ከእስራኤል ጋር ባለው ግጭት ምክንያት በቴህራን የዕለት ተዕለት ሕይወት ውጥረት ውስጥ ገብቷል ከእስራኤል ጋር ባለው ግጭት ምክንያት በቴህራን የዕለት ተዕለት ሕይወት ውጥረት ውስጥ ገብቷል  (ANSA)

ተመራጭ ካርዲናል አቡነ ማቲዩ፥ የበላይነትን ለመቀዳጀት ያለው ፍላጎት ለሰላም እንቅፋት መሆኑን አስገነዘቡ

በኢራን የላቲን ሥርዓት የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የቴህራን-ኢስፓሃን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዶሚኒክ ዮሴፍ ማቲው አገራቸው ከእስራኤል ጋር የጀመረችውን ወታደራዊ ጥቃት አስመልክተው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በኅዳር 29/2017 ዓ. ም. በቫቲካን በሚፈጸመው መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓት ላይ የካርዲናልነት ማዕረግ የሚሰጣቸው ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዶሚኒክ ጆሴፍ ማቲዩ በኢራን እና እስራኤል መካከል በተፈጠረው ግጭት ውስጥ የታዩ የቅርብ ጊዜ ለውጦችን በማስመልከት በሰጡት አስተያየት፥ በአካባቢው ሰላም ሊገኝ የሚችለው ሁለቱ ወግኖች በቀጣናው ውስጥ የበላይነትን ለመቀዳጀት ያላቸውን ፍላጎት ወደ ጎን ሲተው ብቻ ነው ብለዋል።

በመካከለኛው ምሥራቅ እና በዓለም ላይ ሰላምን ወደነበረበት ለመመለስ የሚያግዝ ዋናው መንገድ፥ ሁሉም የግጭት እና ጦርነት ተሳታፊ ወገኖች ለበላይነት ያላቸውን ፍላጎት ሲተው እና ጊዜን፣ ጉልበትን እና ሃብትን በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ከማዋል ሲቆጠቡ እና ከዕድገት እንድንርቅ በሚያደርጉ ስልቶች ላይ ገንዘብን ማፍሰስን ሲያቆሙ ነው” ሲሉ አዲስ ተመራጭ ካርዲናል ብጹዕ አቡነ ዶሚኒክ ዮሴፍ ማቲዩ አስተያየታቸውን ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለካርዲናልነት ማዕረግ ካጯቸው ጳጳሳት መካከል አንዱ የሆኑት ቤልጂዬማዊ ጳጳሳ አቡነ ዶሚኒክ ዮሴፍ ማቲዩ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 2021 ጀምሮ 82 ሚሊዮን የሚሆን የሺዓ ሙስሊም ማኅበረሰብ ባለባት ኢራን ውስጥ 2,000 የሚደርሱ ካቶሊካዊ ምዕመናንን ያቀፈ ብቸኛው የላቲን-ሥርዓት የሚከተል የቴህራን-ኢስፓሃን ሀገረ ስብከት በመምራት ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።

የ 61 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ ሊቀ ጳጳሳ አቡነ ዶሚኒክ ዮሴፍ ማቲዩ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኅዳር 29/2017 ዓ. ም. የካርዲናልነት ማዕረግ ከሚሰጧቸው 21 እጩዎች መካከል አንዱ ሲሆኑ ይህም በእስላማዊ ሪፐብሊክ ታሪክ ሦስተኛው ካርዲናል እንደሚያደርጋቸው ታውቋል። ፍራንችስካዊው ጳጳሳ ብጹዕ አቡነ ዶሚኒክ ዮሴፍ ማቲዩ በምስራቅ እና በቅድስት ሀገር ግዛቶች በሚገኘው ማኅበራቸው ውስጥ ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉ ሲሆን ከእስልምና እምነት ተከታዮች ጋር የረጅም ጊዜ የውይይት ልምድ ያላቸው መሆኑ ታውቋል።

ግጭቶችን በድፍረት እና በግልጽነት የሚጋፈጡበት ጊዜ ደርሷል!
በቅርቡ በኢራን ላይ ያነጣጠረ የእስራኤልን የአየር ጥቃት ተከትሎ ፊደስ የተሰኘ የቫቲካን የዜና አግልግሎት ያነጋገራቸው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዶሚኒክ ዮሴፍ ማቲዩ፥ በመካከለኛው ምሥራቅ እየተባባሰ ከመጣው ሁኔታ አንጻር ግጭቶችን በድፍረት እና በግልጽነት የሚጋፈጡበት ጊዜ መድረሱን ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በክልሉ እየታየ ያለው አመፅ እና ስቃይ እንዲያቆም በመማጸን “በጋራ መኖሪያ ምድራችን ወንድማማችነት ሊመጣ የሚችለው እግዚአብሔር በአደራ በሰጠን ፍቅር እርስ በርስ ስንገናኝ ብቻ ነው” ያሉትን በመድገም፥ ቅዱስነታቸው ይህን በመናገር ሞትን እና ጨለማን ብቻ የሚያመጡ ጦርነቶችን የማስቆምን አጣዳፊነት ሳያቋርጡ ማሳሰባቸውን ተናግረዋል።

ለእርቅ እና አንድነት ተጨባጭ ተግባራት ያስፈልጉናል!
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዶሚኒክ ዮሴፍ ማቲዩ፥ ሰላምን ለመገንባት እርቅን እና አንድነትን በተግባር ማሳየት እንደሚያስፈልግ አሳስበው፥ “ከልዩነቶቻችን ባሻገር በአንድነት በመጓዝ የሰላም እውነተኛ ምስክሮች መሆን እንችላለን” ብለዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዶሚኒክ ዮሴፍ ማቲዩ ቀደም ሲል አዲስ ስለሚሰጣቸው የካርዲናልነት ማዕረግ እና በኢራን የሚያበረክቱትን ሐዋርያዊ አገልግሎት በማስመልከት ከእስያ የዜና ኤጀንሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ በመካከለኛው ምሥራቅ ቀውስ ውስጥ ያለውን የጦርነት ሁኔታን አውግዘው ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጀምሮ የዓለም አቀፍ ተቋማት ድክመት ጠቁመዋል።

የተባበሩት መንግሥታት እና የአውሮፓ ኅብረት ተነሳሽነት
“የአውሮፓ ኅብረት ተኩስ እንዲቆም በማሳሰብ የሰላም ጥሪ ቢያቀርብም በሌላ ወገን የጦር መሣሪያ ወደ ታጣቂዎች መላኩን ቀጥሏል” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዶሚኒክ ዮሴፍ ማቲዩ፥ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርቡ በቤልጂየም ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው፥ የመንግሥት አካላት ኃላፊነትን በመውሰድ የሰላም ታላቅነት እንዲሰማቸው” በማለት ያሳሰቡትን በማስታወስ በብዙ አገሮች ውስጥ እጅግ ትርፋማው የጦር መሣሪያ ምርት እንደሆነ አስረድተዋል።

በመጨረሻም “ዛሬ የምንኖረው ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ማዕቀፍ እና የዲፕሎማሲ ቋንቋ በጦርነት፣ በዛቻ እና በበቀል የተሞላ ነው” ብለው ይህም እንደሚያሳዝናቸው ገልጸዋል።

 

30 October 2024, 16:23