ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፥ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፥   (Vatican Media)

ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፥ “እጮኛሞችን ለጋብቻ ስለ ማዘጋጀት”

የሲኖዶሱ አባቶች በብዙ መንገዶች እንዳወሱት፥ የጋብቻን ክቡርነትና ውበት እንዲያውቁ ወጣቶችን መርዳት ያስፈልገናል። የህልውናን ማኅበራዊ ገጽታ የሚያጎላውንና ፍጹም የሚያደርገውን፣ ለወሲባዊ ተራክቦ ጥልቅ ትርጉም የሚሰጠውንና ለልጆች እድገትና ልማት ከሁሉ የተሻለ ሁኔታ የሚያመቻቸውን የምሉእ አንድነትን ማራኪነት እንዲመለከቱ ወጣቶችን መርዳት ይገባል።

“የዛሬ ኅብረተሰብ ውስብስብነትና ቤተሰብን የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች እጮኛሞችን በማዘጋጀት ረገድ የመላ ክርስቲያን ማኅበረሰብን ትልቅ ጥረት ይጠይቃሉ። የመልካም ምግባራት ጠቃሚነትም ሊካተት ይገባል። ከእነዚህም መካከል፣ በሰዎች መካከል እውነተኛ ፍቅር እንዲያብብ ንጽሕና ተወዳዳሪ አይገኝለትም። በዚህ ረገድ የሲኖዶሱ አባቶች የራሳቸውን የቤተ ሰቦችን ምስክርነት በማጉላትና በጋብቻ፣ በጥምቀትና በሌሎች ምሥጢራት መካከል ያለውን ግንኙነት በማሳየት ለጋብቻ የሚደረገውን ዝግጅት ከክርስትና ሕይወት ጅማሮ ሂደት ጋር በማስተሳሰር መላውን ኅብረተሰብ በሰፊው ማሳተፍ አስፈላጊ መሆኑን አምነውበታል። እንደዚሁም፣ ጥንዶች በቤተክርስቲያን ሕይወት ውስጥ እውነተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸውና ከቤተሰብ ሕይወት የተለያዩ ገጽታዎች ጋር ሙሉ በሙሉ እንዲተዋወቁ የሚያደርጉ ልዩ የጋብቻ ዝግጅት ፕሮግራሞች እንደሚያስፈልጉ የሲኖዶሱ አባቶች ተናገረዋል”።

ስለዚህ እጮኛሞች በፍቅር እንዲያድጉ በመርዳት እነርሱ ራሳቸው ትልቅ ጥቅም እንደሚያገኙበት ያውቁ ዘንድ ክርስቲያን ማኅበረሰቦችን አበረታታለሁ። የጣሊያን ጳጳሳት እንዳመለከቱት፣ ጥንዶች “ትልቅ ሀብት ናቸው፤ ምክንያቱም በፍቅርና ራስን አሳልፎ ለመስጠት ራሳቸውን በሐቅ ሲያዘጋጁ፣ መላውን የቤተክርስቲያን አካል አkም ለማደስ ይረዳሉ። የእነርሱ ልዩ ወዳጅነት ወደ ሌሎችም የሚጋባና አካሉ በሆኑበት ክርስቲያን ማኅበረሰብ ውስጥ ወዳጅነትንና ወንድማማችነትን የሚያዳብር ሊሆን ይችላል”። የጋብቻ ዝግጅት ፕሮግራሞችን ለማዋቀር የሚረዱ በርካታ ሕጋዊ መንገዶች አሉ፤ እያንዳንዱ የአጥቢያ ቤተክርስቲያንም ወጣቶችን ከምሥጢረ ተክሊል ሳያርቅ ተስማሚ ሕንጸት መስጠት የሚቻልበትን ዘዴ ለይቶ ማወቅ አለበት። ለወጣቶች ሁሉንም ትምህርተ ክርስቶስ ማስተማር፣ ወይም በብዙ መረጃ ማጨናነቅ አስፈላጊ አይደለም። እዚህም ላይ ቢሆን “ነፍስን የሚያረካውና የሚያጠግበው ትልቅ እውቀት ሳይሆን፣ ነገሮችን ከውስጥ ለመረዳትና ለመውደድ መቻል ነው”። ከብዛት ይልቅ ጥራት ስለሚበልጥ፣ ስብከተ ወንጌልን በአዲስ መልክ ከማወጅ ጎን ለጎን፣ ጥንዶችን ቀሪ ሕይወታቸውን ‹‹በታላቅ ጀግንነትና ልግስና›› እንዲኖሩ ለሚረዳ ማራኪና ጠቃሚ መረጃ ቅድሚያ መስጠት ይገባል። የጋብቻ ዝግጅት ለምሥጢረ ተክሊል “መለማመጃ”፣ ጥንዶች ምሥጢሩን በተገባ መንገድ እንዲቀበሉትና እንደ ቤተሰብ ሕይወትን በጽኑ መሠረት እንዲጀምሩ የሚረዳ መሆን አለበት።

