ቫቲካን ውስጥ ያለው  የአትክልት ስፍራ ቫቲካን ውስጥ ያለው የአትክልት ስፍራ  

ነሃሴ 26 እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ለመፍጠር የወሰነበት ቀን የሚከበርበት ነው

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለፍጥረታት እንክብካቤ የዓለም የጸሎት ቀንን ነሃሴ 26 ላይ ባከበረች ወቅት፥ የእስያ ጳጳሳት ጉባኤዎች ፌዴሬሽን የሰብአዊ ልማት ጽህፈት ቤት ፕረዚዳንት የሆኑት ህንዳዊው ጳጳስ ብጹእ አቡነ ኦልዊን ዲ ሲልቫ ስለ አስደናቂ የፍጥረታት ስጦታው እግዚአብሔርን ማመስገን ያለውን አስፈላጊነት ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ለዓለም ፍጥረታት የጸሎት ቀን በየዓመቱ ነሃሴ 26 የሚከበር ሲሆን፥ ምስራቃዊው ቤተክርስትያን ለተፈጥሮ ባለው የበለጸገ ባህል በመነሳሳት ሁለቱንም በዓላት ማለትም እግዚያብሄር ሰማይና ምድርን ለመፍጠር በፍቅር የወሰነበት ቀንን እና ይሄንን ታላቅ የፍጥረት ስጦታን እንዴት እንደምንጠብቅ የምናሰላስልበት ጊዜ ነው ብለዋል።

ይህ የእምነታችን የማዕዘን ድንጋይ ነው ያሉት ብጹእነታቸው፥ እንዲያውም ቅዱሳት መጻሕፍት በታላቁ የፍጥረት ምስጢር እንደሚጀምሩ እና ታላቁ መጽሃፋችንም በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ቁጥር 2 ላይ “ምድርም ባዶ ነበረች፥ አንዳችም አልነበረባትም፥ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ” እንደሚለው፥ ፈጣሪ ሕይወትን የፈጠረው “ቅርጽ ከሌለው ባዶነት” እና ብርሃንና ሕይወት ከሌለበት ድቅድቅ ጨለማ ነው ብለዋል። ፈጣሪ በዚያ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ብርሃን እንዲሆን የወሰነበት ውሳኔ ከአስተሳሰባችን በላይ ለጋስነቱን ያሳያል ያሉት ብጹእነታቸው፥ ከምንወዳቸው ሰዎች እስከ መስክ አበባዎች ድረስ በዙሪያችን ያሉ ነገሮች የሚፈሱት ከዚህ በፍቅር ከተከናወነው የፍጥረት ሥራ ነው ያሉ ሲሆን፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሃዋሪያዊ መልዕክታቸው በሆነው ላውዳቶ ሲ እንደነገሩን “መላው ቁሳዊ ዓለም የእግዚያብሄርን ፍቅር፣ ለእኛ ያለውን ወሰን የሌለው ፍቅር ይናገራል” ማለታቸውን አስታውሰዋል።

ፍጥረት ለብቻው አልተተወም ያሉት ብጹእ አቡነ ኦልዊን፥ እኛ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠርን ሰዎች እንድንጠብቀው ተሹመናል፥ እኛ ጠባቂዎቹ ነን፣ የአትክልት ስፍራውን “እንድንከባከብ እና እንድንጠብቅ” ትእዛዝ ተሰጥቶናል (ዘፍ 2፡15) ብለዋል።

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ “ምድር በእርግጥም የፈጣሪ ስጦታ ናት፣ ውስጣዊ ሥርዓቷን በመንደፍ፣ የፍጥረታቱ ጠባቂዎች እንድንሆን የሚመራን አቅጣጫ ሰጥቶናል” በማለት ገልጸው ነበር ብለዋል።

ብጹእ አቡነ ኦልዊን እንዳሉት የዓለም የፍጥረት ቀንን ስናከብር ራሳችንን መጠየቅ የሚገባን ነገር ቢኖር፥ ፈጣሪ የሰጠንን ሚና እየተገበርን ነው ወይ የሚለውን ነው፥ መልሱ ግልጽ ነው፣ በሚያሳዝን ሁኔታ ‘አይደለም’ የሚለውን ነው የምንመልሰው። የራሴ የትውልድ ከተማ ሙምባይ የእግዚአብሔርን የፍጥረት ስጦታ አለመንከባከብ የሚያስከትለውን መዘዝ የሚያሳይ ጥሩ ምሳሌ ናት ብለዋል።

ሙምባይ በተራሮች እና በባህር መካከል የምትገኝ፣ ወደ 21 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በተጨናነቀ ሁኔታ የሚኖሩባት ትልቅ ከተማ ነች። ተፈጥሮአዊ ማዕበል፣ አውሎ ንፋስ እና ከፍተኛ ሙቀት በየጊዜው ያጠቃታል። ቀደም ባሉት ጊዜያት የሙምባይ ሰዎች እነዚህን ፈተናዎች ተቋቁመዋል። ምንም እንኳን አስቸጋሪ ቢሆንም ለዝናብ እና ለአውሎ ነፋስ መዘጋጀትን እና ከሃይለኛው ሙቀት ራሳቸውን መጠበቅን ተምረዋል በማለት የትውልድ ሃገራቸውን ልምድ አካፍለዋል።

