት ከዮሐ. 6:1-15 ተወስዶ የተነበበው የወንጌል ክፍል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱን ሊሰሙት የመጡ አምስት ሺህ ያህል ሰዎችን በጥቂት ዳቦ እና ዓሣዎች ብቻ መመገብ  መቻሉን ይተርክልናል። ይህን ተዓምር ስንሰማ እጅግ እንገረማለን። ኢየሱስ ይህን ተዓምር የሰራው ዳቦን እና ዓሣን እራሱ አዘጋጅቶ ሳይሆን ደቀ መዛሙርቱ ያመጡለትን በመውሰድ ነው። ከደቀ መዛሙርቱ መካከል አንዱ፣ አምስት ዳቦ እና ሁለት ዓሣዎችን የያዘ አንድ ልጅ መኖሩን ይረዳል። ነገር ግን አምስት ዳቦ እና ሁለት ዓሣ አምስት ሺህ ሰዎችን በበቂ ሁኔታ ሊመግብ አይችልም። ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በዚህ ጥቂት ምግብ በሥፍራው የነበሩትን በሙሉ በበቂው ሁኔታ መመገብ እንደሚችል ያውቅ ነበር።

አምስት ዳቦ እና ሁለት ዓሣዎች ይዞ በተገኘው ልጅ ቦታ ራሳችንን እናስቀምጥ። ደቀ መዛሙርቱ ይህ ልጅ የያዛቸውን አምስት ዳቦ እና ሁለት ዓሣ በሥፍራው ከነበሩ አምስት ሺህ ሰዎች ጋር እንዲካፈል በማለት ጠየቁት። ጥያቄያቸው አግባብነት ያለው ሊመስለን ይችላል። ነገር ግን ለራሱ ብሎ ያመጣውን ትንሽ ስንቅ ከሌሎች ጋር እንዲካፈል መጠየቅ ለምን አስፈለገ? ልጁ የያዘው ምግብ በሥፍራው ለነበሩ በርካታ ሰዎች እንደማይበቃ እየታወቀ ከእጁ መውሰድ ለምን አስፈለገ? በሰብዓዊ አስተሳሰብ ብንወስደው ይህ ተግባር ተገቢ አይደለም። እንደ እግዚአብሔር ፍላጎት ግን ትክክል ነው። ማንም ሳያስገድደው በግል ፍላጎቱ በእጁ የያዘውን ስንቅ በስጦታ መልክ ላቀረበው ልጅ ምስጋና ይግባውና ኢየሱስም በዚህ ስጦታ አማካይነት በሥፍራው የነበሩ በርካታ ሰዎችን አንድ በአንድ ሊመግብ ችሏል። ይህ ለእኛ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው። ያለንን ጥቂት ነገር ይዘን ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ስንቀርብ እርሱ ብዙ ሊያደርግልን እንደሚችል ያረጋግጥልናል። በመሆኑም ‘ወደ ኢየሱስ ዘንድ ምን ይዤ ልቅረብ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ያስፈልጋል። ኢየሱስ ክርስቶስ በጸሎት የምንጠይቀውን ነገር እጅግ ርብዝቶ ሊሰጠን ይችላል። ለሌሎች የምናበረክተውን የቸርነት ሥራ፣ በችግር እና በመከራ ወቅት የእርሱን ምሕረት ስንለምን መልስ ሊሆነን ይችላል። ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ይዘን በምንቀርበው ትንሽ ነገር እርሱ ተዓምራትን ሊያደርግ ይችላል። በነጻ ፍላጎት ተነሳስተን በምናቀርብለት ትናንሽ ነገሮች በኩል እግዚአብሔር ተዓምራትን ማድረግ ይፈልጋል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎች፣ ከአብርሐም እና ከቅድስት ድንግል ማርያም ጀምሮ እስከ ቸሩ ልጅ ድረስ የተጠቀሱት ታሪኮች የበታችነትን እና የልግስናን ምስጢር ጉልህ ያደርጉልናል። ይህ ልግስና እኛ ከምናውቀው እና ከለመድነው ልግስና ፍጹም የተለየ ነው። እኛ ባለን ነገር ላይ የበለጠ መጨመርን እንፈልጋለን። ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ካለን ቀንሰን ለሌላቸው እንድንሰጥ ይጠይቀናል። ያገኘው ነገር ጥቂት ቢሆን እንኳ በማባዛት ለሌላቸው መስጠትን ይፈልጋል። እኛም ያለንን ነገር ከሌላቸው ሰዎች ጋር ስንካፈል ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ደስ ይለዋል። በዮሐ. 6:11 ፣ በማቴ. 14:19 ፣ በማር. 6:41 ፣ በሉቃ. 9:16 ኢየሱስ ክርስቶስ አምስት ሺህ ሰዎችን በጥቂት ዳቦ እና ዓሣ እንደመገበ በሚገልጽ ታሪክ ውስጥ ‘ማባዛት’ የሚል ቃል አለተጻፈም። ነገር ግን ‘መቁረስ’ ፣ ‘መስጠት’ እና ‘ማደል’ የሚሉ ቃላት ተጸፍው እናገኛቸዋለን። የእግዚአብሔር እውነተኛ ተዓምር ዳቦን እና ዓሣን ከሌሎች ሰዎች ጋር በመካፈል የሚገኝ ደስታ እንጂ በማባዛት አለመሆኑን ኢየሱስ ተናግሯል። በመሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን ያለንን ከሌሎች ጋር ለመካፈል እንሞክር።

ዛሬም ቢሆን በማኅበረሰባችን መካከል ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ከሌለ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ያለው ቁሳዊ ምርት ችግሮችን ሊያስወግድ አይችልም። ይህን በምንልበት ጊዜ በተለይም የበርካታ ሕጻናት ሕይወት እየቀጠፈ ያለው ረሃብ በቅድሚያ የሚጠቀስ ነው። በዓለማችን ውስጥ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ፣ ቁጥራቸው ወደ ሰባት ሺህ የሚጠጉ ሕጻናት በተመጣጣኝ ምግብ እጥረት በየቀኑ እንደሚሞቱ ይነገራል። ይህ ችግር ጎልቶ በሚታይበት ባሁኑ ወቅት ያለንን ነገር ከሌሎች ጋር መጋራት እንዳለብን ኢየሱስ ክርስቶስ ይጋብዘናል። ያለን ሃብት እና እውቀት ትንሽ ቢሆንም ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ በማቅረብ ከወንድሞቻችን እና ከእህቶቻችን ጋር መጋራት ይኖርብናል። ከሌሎች ጋር በመጋራት የምናጣው ነገር የለም። ይህን ካደረግን ባለን ላይ እግዚአብሔር አብዝቶ ይሰጠናል። ‘ያለን አይበቃም’ ብሎ ከማሰብ ይልቅ የፍቅርን፣ የቸርነትን እና ሌሎችን የማገልገል አስፈላጊነት መረዳት ያስፈልጋል።

የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም ራሷን ዝግጁ አድርጋ የተገኘች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ እኛም ለእግዚአብሔር ጥሪ ልባችንን ከፍተን ሌሎችን ማገልገል የምንችልበትን ጸጋ እንድናገኝ ትርዳን"።

 

 

 

10 August 2024, 17:28