ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በፖርት ሞርስቢ በሚገኘው ካሪታስ የቴክኒክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያደረጉት ጉብኝት ላይ ገዳማዊያቱ ተገኝተዋል  ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በፖርት ሞርስቢ በሚገኘው ካሪታስ የቴክኒክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያደረጉት ጉብኝት ላይ ገዳማዊያቱ ተገኝተዋል  

ወጣቱ ትውልድ አንድ ቀን የፓፑዋ ኒው ጊኒን ልማት ይመራል ተባለ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከኢንዶኔዥያው የሦስት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት በኋላ ጳጉሜ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. የጉብኝታቸው ሁለተኛ ሃገር ወደ ሆነችው ፓፑዋ ኒው ጊኒ የገቡ ሲሆን፥ ብጹእነታቸው በሃገሪቷ ርዕሰ መዲና በሆነችው ፖርት ሞርስቢ በሚገኘው የካቶሊክ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጋር ከነበራቸው ቆይታ ጎን ለጎን፥ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ያገለገሉት ሲስተር ፍሎሬንቲና ቾ ባደረጉት ቃለ ምልልስ በወጣት ትውልዶች ላይ ያላቸውን እምነት በመግለጽ፥ የሃይማኖት ጉባኤያቸው ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ እና የፓፑዋ ኒው ጊኒ የወደፊት መሪዎችን ለመፍጠር እንደሚጥር ተናግረዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ሲስተር ፍሎሬንቲና ቾ በፓፑዋ ኒው ጊኒ ሚስዮናዊ ሆነው ለ38 ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን፥ ከደቡብ ኮሪያዋ ዋና ከተማ ሴኡል ግዛት ውስጥ ከሚገኘው የሳሌሲያን ቤተሰብ አባል የሆነው ‘የካሪታስ እህቶች’ ማህበር በኦሽንያ አህጉር ውስጥ ወደምትገኘው ወደዚህ ደሴት የመጡት “ትምህርት ቤት ለመገንባት” እንዲሁም “ድሆችንና የተቸገሩትን ለመንከባከብ” እንደሆነ ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጳጉሜ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ሲስተር ፍሎሬንቲና ለበርካታ ዓመታት ባገለገሉበት በፖርት ሞርስቢ ከተማ በሚገኘው የካሪታስ ቴክኒካል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ከሚማሩ ተማሪዎች ጋር የተገናኙ ዕለት ባደረጉት ቃለ ምልልስ አጠቃላይ ስለ ትምህርት ቤቱ ገለፃ የሰጡት ተማሪዎቹ ለቅዱስ አባታችን ባደረጉት የእንኳን ደህና መጡ የደስታ ድምፆች በመታጀብ ነበር።

ሲስተር ፍሎሬንቲና እ.አ.አ. በ1997 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ በፖርት ሞርስቢ በሚገኘው የካሪታስ ትምህርት ቤት በገቡበት ወቅት በአጠቃላይ 144 ተማሪዎች ብቻ እንደነበሩ በማስታወስ፥ አሁን ላይ ግን ትምህርት ቤቱ ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ ኮሌጅ ደረጃ ድረስ ከ1,000 በላይ ተማሪዎችን እያስተናገደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በምስጋና ስሜት “እዚህ አዳዲስ በሚመጡ ታናናሽ እህቶቼ በጣም ደስተኛ ነኝ፥ ኩራትም ይሰማኛል” ያሉት ሲስተሯ፥ ከ30 ዓመታት በላይ በፖርት ሞርስቢ ካገለገሉ በኋላ፣ በ 2008 ዓ.ም. በዌስት ኒው ብሪታንያ ግዛት ሥር ወደምትገኘው ኪምቤ ከተማ መጓዛቸውን አስታውሰው፥ እዚያም 200 ተማሪዎች ያሉት ሌላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲገነባ ትልቅ እገዛ እንዳደረጉ ተናግረዋል።

ሲስተር ፍሎሬንቲና ክርስትና በትምህርት አሰጣጥ ሥርዓት ውስጥ ያለውን ትልቅ ጠቀሜታ ጎላ አድርገው የገለጹ ሲሆን፥ ይህም የቤተሰብን የኑሮ ደረጃ ከፍ ለማድረግ እንደሚረዳ እና በተለይም እንደ ፓፑዋ ኒው ጊኒ ባሉ የወንዶች የበላይነት በሚታይበት ማኅበረሰብ ውስጥ በተለይም ጾታዊና የሕፃናት ትንኮሳዎች ዋነኛ ችግሮች በሆኑበት ብሎም “የሴቶች መከራ በርካታ” በሆነበት አከባቢ ያለው ጠቀሜታ ብዙ ነው ብለዋል።

የሴቶች ችግር ርዕስ ሆኖ የሚቀርበው በዚህኛው ጳጳሳዊ ጉብኝት ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ ጊዜ የሚከሰት ችግር መሆኑም ጠቁመው፥ የቅዱስ አባታችን በፓፑዋ ኒው ጊኒ መገኘት በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን የሴቶች ሁኔታ ለማሻሻል ይረዳል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

እስከዚያው ድረስ እሳቸው እና ሌሎች የጉባኤው አባላት የበለጠ ፍትሃዊ የሆነ ማህበረሰብ እንዲገነባ ልጆችን እና ወጣቶችን በማስተማር ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ በመግለጽ፥ በመጨረሻም “አንድ ቀን ይህቺን ሃገር የሚያለሙት ወጣት ትውልዶች ይሆናሉ፥ ይህ የእኛ ታላቅ ተስፋ እና ራዕይ ነው” በማለት አጠቃለዋል።
 

09 September 2024, 14:30