በሚሲዮናዊያን (ልዑካን) ቤተሰቦች፣ በራሳቸው በጥንዶቹ ቤተሰቦችና የተለያዩ ሐዋርያዊ ሥራ ባለሙያዎች እርዳታ በመታገዝ፣ በምሳሌና በጥሩ ምክር የሩቅ ዝግጅት ለማድረግ የሚያስቸሉ መንገዶችን መፈለግ የእጮኛሞችን ፍቅር ለማሳደግና ለማጎልበት ይረዳል። የውይይት ቡድኖች እንዲሁም የወጣቶችን ትኩረት በሚስቡ የተለያዩ አማራጭ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ ንግግሮችም ጠቃሚ ናቸው። ከዚህ ሌላ፣ ዋናው ዓላማ የራስን ሙሉ ሕይወት ለማጋራት የሚፈልጉትን ሰው እንዴት መውደድ እንደሚችሉ ለመርዳት ስለ ሆነ፣ አንዳንድ የግል ስብሰባዎችን ማድረግም አስፈላጊ ነው። አንድን ሰው መውደድን መማር እንዲሁ አይመጣም ወይም ከጋብቻ ሥነ ሥርዓት አስቀድሞ በይድረስ መልክ ማለማመድ አይቻልም። ለእያንዳንዱ ባለትዳር፣ የጋብቻ ዝግጅት የሚጀምረው ከልደት ነው። ከቤተሰባቸው የተማሩት ነገር ራሳቸውን እንዲያውቁና ሙሉና ቁርጥ ውሳኔ እንዲያደርጉ ያዘጋጃቸዋል፡፡ ለጋብቻ በሚገባ የተዘጋጁ ጥንዶች ምናልባትም ከወላጆቻቸው ስለ ክርስቲያናዊ ጋብቻ የተማሩ፣ እያንዳንዳቸውን ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ የተመራረጡና ይህንኑ ውሳኔ በየዕለቱ የሚያድሱት ናቸው። በዚህ ረገድ፣ ባለትዳሮችን በፍቅርና በቤተሰብ ወንጌል እንዲያድጉ የመርዳት ዓላማ ያላቸው ሐዋርያዊ ዕቅዶች፣ ልጆቻቸውንም ለወደፊት የጋብቻ ሕይወት እንዲዘጋጁ ይረዱዋቸዋል። ከዚህ ሌላ፣ የታወቁ ሃይማኖታዊ ልምዶች ያላቸውን ሐዋርያዊ ዋጋ አሳንሰን ማየት አንችልም። አንድ ምሳሌ ለመስጠት ያህል፣ የቅዱስ ቫሌንታይንን ቀን አስታውሳለሁ። በአንዳንድ አገሮች፣ ከእኛ በቤተክርስቲያን ካለነው አስቀድሞ ስለዚህ በዓል አከባበር የሚፈጥኑት የንግድ ድርጅቶች ናቸው።

እጮኛሞችን በጊዜ የሚያዘጋጀው የቁምስና ማኅበረሰብ ከትዳር ጋር አብረው የሚመጡ ችግሮችንና ሥጋቶችንም እንዲያውቁ መርዳት አለበት። በዚህ መንገድ፣ እጮኛሞቹ ጥንዶች የግንኙነት መቋረጥና እርሱም የሚያስከትለውን አሳዛኝ ውጤት አስቀድመው አውቀው ከወዲሁ የሚያስወግዱበትን ጥበብ ያገኛሉ። ጥንዶች በመጀመሪያ ለእርስ በርሳቸው ካላቸው መሳሳብ የተነሣ አንዳንድ ነገሮችን ለመሸፋፈን ወይም አንጻራዊ ለማስመሰልና አለመግባባቶችን ለማስወገድ ጥረት ያደርጋሉ፤ ቆይቶ ግን ችግሮች ብቅ ማለታቸው አይቀርም። በዚህ ምክንያት፣ እያንዳንዳቸው ከጋብቻ ምን እንደሚጠብቁ፣ የፍቅርና የቃለ መሐላ ትርጉም ለእነርሱ ምን እንደ ሆነ፣ አንዱ ከሌላው ምን እንደሚፈልግና በጋራ ሊገነቡ የሚፈልጉት ሕይወት ምን ዐይነት እንደ ሆነ እንዲወያዩበት በጥብቅ ማበረታታት ያስፈልጋል። እነዚህን የመሰሉ ውይይቶች የሚግባቡበት ነገር ምናልባትም ትንሽ እንደ ሆነ እንዲረዱና በውበት መሳሳብ ብቻ በአንድነት ሊያቆያቸው እንደማይችል እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል። ከምኞት የበለጠ ተለዋዋጭ፣ አደገኛና ሊተነበይ የማይችል ነገር የለም። ጥንዶቹ እውነተኛና የተረጋጋ ዝግጁነት እንዳላቸው የሚያረጋግጡ ጥልቅ ምክንያቶችን ለይተው ሳያውቁ የጋብቻ ውሳኔ እንዲያደርጉ ከቶ ሊበረታቱ አይገባም።

