ዩዲ ኢካፑትራ በጃካርታ ኢንዶኔዥያ ውስጥ ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ትርኢት ከሚያቀርቡ 101 ልጆች ጋር በልምምድ ላይ ዩዲ ኢካፑትራ በጃካርታ ኢንዶኔዥያ ውስጥ ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ትርኢት ከሚያቀርቡ 101 ልጆች ጋር በልምምድ ላይ 

በጃካርታ 101 ህፃናት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን በደመቀ ሁኔታ ለመቀበል ዝግጅት እያደረጉ መሆኑ ተነገረ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ወደ ኢንዶኔዥያ፣ ጃካርታ የሚያደርጉትን ሃዋሪያዊ ጉዞ ተከትሎ 101 የሚሆኑ ህጻናት ለብጹእነታቸው በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካቴድራል ደማቅ አቀባበል ለማድረግ ከአንድ ወር በላይ የተለያዩ ዝማሬዎችን ሲለማመዱ እንደነበር ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እነዚህ ህፃናት ኡርሱላ ጃካርታ፣ ማሪያ ጃካርታ፣ ቴሬሲያ ጃካርታ፣ እና ስትራዳ ቫን ሊዝ ከሚባሉ ከአራት የተለያዩ ትምህርት ቤቶች፥ እንዲሁም ከሁለት የወጣት ድርጅቶች ከሆኑት የቅዱስ ኤጊዲዮ ማህበረሰብ እና ከቪታ ዱልሴዶ የህጻናት ማሳደጊያ የተውጣጡ እንደሆነ ተብራርቷል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በኢንዶኔዥያ በሚያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው በሁለተኛው ቀን ማለትም ነሃሴ 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ከጳጳሳት፣ ካህናቶች፣ ዲያቆናት፣ ቅዱሳን ሰዎች፣ ከዘርዓ ክህነት ተማሪዎች እና ካቴኪስቶች ጋር በቅድስት ድንግል ማርያም ካቴድራል ይገናኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ጋብሪኤል ፋውንትለሮይ ሃዲሳፑርቶ የሚባለው የ10 ዓመት የማሪያ ጃካርታ ት/ቤት ተማሪ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን በአካል ስለሚያገኛቸው በጣም እንደተደሰተ የተናገረ ሲሆን፥ “እኔ እሳቸውን ያየሁት በቴሌቪዥን ላይ ብቻ ነው፥ አሁን ግን ከእሳቸው ጋር በአካል ስለምገናኝ ደስተኛ ነኝ” ብሏል።

ሌላኛዋ አሌክሳ ጉናዋን የምታባለው ከኡርሱላ ት/ቤት የመጣችው የ 11 ዓመት ዕድሜ ያላት የቡድኑ ሙዚቀኛ ስትሆን፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን በሚቀበሉበት ወቅት የእሷ ድርሻ የሙዚቃ መሳሪያ መጫወት እንደሆነ ገልፃ፥ “በሚቀጥሉት 10 እና 20 ዓመታት ውስጥ ዳግመኛ በአካል እንደማገኛቸው ተስፋ አደርጋለሁ፤ በኢንዶኔዥያ ቆይታቸውም ከልብ እንደሚደሰቱ እተማመናለሁ” ብላለች።

አሌክሳ ጉናዋን በማከልም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን “አጠቃላይ ጃካርታን እና ኢንዶኔዥያን እንዲዞሩ እና የህዝቡን ከልብ የመነጨ አቀባበል እንዲያዩ እና እንዲሰማቸው አበረታታቸዋለው” ብላለች።

በመርሃግብሩ መሰረት ህፃናቱ ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ለአራት ደቂቃዎች ያህል ዝግጅታቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን፥ በመቀጠልም ብጹእነታቸው ከካህናት እና ከስኮላስ ኦከርንቴስ ወጣቶች ጋር ከተገናኙ በኋላ ከህፃናቱን ቡድን ጋር ለመገናኘት እድሉ ሊኖራቸው ይችላል ተብሏል።

ዩዲ ኢካፑትራ የተባለ የመዘምራን አሰልጣኝ እና ሙዚቀኛ የህፃናቱ ትዕይንት አዘጋጅ ሲሆን፥ ልጆቹ በዘንድሮው የዓለም የህጻናት ቀን ታዋቂ የሆነውን ‘ሲያሞ ኖይ’ የተባለውን ሙዚቃ እንደሚጫወቱ ገልፆ፥ “ሙዚቃው በጣሊያንኛ የተሰራ ስለሆነ ልጆቹ በትክክል እንዴት ማስታወስ እንዳለባቸው እና ማንበብ እንዳለባቸው መማር ነበረባቸው” ብሏል።

አቶ ኢካፑትራ ለአቀባበል በተዘጋጀው ሙዚቃ ውስጥ የብሄር ብሄረሰቦችን ሙዚቃዎች እንዳካተቱ በመግለጽ፥ አንዳንድ ህጻናት በዝግጅቱ ወቅት ሀገር በቀል መሳሪያዎችን እንደሚጠቀሙ ጠቁሞ፥ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ “የአቀባበል ሙዚቃን በመስራቴ ዕድለኛ እና ደስተኛ ነኝ” ካለ በኋላ፥ አክሎም “ይህን መዝሙር ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንዲሁም ለልጆቹ ስል ለማሳተም እቅድ አለኝ” ብሏል።

ህፃናቱን ለዚህ ዝግጅት ለማብቃት ስምንት የሙዚቃ መምህራን እና 21 የኮሚቴ አባላት እንደተሳተፉበትም ለማወቅ ተችሏል።
 

03 September 2024, 16:04