ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በጃካርታ በሚገኘው የኢስቲቅላል መስጊድ ውስጥ በተካሄደ የሃይማኖት ተቋማት ውይይት ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በጃካርታ በሚገኘው የኢስቲቅላል መስጊድ ውስጥ በተካሄደ የሃይማኖት ተቋማት ውይይት ላይ   (Vatican Media)

ሊቀ ጳጳስ ኮመንሶሊ 'እስያ የቤተክርስቲያን የወደፊት ዕጣ ፋንታ ናት' አሉ

በአውስትራሊያ የሜልቦርን ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ፒተር አንድሪው ኮመንሶሊ ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት እስያ የቤተ ክርስቲያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ናት ሲሉ አውስትራላዊያን ቅዱስ አባታችን ወደ አካባቢው እያደረጉት ያለውን ሐዋርያዊ ጉዞ በቅርበት እየተከታተሉት እንደሆነ ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ 45ኛውን የውጪ ሃገራት ሐዋርያዊ ጉዞአቸውን በኢንዶኔዥያ እያደረጉ ባለበት ወቅት በሃገሪቷ ርዕሰ መዲና ጃካርታ በተካሄደው የሃይማኖቶች ተቋማት ውይይት ዝግጅት ላይ በአውስትራሊያ የሜልቦርን ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ፒተር ኮመንሶሊ ከቫቲካን የዜና ወኪል ሊንዳ ቦርዶኒ ጋር ቆይታ አድርገው ነበር።

ቅዱስ አባታችን ወደ እስያ እና ኦሽንያ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉዞ በጀመረ በሦስተኛው ቀን፣ ነሃሴ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕለተ ሐሙስ ላይ በደቡብ ምስራቅ እስያ ትልቁ በሆነው በኢስቲቅላል መስጊድ በመገኘት ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፥ ለብጹእነታቸው ታላቁ ኢማም ዶክተር ናሳሩዲን ኡመር አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ቅዱስ አባታችን የኢስቲቅላል መስጊድን ከቅድስት ማርያም ካቴድራል ጋር የሚያገናኘው እና “የወዳጅነት ዋሻ” ተብሎ የሚታወቀውን የመሬት ውስጥ የእግረኛ መንገድ ከዶክተር ናሳሩዲን ጋር በመሆን አብረው ጎብኝተዋል።

ከዚህም ባለፈ በሁሉም ሃይማኖታዊ ትውፊቶች ውስጥ ባሉ እሴቶች “የጥቃት እና ግዴለሽነት ባህልን ለማሸነፍ” እንዲሁም እርቅ እና ሰላምን ለማጎልበት ውጤታማ በሆነ መንገድ በጋራ እንዲራመዱ አጽንኦት ሰጥቶ ለሚያበረታታው የ ‘ኢስቲቅላል 2024’ የጋራ ሰነድ ላይ ፈርመዋል።

ሊቀ ጳጳስ ኮመንሶሊ በቃለ ምልልሳቸው ወቅት በተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች መካከል ያለውን የወንድማማችነት መንፈስ አስፈላጊነትን አጉልተው የገለጹ ሲሆን፥ ቃለ ምልልሱ እንደሚከተለው ይቀርባል፦

ጥያቄ፦ በኢስቲቅላል መስጊድ የሚደረገውን የሃይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት ተከታትለዋል፥ ይህ ክስተት ለዚህ ክልል እና ለዓለም ምን ያህል አስፈላጊ ነው ይላሉ?

መልስ፦ በግልጽ እንደሚታወቀው፣ በታሪክ ውስጥ ወደ ሁከትና ብጥብጥ የተስፋፉ የእምነት ማህበረሰቦች መካከል ችግሮች ነበሩ። ነገር ግን ባለፉት 15 ወይም ከዚያ በላይ ዓመታት ውስጥ ጉልህ በሆነ መልኩ ተሠርቶበታል። እ.አ.አ. በ2012 ዓ.ም. በኢንዶኔዢያዋ ከተማ በባሊ በተፈፀመ የቦምብ ጥቃት ምክንያት አውስትራሊያ የተወሰነ ልምድ ነበራት፥ እንደሚታወቀው ጥቃቱ የተፈጸመው በአስከፊ ሽብርተኝነት ምክንያት ነው። ነገር ግን እኔ እንደተረዳሁት፣ ዛሬ እዚህ ኢንዶኔዥያ ውስጥ በክርስቲያኖች እና በሙስሊሞች መካከል ያለው ግንኙነት ጤናማ ነው፥ ከዚህም ባለፈ አሁን ባለንበት በዚህ መስጊድ እና በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ካቴድራል መካከል ስላለው ድልድይ መስማት አስደሳች ነገር ነው። ስለዚህ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ትላንት የተናገሩት እርስ በርስ በወንድማማችነት መተሳሰርን የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ።