በማናቸውም ሁኔታ ከጥንዶቹ አንዱ የሌላውን ደካማ ጎኖች በግልጽ ካወቀ፣ የእርሱን ወይም የእርስዋን ሚዛን የሚደፉ በጎ ጎኖችን የሚያዳብርበትና የጋራ ሰብዓዊ እድገታቸውን ለማጠናከር የሚረዳ እውነተኛ እምነት ማሳደር ያስፈልገዋል። ይህም የሚያጋጥሙ መሥዋዕትነቶችን፣ ችግሮችንና የግጭት ሁኔታዎችን በፈቃደኝነት መቀበልን፣ ለዚህም ዝግጁ መሆንንና ቁርጠኝነትን ይጠይቃል። ጥንዶች በግንኙነታቸው ውስጥ የአደጋ ምልክቶችን መለየትና ከጋብቻ በፊት ለእነዚህ ምልክቶች ምላሽ የሚሰጡባቸውን ውጤታማ መንገዶች ማግኘት መቻል አለባቸው። ይሁን እንጂ በሚያሳዝን ሁኔታ ብዙ ጥንዶች እርስ በርስ በሚገባ ሳይተዋወቁ ይጋባሉ። ከእርስ በርሳቸው ጋር አብሮ መሆን አስደስቶአቸዋል፣ አንዳንድ ነገሮችንም በጋራ አድርገዋል። ነገር ግን ይህን ያደረጉት ራሳቸውን የማጋለጥና ሌላው ሰው በእውነት ማን እንደ ሆነ የማረጋገጥ ፈተና ሳያጋጥማቸው ሊሆን ይችላል።

የአጭርና የረጅም ጊዜ የጋብቻ ዝግጅት ጥንዶቹ የጋብቻ ሥነ ሥርዓትን እንደ መዳረሻ ግብ አድርገው አለመመልከታቸውን ይልቁንም ጋብቻን ማናቸውንም ፈተናና አስቸጋሪ ወቅቶችን በጋራ ለመጋፈጥ በሚደረግ ጽኑና እውነተኛ ውሳኔ ላይ የተመሠረተ የዕድሜ ልክ ጥሪ መሆኑን መገንዘባቸውን የሚያረጋግጥ ሊሆን ይገባል። ለተጫጩና ላገቡ ጥንዶች የሚደረግ ሐዋርያዊ ክብካቤ የጋብቻ ትስስርን ያማከለ፣ ጥንዶችን ፍቅራቸውን እንዲያጎለብቱ ብቻ ሳይሆን ችግሮችንና መከራዎችን እንዲያሸንፉ የሚረዳቸው መሆን አለበት። ይህም የቤተክርስቲያንን አስተምህሮ እንዲቀበሉና የእርስዋን ዋጋ ያለው የሀብት ምንጭ እንዲያገኙ መርዳትን ብቻ ሳይሆን ተጨባጭ ፕሮግራሞችን፣ ተስማሚ ምክሮችን፣ ፍቱን ስትራቴጂዎችንና ሥነ ልቦናዊ አመራር መስጠትን ያካትታል። ይህ ሁሉ ከወጣቶች ፍላጎትና ስሜት ጋር የተቃኘና ውስጣዊ እድገት እንዲኖራቸው የሚረዳ የፍቅር ትምህርት መስጠትን ይጠይቃል። የጋብቻ ዝግጅት ጥንዶች ችግር ሲገጥማቸው እርዳታ የሚያገኙባቸውን የቦታዎች፣ የሰዎችና የአገልግሎቶች ስሞች የሚያሳውቅ መሆን አለበት። እንደዚሁም ኃጢአታቸውን ያለፉ ስህተቶቻቸውና ግንኙነቶቻቸውን ጭምር ወደ እግዚአብሔር ፊት የሚያቀርቡበትና በአንጻሩም የእርሱን ምሕረትና የፈውስ ብርታት የሚያገኙበት የዕርቅ ምሥጢር መኖሩን ለጥንዶቹ ማስታወስ አስፈላጊ ነው።

ምንጭ፡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርእስ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 206-211 ላይ የተወሰደመሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።

አዘጋጅ አባ ዳንኤል ኃይለ
 

26 October 2024, 16:22