በጃፓን እየቀነሰ የሚሄደው የወሊድ መጠን እና እየተራዘመ የመጣው የዕድሜ መጠን በጃፓን እየቀነሰ የሚሄደው የወሊድ መጠን እና እየተራዘመ የመጣው የዕድሜ መጠን   (ANSA)

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኢሳኦ ኪኩቺ፥ ጃፓን ውስጥ አረጋውያን መገለል እንደሌለባቸው አስጠነቀቁ

የቶኪዮው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኢሳኦ ኪኩቺ፥ በወጣት እና በአረጋዊያን ትውልዶች መካከል የበለጠ መስተጋብር እንዲኖር ጥሪ በማቅረብ ጃፓን በፍጥነት እያሽቆለቆለ ካለው የወሊድ መጠን እና እርጅና ጋር እየታገለች ያለች አገር በመሆኗ አረጋውያን መገለል የለባቸውም ሲሉ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኢሳኦ ኪኩቺ እሁድ መስከረም 5/2017 ዓ. ም. ባደረጉት ንግግር በትውልዶች መካከል መተሳሰብ እንዲኖር ጥሪ አቅርበው፥ አረጋውያን በኅብረተሰቡ ውስጥ ለሚጫወቱት የማይናቅ ሚና አጽንኦት ሰጥተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዓለም የአያቶች ቀን ያስተላለፉትን መልዕክት በመጥቀስ፥ አረጋውያን ለወጣት ትውልዶች እንደ ሸክም የሚቆጥሩ የኅብረተሰብ አዝማሚያዎችን አስጠንቅቀዋል። አረጋውያን የወጣቶችን የወደፊት ሕይወት ይነጥቃሉ የሚለውን የተሳሳተ እምነት መከላከል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኢሳኦ ኪኩቺ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን በመጥቀስ፥ “ሥራቸው ውጤታማ በማይሆንበት ጊዜ እና ኃይላቸውም እያሽቆለቆለ በሚሄድበት ጊዜ እግዚአብሔር ልጆቹን ፈጽሞ አይተዋቸውም” ማለታቸውን አስታውሰዋል።

የጎርጎሮሳውያኑን የቀን አቆጣጠር የምትከተል ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሐምሌ ወር አራተኛ እሁድን የዓለም የአያቶች እና የአረጋውያን ቀን አድርጋ ማወጇ ይታወሳል። ይሁን እንጂ በጃፓን የምትገኝ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የአረጋውያን ቀንን ከብሔራዊ በዓል ጋር በማስማማት ወደ መስከረም ለማዘዋወር የቅድስት መንበርን ፍቃድ በመጠየቋ መስከረም 5 ቀን በጃፓን የዓለም የአያቶች እና አረጋውያን ቀን ተከብሮ ውሏል።

የጃፓን የእርጅና ቀውስ በዓለም ላይ እጅግ አስከፊ ከሚባሉት ውስጥ አንዱ ሲሆን፥ ከሕዝቧ 30 በመቶው ከ65 ዓመት በላይ እንደሆነ ታውቋል። እየቀነሰ የሚሄደው የወሊድ መጠን ከተራዘመው የሕይወት ዘመን ጋር ተዳምሮ የሥነ-ሕዝብ አወቃቀር መዛባትን ፈጥሮ ባሕላዊ የቤተሰብ መዋቅሮችን አበላሽቷል።

እንደ የቅርብ ጊዜ አኃዛዊ መረጃዎች መሠረት ጃፓን ውስጥ አንዲት ሴት በሕይወት ዘመኗ እንድትወልድ የሚጠበቅባት አማካይ መጠን ባለፈው ዓመት ወደ 1.2 ዝቅ ብሏል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2023 ዓ. ም. ጃፓን 727,277 ልደቶችን ያስመዘገበች ሲሆን፥ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ 5.6 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል። ይህም ከ 1899 ዓ. ም. በኋላ የተመዘገበው ዝቅተኛው ነው ሲል ሚኒስቴሩ ገልጿል።

መረጃው በተጨማሪም በትዳሮች ውስጥ 6 በመቶ ማሽቆልቆል ማሳየቱን እና ባለፈው ዓመት 474,717 ጥንዶች ጋብቻ መፈፅማቸውን አስታውቋል። ባለሥልጣናቱ ይህ በትዳሮች ላይ ያለው ውድቀት ለወሊድ መጠን መውረድ ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳደረገ ጠቅሰዋል።

 

16 September 2024, 17:29