የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ  

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን የ2017 ዓ/ም የዘመን መለወጫ በዓልን በማስመልከት መልዕክት አስተላለፉ

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ የ2017 ዓ/ም የዘመን መለወጫ በዓልን በማስመልከት ለመላው ምዕመናን ያስተላለፉት መልእክት እንደሚከተለው ይቀርባል፦

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡
‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንት ዛሬም ለዘለዓለምም ያው ነው›› ዕብ 13፡8

በክርስቶስ የተወደዳችሁ ብፁዓን ጳጳሳት
ክብራን ካህናት፣ ገዳማውያንና /ውያት
መላው ምምዕመናንና የሀገራችን ሕዝቦች
በመላ ዓለም የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና
ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወገኖች

እንኳን ለ2017 ዓ/ም የዘመን መለወጫ በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት በራሴ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ስም መልካም ምኞቴን አስተላልፋለሁ፡፡

የጊዜ ባለቤት የሆነው ፈጣሪያችን መድኃኒታችን እነሆ ጠብቆ ለአዲሱ ዓመት አድርሶናል፡፡ ጋሻ ከለላ ሆኖ አበርትቶናል በሃዘናችን አጽናንቶናል የጀመርነውን አስጨርሶናል፡፡ አዳዲስ ሐሳቦችን እንድናፈልቅ አድርጎናል፡፡ ብዙ ዕቅዶችን እንድናወጣ ረድቶናል፡፡ ለዚህ ሁሉ ለልዑል እግዚአብሔር ክብርና ምስጋና ይድረሰው፡፡ ኅሊናችንን እንድንመረምር፤ ጥረታችንን እንድንቀበል፤ ንሰሓም እንድንገባ ስለረዳን እናመሰግነዋለን፡፡ ከስሕተታችን እንድንማር ስላደረገንም እንወድሰዋለን ባለፈውና በሚመጣው መካከልም ያለውን ጊዜ ለእግዚአብሔር እናቀርባለን፡፡

የሰው ልጅ ከሌሎችም ፍጥረታት በተለየ መልኩ ስለ ጊዜ ያስባል፤ በጊዜ ውስጥ ይመላለሳል ያለፈውን ዘመን ያስታውሳል፡፡ የሚመጣውንም በተስፋ ይመለከታል፡፡ የሰው ልጅ ያለ ትውስታ አይኖርም፡፡ ትውስታ የሰው ልጅ ክፍል መሆኑን ከእግዚአብሔር ቃል እንማራለን፡፡ ለምሳሌ ህዝበ እሥራኤል ከግብፅ ባርነት የወጣበትን ጊዜ እንዲያስታውስ ተነግሮታል፡፡ ሌላ ቀርቶ ያሳለፉትን መራራ ነገር እንዳያስታውሱ ተነግሯቸው ነበር፡፡ እግዚአብሔር ያንን ዘመን እንዳያስታውሱ የነገራቸው ለበቀል እንዲነሳሱ ብሎ አልነበረም፡፡ ይልቁንም የደረሰባቸውን እንዳይደገም ለማስተማርም ጭምር ነበር፡፡ እናንተ መከራ ደርሶባችሁ ነበር፤ ነገር ግን እንዲህ ዓይነት መከራ በሌሎች ላይ እንዳትፈጽሙ ለማለት ነበር ያስተማራቸው፡፡ በሌላ አነጋገር ያለፈውን እርሱት አላላቸውም፡፡ ያለፈውን ጊዜ በእግዚአብሔር ፍቅር ፈውሱት ነው ያላቸው፡፡

እኛም አዲስ ዘመንን ስናከብር ያለፈውን በእግዚአብሔር መፈወስ እንችል ይሆን? ባለፈው መልካሙን ይዘን በመቀጠል መልካም ያልነበረውን ደግሞ እንዴት ይሆን መፈወስ የምንችለው? እግዚአብሔር ህዝቡ የደረሰበትን እያስታወሰ እንዲፈወስ የእግዚእብሔርን ማዳን እንዲያከብር ያስተማረው ዓለምን የፈጠረ አምላክ ከባርነትም ነጻ የሚያወጣ አምላክ መሆኑን ለማሳየትም ነበር፡፡

