በሉክሰምበርግ ስለምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ምን ያህል እናውቃለን?
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ከሚያደርጉባቸው ሁለት አገራት መካከል የመጀመሪያዋ ሉክሰምበርግ ስትሆን በዚህ ጽሑፋችን በአገሪቱ ስለምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ያገኘነውን ጠቅለል ያለ ታሪክ እናስቃኛችኋለን።
ዛሬ ሉክሰምበርግ ተብሎ ወደምትጠራ አገር የክርስትና እምነት ለመጀመሪያ ጊዜ የግባው በ 4ኛው ክፍለ ዘመን ሲሆን መነሻውም ዛሬ ጀርመን ተብላ በምትጠራ አገር ውስጥ ከምትገኝ የትሪየር ከተማ ነው። የቅዱስ በነዲክቶስ ገዳም መሥራች፣ የአንግሎ ሳክሶን ሚስዮናዊ እና የኔዘርላንድ፣ የቤልጂየም እና የሉክሰምበርግ ባልደረባ ተብሎ በሚጠራው በቅዱስ ዊሊብሮርድ (እ.አ.አ ከ 658-739) በተደረገ ከፍተኛ የስብከተ ወንጌል ጥረት እንደነበር ሲነግር፥ በመካከለኛው ዘመን የቅዱስ በኔዲክቶስ፣ የቅዱስ ፍራንችስኮስ እና የቅዱስ ዶሜኒኮስ ማኅበር ገዳማውያን በኋላም ወደ ንጉሣዊ አገዛዝ በተቀየረች አገር ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ሚና መጫወቱ ይነገራል።
ረጅም ጊዜ የቆየ የካቶሊክ ባሕል
በመካከለኛው ዘመን የሉክሰምበርግ ሕዝብ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጠንካራ አክብሮት እንደ ነበረው ይነገራል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1666 በተከሰተው ታላቅ መቅሰፍት ምእመናን በሉክሰምበር ሊምፐርትስበርግ አውራጃ ውስጥ ተአምር አድርጓል ተብሎ ወደሚታመነው የእመቤታችን የእንጨት ሐውልት ፊት ቀርበው ድውያን እንዲፈወሱ በማለት ጸሎት ማቅረብ ጀመሩ።
በኋላም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሐውልት በከተማዋ ወደሚገኘው ካቴድራል ተዛወረ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የአገሪቱ ቤተ ክርስቲያናት ከብርሃነ ትንሳኤው በኋላ በሚውሉ ሦስተኛ እና አምስተኛ እሑዶች መካከል “ኦክታቭ” በመባል የሚታወቀውን ዓመታዊ ንግደት መጀመሩ ይታወሳ። በዚህ መሠረት ዛሬም በሉክሰምበርግ ውስጥ ከፍተኛ ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓት የሚፈጸም ሲሆን ለሁለት ሳምንታት በሚቆየው በዓል ላይ በየዓመቱ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የክልሉ ምዕመናን ይሳተፋሉ።
እስከ 19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ሉክሰምበርግ የራሷ የጳጳሳት ጉባኤ አልነበራትም። ለረጅም ጊዜ በሰሜን በሚገኘው የቤልጂየም-ሊጌ ሀገረ ስብከት እና በደቡብ በሚገኘው የጀርመን-ትሪየር ሀገረ ስብከት ስር ነበረች። ከዚያም የፈረንሳይ አብዮት ተከትሎ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1801 ዓ. ም. በፈረንሳይ የሜትዝ ሀገረ ስብከት አካል ሆነች። ከዚያም በ 1823 ሰፊው የግዛቲቱ ክፍል ናሙር ከተሰኘ የቤልጂየም ሀገረ ስብከት ጋር ተጠቃለለ።
በመጨረሻም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1840 ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጎርጎርዮስ 16ኛ የሉክሰምበርግ ሐዋርያዊ አስተዳደር ሲመሠርቱ፥ ከዚያም በ 1870 ወደ ሀገረ ስብከትነት ከፍ ካለ በኋለ በ 1988 ዓ. ም. ሊቀ ጳጳስ ያለው ሀገረ ስብከ ሆነ።
የርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት ጉብኝቶች
ቅድስት መንበር እንደ ጎርጎሮሳውያን ከ 1891 ዓ. ም በሉክሰምበርግ ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት ካቋቋመችበት ጊዜ ጀምሮ ከንጉሣዊ ቤተሰብ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ስታደር ቆይታ በኋላም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1955 የሐዋርያዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤት ተቋቋመ።
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በለውጥ ላይ በሚገኝ ማኅበረሰብ ውስጥ ለሚከሰቱ አዳዲስ ፈተናዎች ምላሽ ለመስጠት በሚል ዓላማ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከግንቦት 11-21/1985 ዓ. ም. ሆላንድን፣ ሉክሰምበርግን እና ቤልጂየምን በጎበኙበት አጋጣሚ ታላቁን ንጉሣዊ ቤተሰብ እንደጎበኙ ይታወሳል።
ሉክሰምበርግ ጥንታዊ የክርስትና ባሕል ያላት ሀገር ስትሆን በዚያ የምትገኝ ካቶሊካዊ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር የንጉሣዊ ቤተሰብ ማንነት ዋና አካል እና በተለይም ሁለቱን የዓለም ጦርነቶች ጨምሮ በታሪኳ በጣም አስቸጋሪ ጊዜያትን ባሳለፈች ሉክሰምበርግ ውስጥ ተጠቃሽ ሆና እንደኖረች ይታወቃል።
በሉክሰምበርግ ውስጥ የካቶሊክ እምነት ዛሬም የብዙሃኑ ሃይማኖት ሲሆን፥ በአሁኑ ጊዜ ከአገሪቱ 672,000 ሕዝብ መካከል 67% በብፁዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆሌሪች የሚመሩ ካቶሊክ ምዕመናን ሲሆኑ 5% የሚሆኑት ፕሮቴስታንቶች እንደሆኑ ይነገራል።
ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው የዓለማዊነት መንፈስ አጠቃላይ ሃይማኖታዊ ባሕል እያሽቆለቆለ በመምጣቱ፣ ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተጽዕኖ ፈጣሪነት ቀንሶ ይታያል። በተጨማሪም ሉክሰምበርግ ከጊዜ ወደ ጊዜ የብዙ-ብሄር እና የብዙ ሃይማኖታዊ ማኅበረሰቦች መኖሪያ በመሆኗ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች፣ ትንሽ የአይሁድ እምነት ተከታዮች እና በባልካን አገራት ከተካደው ጦርነት በኋላ የእስልምና እምነት ተከታዮች ቁጥር እንደጨመረ እንዲሁም የቡዳ እና የሂንዱ እምነቶች ተከታዮችም መኖራቸው ታውቋል።