በኢንዶኔዥያ ትልቁ ሀገረ ስብከት የሩተንግ ሀገረ ስብከት ካቴድራል በኢንዶኔዥያ ትልቁ ሀገረ ስብከት የሩተንግ ሀገረ ስብከት ካቴድራል  (Paris Foreign Missions)

የሩተንግ ሀገረ ስብከት በኢንዶኔዥያ 'ተስፋ የተጣለበት የመንፈሳዊ ጥሪ ምድር' ሆኖ ብቅ ማለቱ ተገለጸ

በኢንዶኔዢያ ሃገር በፍሎሬስ ደሴት የሚገኘው የሩተንግ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሀገረ ስብከት ለመንፈሳዊ ጥሪዎች እያበረከተ ባለው ከፍተኛ ሥራ ምክንያት “የተስፋ ምድር” የሚል ስም አትርፏል ሲሉ ብጹእ አቡነ ሲፕሪነስ ሆርማት ተናግረዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

17,000 ደሴቶች ባሏት እና ሙስሊሞች ትልቁን የህዝብ ቁጥር በያዙባት ኢንዶኔዥያ ውስጥ፥ ከአንድ ሚሊዮን ነዋሪዎች ውስጥ 800,000 የሚሆኑ የካቶሊክ ሃይማኖት ተከታይ ህዝብ ያላት ሩተንግ ከተማ በሃገሪቷ ውስጥ ትልቁ የካቶሊክ ሀገረ ስብከት መሆኗ ተነግሯል።

“የሺህ ጉባኤዎች ሀገረ ስብከት” በመባል የሚታወቀው የሩተንግ ሃገረ ስብከት በርካታ የሃይማኖታዊ ተቋማት፣ የማህበራዊ ስራዎች፣ መደበኛ ትምህርት ቤቶች እና የዘርዓ ክህነት ት/ቤቶች እንደሚገኙበት ተገልጿል።

ይህ ጠንካራ ሃይማኖታዊ መሠረት የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን ትኩረት የሳቡ ሲሆን፥ በ2014 ዓ.ም. በኢንዶኔዥያ ትልቋ ደሴት የሆነችውን ፍሎሬስ ለዓለም አቀፉ ቤተክርስቲያን የጥሪ ምንጭ እንደሆነች የጠቀሱት ቅዱስ አባታችን፥ “ጥሪን በተመለከተ እየገጠሙን ካሉት ተግዳሮቶች ጋር በተያያዘ ደሴቲቱ ትልቅ መፍትሄ እየሆነች ነው” በማለት ሃገረስብከቱ እየሰራው ላለው ሥራ እውቅና መስጠታቸው ይታወሳል።

የሩተንግ ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ሲፕሪያነስ ሆርማት ከቫቲካኑ ፊደስ የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በአካባቢው ያለውን አንጸባራቂ የዘርዓ ክህነት ህይወት አጉልተው በማሳየት፥ በሩተንግ ንኡስ ዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት ውስጥ 450 ወንዶች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሆነ ገልጸው፣ በቅርብ ከሩተንግ ሃገረስብከት ራሷን ችላ በወጣችው እና በአቅራቢያው በምትገኘው የላቡአን ባጆ ሀገረ ስብከት ውስጥ ደግሞ 350 ተማሪዎ እንዳሉ በመጥቀስ፥ “በየዓመቱ በርካታ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤቱ መግባት ይፈልጋሉ” በማለት ጨምረው ገልጸዋል።

ብጹእነታቸው የዘርዓ ክህነት ማዕከላቱ በዋነኛነት ጠንካራ መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቢሆኑም “እምነት የሚዳብርበት እና ሃይማኖታዊ ጥሪዎች የሚለዩበት ቦታ እንደሆኑም ጭምር ጠቁመዋል።

ብጹእ አቡነ ሆርማት በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ስላለው የጥሪ ሂደት ተፈጥሯዊ አካሄድን ሲያብራሩ፥ “ከንኡስ ዘርዓ ክህነት ወደ ዐብይ ዘርዓ ክህነት የሚደረገውን ጉዞ የሚቀጥሉ ሰዎች 40 ወይም 50 በመቶ መሆኑ እውነትነት ያለው እና ተፈጥሮአዊ ቢሆንም፣ ነገር ግን ይህ መሆኑ ትክክል ነው” ብለዋል።

ጳጳሱ አክለውም ወጣቶቹ “የእግዚአብሔርን ፈቃድ በሕይወታቸው ውስጥ ማዳመጥ እና መመርመር እንዲሁም መንገዳቸውን መከተል አለባቸው” ካሉ በኋላ፥ “ያም ሆነ ይህ፣ እነዚህ ዓመታት ለሰው ልጅ እና ለክርስቲያናዊ ምስረታ ጠቃሚ ናቸው፤ እነዚህ ዓመታት በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ይዘውት የሚቆዩት ጠቃሚ ቅርስ ናቸው” በማለት የጥሪን አስፈላጊነት ገልጸዋል።