ያለፈውን ማስታወስ ለማመስገን እንደሚጠቅም ሁሉ የሚመጣውንም በክርስቶስ ተስፋ መመልከት የእምነታችን አንቀጽና አምድ ነው፡፡ የተስፋ ምስጢር ከእምነትና ከፍቅር ምስጢር ጋር በደንብ የተሳሰረ ነው፡፡ የረጅምና የአጭር ጊዜ እቅዳችን በመለኮታዊ ፍቅርና ተስፋ በተቃኘ ቁጥር በረከትን ያመጣልናል፡፡ እኛም ዛሬ የምናከብረው በዓል ይህንን ምስጢር እንድንገነዘብ ያደርገናል፡፡ እንደ ግለሰብም ሆነ እንደማህበር ምን ያህል እናስባለን? ዛሬ የምንጀምረውን አዲስ ዓመት በፈሪሃ እግዚአብሔርና በእግዚአብሔር ፍቅር እንድናቅደው ያስፈልጋል፡፡ ያን ጊዜ ‹‹መንግሥትህ ይምጣ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነ እንዲሁም በምድር ይሁን›› የሚለው ፀሎታችን ወደ ተግባር ይቀየራል፡፡

ዘመን፤ ዓመት፤ ወራት፤ ሳምንታት፤ ቀናት፤ ሰዓታት፤ ደቂቃዎች፤ በሙሉ የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው፡፡ የምንፈጥራቸው ሳይሆኑ የምንቀበላቸው በረከቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ስጦታ መሆናቸውን መረዳት ትልቅ ቁም ነገር ነው፡፡ ጊዜን እንዳናባክን ያግዘናል፡፡ እንድንቀሳቀስ፣ እንድንተጋ፣ እንድንለወጥም ያደርገናል፡፡ በሌላ በኩል አላግባብ እንዳንጨነቅም ይረዳናል፡፡ የማንለውጠውን ወይንም ሊለወጥ የማይቻለውን እንለውጣለን ብለን በከንቱ እንዳንደክም ያደርገናል፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተለይም በነቢያት ዘንድ ‹‹የጌታ ቀን›› የሚባል አለ፡፡ ያ ቀን እግዚአብሔር ሕዝቡን የሚባርክበት ዘመን ነው፡፡ ሕዝበ እግዚአብሔር በአምላክ ፀጋ ከጨለማ ወደ ብርሃን፤ ከስቃይ ወደ እረፍት፤ ከባርነት ወደ ነፃነት የሚጓዝበት ሂደት ነው፡፡ ነገር ግን ነብያት ማስጠንቀቂያ ነበራቸው፡፡ ፍትሕ ከጎደለ፤ ደሃ ከተበደለ፤ ፈሪሃ እግዚአብሔር ከጠፋ፤ ፍቅር ከተተወ ያ ቀን የብርሃን ሳይሆን የጨለማ፤ የነፃነት ሳይሆን የባርነት፤ የሰላም ሳይሆን የስቃይ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ የሰላም ዘመን እንዲሆንልን የነቢያትን ምክር እንስማ፡፡ ትንቢታቸውን እንመርምር፤ ራዕያቸውን እናስተውል ነቅተን እንጠብቅ፡፡ ጉዳዩ የሚመጣውን አዲስ ዓመት በቁጥር የማስላት አይደለም፡፡ ጉዳዩ አምላክንና በእርሱ የተፈጠረውን የሰው ልጅ የማፍቀር ጉዳይ ነው፡፡ ጉዳዩ ለፍትሕ የመቆም፤ ለድሃ የማሰብና የመሥራት ጉዳይ ነው፡፡

የአቤልና የቃየል ታሪክ ከእኛ ሕይወት ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው የሩቅ ጊዜ ታሪክ ብቻ ሁኔታ ይመስለን ይሆናል፡፡ ነገር ግን ከጥንት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዘመናችን ያለውን የዓለማችንን ታሪክ ስንመለከት የቃየልና የአቤል ታሪክ ያለማቋረጥ እየተደገመ መሆኑን መረዳት አያስቸግርም፡፡ ስንት ጊዜ የቃየልና የአቤል ታሪክ ይፈፀማል? ከምንኖርበት አካባቢ አንስቶ ቅናትና ተንኮል ሥራውን ይሰራል፤ በሥራችን ተደስተን አምላክን አመስግነን አብረውን ለሚሰሩት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መልካሙን እንመኝ ይሆን? እግዚአብሔርን እናወድስ ይሆን? ተግተው እንዲሠሩ ለህዝቦቻቸው ቁም ነገር እንዲያከናውኑ በሃሳብና በተግባር እንደግፋቸው ይሆን?