ጥያቄ፡- ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ከዚህ መስጊድ ታላቅ ኢማም ጋር የጋራ መግለጫ እየተፈራረሙ ነው። መስጊዱ በደቡብ ምስራቅ እስያ ውስጥ ካሉት ትልቁ መስጊድ ነው። ይህ መልዕክት ለዓለም እንደሚደርስ ተስፋ ያደርጋሉ? ይህስ በራሱ ምን ያህል ጠቃሚ ነው ይላሉ?

መልስ፦ በጣም አስፈላጊ ነው ብዬ አስባለሁ፥ ከጥቂት ዓመታት በፊት ተመሳሳይ ነገር በአቡ ዳቢ ተከስቶ ነበር፥ ይህ ትልቅ ምልክት ነው። ነገር ግን ምልክቶች ወደ እውነታዎች መሸጋገር አለባቸው፥ እናም ይህ ክስተት እነዚያን ድልድዮች ለመገንባት የሚያስችል መንገድ እንደሆነ ተስፋ እናደርጋለን።

በርግጥ በሌሎች ቦታዎችም አስፈላጊ ነው ብዬ አስባለሁ፥ እዚህ በእስያ ውስጥ እየሆነ ያለውን ነገር ለእኛም በርካታ የሙስሊም እና የአይሁድ ማህበረሰብ ባለበት በአውስትራሊያ ውስጥ ላለነውም ጭምር አስፈላጊ ነገር ነው። ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ በሁለቱ መካከል ያለው ግንኙነት በጣም የተወሳሰበ እና አስቸጋሪ ነው፥ ስለዚህ እንደዚህ ያሉ መንገዶችን መፈለግ እድሎችን መክፈት ሊሆን ይችላል።

ጥያቄ፦ የኢንዶኔዥያ የዲሞክራሲ እና የመቻቻል ሞዴል የሰላም እና የመተሳሰብ እንዲሁም አብሮ የመኖር ምሳሌ ሊሆን ይችላል ብለው ያስባሉ?

መልስ፦ እዚህ ያለችው ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን ትናንት '100 በመቶ ኢንዶኔዥያ፣ 100 በመቶ ካቶሊክ' የሚል መፈክር ሲያሰሙ ሰምቼ ነበር። እናም ይሄ ጥሩ ነገር ነው ብዬ አስባለሁ፥ ኢንዶኔዥያ ውስጥ ብዝሃነት በሰፊው ይታያል፥ በእያንዳንዱ ደሴት... የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ልማዶች፣ ወዘተ ያሏቸው ነባር ሕዝቦች አሉ። ስለዚህ ኢንዶኔዢያ አንድ ልትሆን የምትችልባቸው መንገዶች መኖራቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ከዚያም በደቡብ ምሥራቅ እስያ ዙሪያ ላሉ ሌሎች አገሮች ምሳሌ የሚሆን ነገር ይሆናል።

ጥያቄ፦ አውስትራላዊያን ይህን መንገድ እየተከተሉት ያሉት በጣም ቅርብ ስለሆነ ነው ብለው ያምናሉ?

መልስ፦ አዎ፣ እውነት ነው። እኛ ራሳችንን በዚህ ዘመን የምናስበው ከአሮጌው አውሮፓ ወይም ሰሜን አሜሪካ [አህጉራት] ይልቅ ወደ እስያ የበለጠ እንደምንቀርብ ነው። እስያ የወደፊት ተስፋችን ናት። በአውስትራሊያ ውስጥ በአጥቢያ ቤተክርስትያን ውስጥ እንኳን ሳይቀር፣ ለምሳሌ በሜልቦርን ያሉ ጉባኤዎቻችን ውስጥ የእስያውያን ፊቶች እየበዙ መጥተዋል። በርካታ ፊሊፒኖች፣ ኢንዶኔዥያውያን፣ ቬትናሞች፣ ኮሪያውያን እና ህንዶች አሉ። ይሄ በአውስትራሊያ ውስጥ ስላለው የቤተ ክርስቲያን ሁኔታ አንድ ነገር ያሳያል። እናም እነዚህ የካቶሊክ እምነት ባህላዊ መገለጫዎች ወደ ፊት ምን ሊያመጡ እንደሚችሉ እየተረዳን ነው።

 

06 September 2024, 18:57