ነገር ግን አሁን የምድራችን የአየር ሁኔታ እየተቀየረ ነው ያሉት ብጹእ አቡነ ኦልዊን፥ ፖሊሲ አውጪዎችም ለጉዳዩ ትኩረት እየሰጡ እንዳልሆነ እና በጥንካሬያቸው ሲጋፈጡ የነበሩት የሙምባይ ህዝቦች የበፊቱ ልምዳቸው ከአሁን በኋላ እንደማያገለግል አክለው፥ ይልቁንም ከፍተኛ ሙቀት እየጨመረ እንደሆነ፥ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በሙምባይ አካባቢ ከ39 እስከ 43 ዲግሪ ያለው ሙቀት ለበርካታ ቀናት ተመዝግበዋል ያሉ ሲሆን፥ የምሽት እና የሌሊት ሰዓታት እንኳን ሳይቀሩ ከባድ እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቁመው፥ ይህም በተለይ ማቀዝቀዣ ማግኘት ለማይችሉ ድሆች በጣም አስቸጋሪ ነው ብለዋል።

በየጊዜው የሚከሰተው ከፍተኛ ንፋስ የቀላቀለው ዝናብ እና በተራራማ አካባቢዎች ያሉ መደበኛ ያልሆኑ ሰፈራዎች መስፋፋት ገዳይ ወደሆነው የመሬት መንሸራተት እያመራ ነው ያሉት ብጹእነታቸው፥ በተመሳሳይ ጊዜ ከባህር ላይ የሚነሱ አውሎ ነፋሶች እና የአውሎ ነፋሶችን ኃይል ለማቀዝቀዝ እና ለመመከት የሚውሉ እፅዋቶች መጥፋት ምክንያት በባህር ዳርቻ ላይ ያሉ ሰዎች መኖሪያ ቤታቸውን ለማጣት የተጋለጡ ሆነዋል ብለዋል።

ለ21 ዓመታት የሙምባይ ከተሞች በሆኑት ጀሪሜሪ እና ዳራቪ ውስጥ በሚገኙ ሁለት የድሆች መንደር ውስጥ ሠርቻለሁ ያሉት ብጹእነታቸው፥ ድሆች እነዚህን ችግሮች የበለጠ እንደሚጎዳቸው እመሰክራለሁ፥ በእነዚህ ሰፈሮች ውስጥ ያሉ ቤተሰቦች የትምህርት፣ የመሠረተ ልማት እና ጥሩ የስራ እድል እጦት ያጋጥሟቸዋል። አየሩ በአደገኛ ሁኔታ በሚሞቅበት ጊዜ በስራ ቦታ መቆየት፣ ወይም አውሎ ንፋስ እና የመሬት መንሸራተት አደጋ በሚፈጠርበት ጊዜ ቤቶችን መቀየር አይችሉም በማለት ድሆች ላይ ስለሚያስከትለው አደጋ አብራርተዋል።

እነዚህን ቤተሰቦች ችግሩን በራሳቸው ጥረት ለመቋቋም ከሚያደርጉት ጥረት ሁሉ በላይ የአየር ንብረት አደጋዎችን እንዲቋቋሙ ማስገደድ ከፍተኛ ደረጃ የሞራል ውድቀት ነው ያሉት ብጹእ አቡነ ኦልዊን ዲ ሲልቫ፥ የሳይንሱ ማህበረሰብ የሰው ልጅ እኩይ ድርጊቶች በአየር ንብረታችን ላይ ለውጦችን እያመጡ እንደሆነ ደጋግመው ያስታውሱናል ካሉ በኋላ፥ ፈጣሪያችን እኛን የፍጥረቱን ጠባቂዎች እንደመሆናችን መጠን እንድናደርግ የሚፈልገው ይሄንን ነው ብዬ ማሰብ አልችልም ብለዋል።

ብጹእነታቸው በመጨረሻም ባስተላለፉት መልዕክት ይህ ዓመታዊ ክብረ በዓል ትልቅ እድል ይሰጠናል፥ እግዚአብሔር ምድራችንን ለመፍጠር ባደረገው ፍቅር የተሞላበት ውሳኔ ላይ የምናሰላስልበት እና የፍጥረት ጠባቂዎች የመሆናችንን ሚና እንዴት እንደምንወጣው የምናስብበት ጊዜ ይህ ነው ካሉ በኋላ፥ ይህ የጸሎት ቀን ለአንድ ወር ያክል የሚከበረው ‘የፍጥረት ወቅት’ የሚጀመርበት ሲሆን፥ ዛሬን እና በነዚህ ጊዜያቶች ሁሉ ፈጣሪን እናመስግን፥ እንዲሁም የተቀደሰውን የፍጥረት ስጦታ ለመንከባከብ በጋራ እንስራ በማለት አጠቃለዋል።
 

02 September 2024, 13:13