የአዲሱ ዓመት በዓል የእግዚአብሔር መንግስት በዓል ነው፤ በአዲሱ ዓመት ለመስቀልና ለትንሣኤ ቦታ መስጠት ማለትም ለለውጥ መዘጋጀትና መፍቀድ ማለት ነው፡፡ ሕይወት ያለው ነገር ይንቀሳቀሳል፣ ይለወጣል፣ ይሻሻላል ወይም ያሽቆለቁላል፡፡ የክርስቶስ ጥሪ ወደ ዕድገት የሚመራ ተባሪነትንና በጎ ምላሽን የሚጠይቅ ጥሪ ነው፡፡ ነገሮች እንዳሉ ይቆዩ ወይንም ይቀጥሉ የሚሉ ሃሳቦች ሊሠራጩ ይችላሉ፤ እንደ ሰው መለወጥን እንፈራ ይሆናል፡፡

ያለፈውን ጊዜ መልካም እንደነበረ ወይንም እንዳልነበረ የምናውቀው በጽሞና በእግዚአብሔር ቃል ብርሃን ስንመረምረው ነው፡፡ በመስቀልና በትንሳኤ ብርሃን ስንገመግመው ነው፡፡ መልካሙን ሐሳብ በንግግርና በተግባር በሰብዓዊ እውቀት ብቻ ልንመረምረው አንችልም፡፡ ስህተት የሆነውንም የሚነግረን የእግዚአብሔር ቃልና የመስቀል ትንሣኤ ምስጢር ነው፡፡ እንደ ሰው እኔ፤ እኛ ሁልጊዜ ትክክል ነን ፤ የሚያጠፉት ሌሎች ናቸው ካልን ቆም ብለን ማሰብ ያስፈልገናል፡፡ የፈሪሳውያን እርሾ ‹‹እኛ ትክክል ነን ክርስቶስ የሚሰብከው የእግዚአብሔር መንግስት ልክ አይደለም›› የሚል ነበር፡፡ ከዚያም አልፎ ፈሪሳውያን የሙሴን ሕግ ይጠቅሱ ነበር፡፡ ሆኖም ክርስቶስን መቀበል አልፈለጉም፡፡ ለእግዚአብሔር ሕግ እንቆረቆራለን እያሉ የእግዚአብሔርን ሕግ ማፍረሱን አልፈሩም፡፡ እኛም ባለፈው ዓመት የተፈታተኑንን ጉዳዮችና ችግሮች ዛሬ በአዲሱ ዓመት መፍታት እንድንችል እግዚአብሔር የመፍትሔውን መንገድ እንዲያሳየን የምንጸልይበትም ጊዜ ነው፡፡

አዲሱ ዓመት የተሰጠን በጎ ነገሮችን እንድናስብና ለጋራ ጥቅም የሚሆኑ ተግባራትን እንድንፈጽም ነውና ለዚህ እንነሳሳ፡፡ አዲሱ ዓመት ለተራቡት፤ ለተጠሙት፤ ለታረዙት፤ ለተፈናቀሉት፣ ለታሰሩት፤ ለታመሙትና ላዘኑት የምንደርስበት ጊዜ ይሁንልን፡፡ በአዲሱ ዓመት ለእግዚአብሔር ክብር፤ ለአገራችን ሰላምና ዕድገት፤ አዳዲስ ነገሮችን እንሥራ፤ የልግስና ዓመትም እንዲሆንልን ወደ እርሱ እንማፀን፡፡

ልዑል እግዚአብሔር አዲሱን ዓመት ይባርክልን !
ሰላሙን ያውርድልን !
ውድ አገራችንን ኢትዮጵያን ይባርክልን !

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ
ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን
 

10 September 2024, 12:25