በጎረጎሳዊያኑ 2025 ዓ.ም. የሚከበረው የኢዮቤልዩ ክብረ በዓልን አስመልክቶ ለሁለት ቀናት የቆየ የስልጠና መርሃ ግብር በህንድ ተካሄደ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ከነሃሴ 13 እስከ 14 ቀን 2016 ዓ.ም. በጃላንድሃር ክልል፣ ፑንጃብ ከተማ በሚገኘው በአዲሱ የጂያኖ-ዳያ ሃዋሪያዊ ማዕከል የተካሄደው የኢዮቤልዩ የስልጠና መርሃ ግብር የህንድ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ፣ በህንድ ጳጳሳዊ ተልእኮ ድርጅቶች እና በኮሙኒዮ የህትመት ሚዲያ መካከል በተደረገ ትብብር የተዘጋጀ ነበር።
በህንድ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ምክትል ዋና ጸሃፊ በሆኑት በአባ እስጢፋኖስ አላታራና የብሄራዊ አመቻች ቡድን የተዘጋጀው ይህ ፕሮግራም ከየሀገረ ስብከቱ የተመረጡ ተጠሪዎች መጪው ዓመት ለሚከበረው ኢዩቤልዩ ክብረ በዓል የሚያስፈልጉትን እውቀት እና ስልቶችን እንዲያዳብሩ ተብሎ የተዘጋጀ መርሃ ግብር እንደሆነ ተገልጿል።
ስልጠናው የኢዮቤልዩ መንፈሳዊ ጠቀሜታን ከዕቅድ ቴክኒኮች እና የግንኙነት ስልቶች ጋር በማዋሃድ የዳሰሰ መሆኑን የህንድ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የትብብር እና የግንኙነት መድረክ የሆነው ‘ካቶሊክ ኮኔክት’ ዘግቧል።
ዓመቱ የትምህርት እና የጸሎት ዓመት እንደሚሆን በማስተዋወቅ፣የኢዮቤልዩ አስፈላጊነትን በሚገልጹ እና ከተለያዩ ሀገረ ስብከት የተውጣጡ ውጤታማ አሠራሮችን እርስ በርስ እንዲካፈሉ የተበረታቱበት ክፍለ ጊዜዎች የነበሩት መርሃ ግብር እንደነበረም ተጠቁሟል።
በሁለት ቀናቱ መርሃ ግብር ላይ ተሳታፊዎቹ፡ በህንድ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ቅድመ ሰነድ፣ በዓሉን አስመልክተው በየቁምስናዎች ለሚደረጉ አምልኮዎች የሚሆኑ መሪ ቃሎች እና ለ2025ቱ ኢዮቤልዩ የሚዘጋጅ የቀን መቁጠሪያን አስመልክቶ ተጨማሪ ውይይቶች የተደረጉ ሲሆን፥ ለዝግጅቱ የሚረዱ ግብአቶች ቤተመፃህፍት እና መርጃ መሳሪያም እንደሚዘጋጅ ተገልጿል።
የቫሳይ ሀገረ ስብከት ካህን የሆኑት አባ ሮበርት ጆሴፍ “መርሃ ግብሩ ለ2025ቱ ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል የሚጠቅሙ ግብአቶችን እንድናገኝ ረድቶናል” በማለት ስለዝግጅቱ የተናገሩ ሲሆን፥ ከእሳቸው በተጨማሪም ከሲምላ-ቻንዲጋር ሀገረ ስብከት የመጡት አቶ ሳሜር ላክራ በበኩላቸው እንደዚህ ዓይነት መርሃ ግብሮች የሚዘጋጁት ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የተደራሽነት ጥረት የተገኙ እንደሆነም አንስተዋል።
የስልጠናውን ዝግጅት በአስተባባሪነት የመሩት የሰሜን ክልል ካቶሊካዊት ጽ/ቤት ምክትል ዋና ፀሃፊ የሆኑት አባ አንቶኒ ቱሩቲል ሲሆኑ፥ ዝግጅቱ የተጠናቀቀው የጃላንድሃር ሀገረ ስብከት ሐዋሪያዊ አስተዳዳሪ የሆኑት ብጹእ አቡነ አግኔሎ ግራሲያስ ስኬታማ የኢዮቤልዩ ክብረ በዓልን ለማረጋገጥ የሀገረ ስብከት ተጠሪዎችን ወሳኝ ሚና በማስታወስ ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር ተጠናቋል።