ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፥ “አንዳንድ ሐዋርያዊ እይታዎች”
በሲኖዶሱ ወቅት የተካሄደው ውይይት የአዳዲስ ሐዋርያዊ ዘዴዎችን አስፈላጊነት አንሥቶአል። እኔም ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹን ጠቅለል ባለ መንገድ ለመጥቀስ እወዳለሁ። የተለያዩ ማኅበረሰቦች የቤተክርስቲያንን አስተምህሮና የአካባቢ ችግሮችንና ፍላጎቶችን የሚያከብሩ ይበልጥ ተጨባጭና ውጤታማ ዕቅዶችን መንደፍ አለባቸው። እኔም እዚህ ላይ ለቤተሰብ የሚሆን ሐዋርያዊ ዕቅድ አቅርቤአለሁ ብዬ ሳልኩራራ፣ በአንዳንድ ዋና ዋና ሐዋርያዊ ተግዳሮቶችን ብቻ ለማብራራት እፈልጋለሁ።
ዛሬ የቤተሰብ ወንጌልን ስለ መስበክ
የሲኖዶሱ አባቶች አበክረው እንደገለጹት፣ በምሥጢረ ተክሊል ጸጋ የተሞሉ ክርሰቲያን ቤተሰቦች በዋናነት የቤተሰብ ሐዋርያዊ ሥራ ዋና ወኪሎች ናቸው። ይህንንም ውክልናቸውን የሚፈጽሙት “በደስታ የተሞላ የቤተሰብ አብያተ ክርስቲያናት ምስክሮች” በመሆን ነው። ስለዚህ፣ “ሰዎች የቤተሰብ ወንጌልን ‘ልብንና ሕይወትን በሚሞላ’ ደስታ ቢቀበሉ መልካም ነው፤ ምክንያቱም በክርስቶስ ‘ከኀጢአት፣ ከትካዜ፣ ከውስጣዊ ባዶነትና ከብቸኝነት ነጻ ወጥተናል’ (ኤቫንጄሊ ጋውዲዩም፣ 1)። በዘሪው ምሳሌ እንደተነገረው (ማቴ. 13፡ 3-9)፣ ዘርን በመዝራት ረገድ እንድንረዳ ተጠርተናል፤ ቀሪው የእግዚአብሔር ሥራ ነው። እንደዚሁም፣ ቤተክርስቲያን ስለቤተሰብ በምታስተምረው ትምህርት የቅራኔ ምልክት ናት”። መንፈሳዊ እረኞቻቸው ብርቱ፣ ጽኑ፣ ዘላቂና የሚያጋጥሙአቸውን ማናኛውንም ዐይነት ፈተናዎች ለመከላከልም የሚያስችል ከፍተኛ የፍቅር ተምሳሌት በመሆናቸው ባለትዳሮች ያመሰግኑአቸዋል። ቤተክርስቲያንም በትህትናና በርኅራኄ ወደ ቤተሰቦች ለመቅረብና “እያንዳንዱን ቤተሰብ ማናቸውንም መሰናክሎች ለመወጣት የሚያስችለውን ከሁሉ የተሻለ መንገድ እንዲፈልግ ለመርዳት ትመኛለች”። በሐዋርያዊ እቅድ ውስጥ ለቤተሰቦች የተለመደውን ተቆርkሪነት ማሳየት በቂ አይደለም። ቤተሰቦች የቤተሰብ ሐዋርያዊ ሥራ ንቁ ወኪሎች የመሆናቸውን ሚና እንዲጫወቱ ለማስቻል “በቤተሰብ ውስጥ ወንጌልን የመስበክና የማስተማር ጥረትን ይጠይቃል”። “ይህ ጥረት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሁሉንም ሰው ተልዕኮአዊ እምነት፣ ማለትም ከሰዎች ተጨባጭ ችግሮች ጋር ግንኙነት የሌለው ንድፈ ሐሳባዊ መልእክትን ብቻ በማወጅ የማይረካ እምነትን መኖር ይጠይቃል”። (ለቤተሰቦች የሚደረግ ሐዋርያዊ እንክብካቤ) “የቤተሰብ ወንጌል ለሰው ልጅ ውስጣዊ ተስፋ፣ ይኸውም ለእያንዳንዱ ሰው ክብርና ለጋራ ስኬት፣ ለአንድነትና ለፍሬያማነት ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን በግልጽ ማሳየት ያስፈልገዋል፡፡ ይህም ሥርዓቶችን ማስቀመጥ ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬ እጅግ ዓለማዊ በሆኑ አገራት ጭምር፣ የሚፈለጉ እሴቶችን ማቅረብንም ያካትታል”።
የሲኖዶሱ አባቶችም “ስብከተ ወንጌል ለገበያ ሥነ አመክንዮ የተጋነነ ዋጋ የሚሰጡ፣ እውነተኛ የቤተሰብ ሕይወትን የሚያደናቅፉና ወደ አድልዎ፣ ድህነት፣ ማግለልና ብጥብጥ የሚመሩ ባህላዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚአዊ ምክንያቶችን ያለ ጥርጥር ማውገዝ እንደሚያስፈልግ አስምረውበታል። ስለሆነም፣ ከኅብረተሰብ መዋቅሮች ጋር ውይይትና ትብብር መፍጠርና እንደ ክርስቲያኖች በባህላዊ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ መስኮች የተሰማሩ ምእመናንን ማበረታታት ያስፈልጋል”። “ለቤተሰቦች ሐዋርያዊ እንክብካቤ ትልቁን አስተዋጽኦ የሚያበረክተው ንዑሳን ማኅበረሰቦች፣ የቤተክርስቲያን እንቅስቃሴዎችና