ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሲንጋፖር ወጣቶችን ባሳተፈ የሃይማኖቶች የጋራ ውይይት ላይ  ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሲንጋፖር ወጣቶችን ባሳተፈ የሃይማኖቶች የጋራ ውይይት ላይ   (Vatican Media)

በሲንጋፖር የቤተ ክርስቲያን እና የሲቪል መሪዎች በሃይማኖቶች መካከል ውይይትን ለማጠናከር ቃል ገቡ

በሲንጋፖር የምትገኝ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና የሲቪል ማኅበራት መሪዎች በሃይማኖቶች መካከል የሚደረገውን ውይይት እና አንድነት ለማጠናከር ቃል ገብተዋል። ውይይቱ ብዙ ኃይማኖቶች በሚገኝበት ማኅበረሰብ ውስጥ ሰላም እና ትብብርን ለማምጣት ያለውን ጠቀሜታ ገልጸዋል። ባለስልጣናቱ ይህን የገለጹት ዓርብ መስከረም 3/2017 ዓ. ም. በተካሄደው እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተገኙበት የሃይማኖቶች የጋራ ውይይት መድረክ ላይ እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሲንጋፖር ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ዊልያም ጎህ ዓርብ ጠዋት በሲንጋፖር ካቶሊክ መለስተኛ ኮሌጅ ውስጥ ከልዩ ልዩ ሃይማኖቶች የመጡ ወጣቶች ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ ንግግር አድርገዋል።

ካርዲናል ዊልያም አገሪቱ ሃይማኖታዊ አንድነትን ለማስጠበቅ እያደረገች ያለውን ጥረት አስመልክተው ንግግር ያደረጉ ሲሆን፥ በተለያዩ እምነቶች መካከል ጥልቅ ወዳጅነትን ለመፍጠር የምትከተለውንም አካሄድ አብራርተዋል።

“በሲንጋፖር ውስጥ በሃይማኖቶች መካከል የሚደረገው ውይይት አንዱ የሌላውን እምነት ከማክበር እና ከመቻቻል የዘለለ ነው” ብለው፥ ወዳጅነት እና የጋራ መግባባት ለሰላም ወሳኝ መሆናቸውን አፅንዖት ሰጥተዋል።

ካርዲናል ዊልያም በሃይማኖቶች መካከል የሚካሄደውን ዓመታዊ የብርሃነ ልደቱ ወቅት ዝግጅት እና ከተለያዩ ሃይማኖቶች የተውጣጡ ወጣቶችን የሚያሰባስብ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ጨምሮ በርካታ ውጥኖችን ጠቅሷል።

እነዚህ ዝግጅቶች መተማመንን ለመፍጠር እና የማኅበረሰብ ትስስርን ለማጠናከር እንደሚረዱ ገልጸው፥ ሆኖም ግን ፅንፈኝነት አሁንም ስጋት እየፈጠረ መሆኑ በመጥቀስ ችላ ሊባል እንደማይገባ አስጠንቅቀዋል። “በሲንጋፖር የሃይማኖቶችን መስማማት እንደ ዋዛ አንወስደውም” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ዊልያም አክለውም፥ በሃይማኖቶች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ቀጣይ ጥረቶች እንዲደረጉ አሳስበዋል።

የባሕል፣ የማኅበረሰብ እና የወጣቶች ሚኒስትር የሆኑት ኤድዊን ቶንግ፥ የሃይማኖት መሪዎች የሲንጋፖርን ማኅበራዊ ትስስር በመጠበቅ ረገድ የሚጫወቱትን ሚና በመግለጽ እነዚህን ሃሳቦች አስተጋብተዋል።

“የሃይማኖቶች ስምምነት ለሲንጋፖር ህልውና እና የኅብረተሰብ ትስስር መሠረት ነው” ያሉት ሚኒስትር ቶንግ፥ የዘር እና የሃይማኖት አንድነትን የሚደግፉ የመንግሥት ፖሊሲዎችን እና አወቃቀሮችን ጠቁመው፥ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለአገር ግንባታ በተለይም በትምህርት ዘርፍ እና በጤና አጠባበቅ ዙሪያ የምታበረክተውን አስተዋፅዖ አስታውሰዋል።

በተጨማሪም በክርስትና ቤተ እምነቶች እና በሌሎች እምነቶች መካከል ውይይትን የሚያበረታታውን የሲንጋፖር የሃይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት እና አንድነት ማዕከልን በመጥቀስ፥ "የሲንጋፖር ካቶሊክ ምዕመናን ከሌሎች ማኅበረሰቦች ጋር ጠንካራ ግንኙነት አላቸው" ሲሉ ሚኒስትር ቶንግ ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ በማከልም፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሚያደርጉት ቀጣይ የውይይት እና የወንድማማችነት ቅስቀሳ አመስግነው የሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን አስፈላጊነት አውስተዋል። “የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት ማኅበረሰቦቻችን በተለይም ወጣቶቻች አንድ እንዲሆኑ እና የወደፊት ተስፋቸውን እንዲያድሱ ያነሳሳቸዋል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስንጋፖር ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ከአራት አሥርት ዓመታት በፊት ያደረጉትን የመጀመርያውን ጉብኝት እንደሚያስታውስ ተገልጿል።

የሃይማኖቶች የጋራ ውይይቱ ወጣቶች እና የሃይማኖት አባቶች ሰላማዊና ሁሉን አቀፍ ኅብረተሰብ ማስፈን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት የሚደረግበትን መድረክ አዘጋጅቷል።

ካርዲናል ጎህ እና ሚኒስትር ቶንግ የዓለምን ፈተናዎች ለመጋፈጥ ቀጣይነት ያለው ትብብር እና መተማመን አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

 

13 September 2024, 17:28