ማኅበራት ተስማምተው የሚኖሩበትና የቤተሰቦች ቤተሰብ የሆነው ቁምስና ነው”። ይህም በተለይ በቤተሰቦች ላይ ካተኮረው ሐዋርያዊ ተደራሽነት በተጓዳኝ፣ “ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ወንድና ሴት መነኮሳት፣ የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን (ካቲኪስቶች) እና ሌሎች የሐዋርያዊ ሥራ ሠራተኞች… በቂ ሕንጸት” እንደሚያስፈልጋቸው አመላካች ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ለተካሄደው ምክክር በተሰጡ ምላሾች ውስጥ ካህናት አገልጋዮች ብዙውን ጊዜ አሁን ቤተሰቦችን የሚያጋጥሙአቸው ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ሥልጠና እንደሚያስፈልጋቸው ግልጽ ሆኖአል፡፡ የምሥራቅ አገራት የባለትዳር ካህናት ሰፊ ትውፊትም በተሞክሮነት ሊወሰድ ይችላል።
የዘርአ ክህነት ተማሪዎች የቤተክርስቲያንን ትምህርት ብቻ ሳይሆን፣ በመተጫጨትና በጋብቻ ዙሪያ ብዙ ሙያዎችን ያካተተ ሰፋ ያለ ሕንጸት ያስፈልጋቸዋል። የሚሰጣቸው ሥልጠና ሁሌም የራሳቸውን ሥነ ልቦናዊና ስሜታዊ ልምድና ተሞክሮ እንዲያስሱ አያስችላቸውም። አንዳንዶች ችግር ካለበት፣ ወላጆች ከሌሉበትና ስሜታዊ መረጋጋት ከማይታይበት ቤተሰብ የሚመጡ ናቸው። ስለዚህ፣ የሕንጸቱ ሂደት ለወደፊት አገልግሎታቸው የሚያስፈልጋቸውን ብስለትና ሥነ ልቦናዊ ሚዛን እንዲቀዳጁ የሚያስችላቸው መሆኑን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው። የቤተሰብ ትስስሮች ጤናማ የሆነ በራስ መተማመንን ለማጎልበት ይረዳሉ። ቤተሰቦች የዘርዐ ክህነት ትምህርት ሂደትና የክህነት ሕይወት አካል ቢሆኑ መልካም ነው፤ ምክንያቱም እነዚህን የቤተሰብ ትስስሮች ለማጠናከርና በእውነታ ላይ የተመሠረቱ እንዲሆኑ ይረዳሉና። በዚያም በወደፊት አገልግሎታቸው በዋናነት ከቤተሰቦች ጋር ስለሚሠሩ፣ ከቤተሰብ ሕይወት ተጨባጭ እውነታዎች ጋር የበለጠ ግንኙነት ይኖራቸዋል። “በክህነት ሕንጸት ውስጥ የምእመናን፣ የቤተ ሰቦችና በተለይም የሴቶች መኖር፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ የልዩ ልዩ መንፈሳዊ ጥሪዎችን ብዝሃነትና ተደጋጋፊነት ለማወቅ ይረዳል”።
የምክክሩ ምላሽም በመምህራንና በአማካሪዎች፣ በማኅበረሰብ ሐኪሞች፣ በማኅበራዊ ኑሮ ሠራተኞች፣ በወጣቶችና በቤተሰብ ጠበቆች በመታገዝ እንዲሁም የስነ ልቦና፣ የስነ ኅብረተሰብና የጋብቻ የምክር አገልግሎት ተሞክሮዎችን በመጠቀም ለቤተሰቦች ሐዋርያዊ አገልግሎት የሚሰጡ የምእመናን መሪዎችን የማሠልጠን አስፈላጊነት አሳይቶአል። በተለይም ተጨባጭ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች መኖር ሐዋርያዊ ዕቅዶችን በቤተሰቦች ተጨባጭ ሁኔታዎችና ፍላጎቶች ላይ የተመሠረቱ እንዲሆኑ ይረዳል። “በተለይ ለሐዋርያዊ ሠራተኞች የታለሙ የትምህርት ዐይነቶችና ፕሮግራሞች የቅድመ ጋብቻ የዝግጅት ፕሮግራምን ከሰፊው የቤተክርስቲያን ሕይወት እንቅስቃሴ ጋር በማቀናጀት ረገድ ድጋፍ ሊሰጡ ይችላሉ”። ጥሩ ሐዋርያዊ ሥልጠና “በተለይ ከቤት ውስጥ ሁከት፣ ብጥብጥና የጾታ ጥቃት ከሚነሡ ድንገተኛ ሁኔታዎች አንጻር ሲታይ” አስፈላጊ ነው። ይህ ሁሉ የመሠረታዊ መንፈሳዊ አመራርን ዋጋ፣ የቤተክርስቲያንን መንፈሳዊ ሀብትና የእርቅ ምሥጢርን አስፈላጊነት የሚደግፍ እንጂ በማናቸውም መልኩ የሚቀንስ አይሆንም።
ምንጭ፡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርእስ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 199-205 ላይ የተወሰደመሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።
አዘጋጅ አባ ዳንኤል ኃይለ