በሀገረ ስብከቱ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ሃዋሪያዊ ሥራም በተመሳሳይ መልኩ አስደናቂ እንደሆነ በቃለ ምልልሱ ወቅት የተጠቀሰ ሲሆን፥ 85 ደብሮች፣ 212 የሀገረ ስብከቱ ካህናት እና ከ200 የሚበልጡ የማህበራት ካህናት፣ እንዲሁም 50 ከሚሆኑ የተለያዩ ገዳማት የተውጣጡ ከ1,000 በላይ ገዳማዊያት ሴቶች በሃገረ ስብከቱ ውስጥ እያገለገሉ እንዳሉ ጠቁመዋል።

“እምነት እዚህ ሕያው ነው፣ ለዚህም በሁሉም መንደሮች ወንጌልን አምጥተው የሰበኩ የፖርቹጋል እና የኔዘርላንድ ሚስዮናውያንን እናመሰግናለን” ያሉት ብጹእ አቡነ ሆርማት፥ የአካባቢው ቤተ ክርስቲያን ከ 1984 ዓ.ም. ጀምሮ እራሷን ችላ እንደወጣች ተናግረዋል።

ከሃይማኖታዊ ተጽእኖ በተጨማሪ ሩተንግ የምትገኘው የካቶሊክ ቤተክርስትያን በመደበኛው የትምህርት ሥርዓት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያበረከተች እንዳለ የጠቀሱት ጳጳሱ፣ “ከሌሎች በርካታ ትምህርታዊ ሥራዎች በተጨማሪ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ባሉ 265 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና 20 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች እየተማሩ ይገኛሉ” ብለዋል።

ከታሪክ አኳያ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ጥራት ያለው ትምህርትን የምታበረታታ ተቋም ስትሆን፣ በክልሉ የተቋቋሙት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የካቶሊኮች እንደነበሩ ጳጳሱ አክለው ተናግረዋል።

የሳን ፓኦሎ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ መጠናቀቁ እንደ ቁልፍ ምዕራፍ ይቆጠራል ያሉት ብጹእ አቡነ ሆርማት “ለወጣቶቻችን በጣም ጠቃሚ ይሆናል ብለን እናስባለን” ብለዋል።

የሩተንግ ሃገረ ስብከት በጥሪ በኩል እየሰራ ያለው ሥራ ውጤቱ ከክልሉም በላይ እንደሚዘልቅ በመግለጽ፥ ሀገረ ስብከቱ የኢንዶኔዥያውን “ሚሲዮ ዶሜስቲካ” የሚባል ፕሮግራም በመደገፍ ካህናትን ወደ ፓፑዋ፣ ሱማትራ እና ቦርንዮ ላሉ ክልሎች በመላክ ላይ በንቃት ይሳተፋል ያሉ ሲሆን፥ “ይህንን ሀብት ማለትም የሩተንግ ካህናትን በኢንዶኔዥያ ቤተክርስቲያን እና በዓለምአቀፉ ቤተክርስቲያን ውስጥ ለአገልግሎት እናሰማራለን” ካሉ በኋላ ካህናቱ በስዊዘርላንድ፣ በኦስትሪያ እና ጣሊያንን ጨምሮ በአውሮፓ ሃገራት ውስጥ እንደሚያገለግሉ ገልጸዋል።

ሃገረ ስብከቱ ከሆላንድ ጋር ልዩ የሆነ የሃዋሪያዊ ሥራ ስምምነት ያለው ሲሆን፣ ይህም የሩተንግ ካህናት በ ‘ፊዲ ዶነም’ ቄስ ሆነው ወደ አገራቸው ከመመለሳቸው በፊት ለጥቂት ዓመታት በኔዘርላንድ ውስጥ እንዲሰሩ ያስችላቸዋል ተብሏል።

“የክህነት እና የቅድስና ጥሪ ስጦታ ሁል ጊዜ ምስጢር ነው፥ ምክንያቱም የሚጠራው እግዚአብሔር ነው” ያሉት ብጹእ አቡነ ሆርማት “ወጣቶችን ወደ ክህነት እንዲገቡ ማገዝ ለእኛ ብቻ ሳይሆን አውሮፓን ጨምሮ ለመላው የቤተክርስቲያን ማህበረሰብ ትልቅ ጠቀሜታ አለው” ብለዋል።

የሩተንግ ሃገረስብከት ለዓለም አቀፉ ቤተክርስቲያን የሚያበረክተው ቀጣይነት ያለው ቁርጠኝነት ከደች ሚስዮናውያን ጋር ባለው ታሪካዊ ትስስር ላይ የተመሰረተ ነው ያሉት ጳጳሱ፥ እ.አ.አ. ከ1951 እስከ 1972 ዓ.ም. ድረስ የሩተንግ ሀገረ ስብከት የመሩትን የመጨረሻው ሆላንዳዊ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ቨርቢት ዊል-ሄልም በደስታ ስሜት በማስታወስ፥ “የመጨረሻው የኔዘርላንድ ጳጳስ የሰሩት መልካም ስራ ትዝታ አሁንም በልባችን ውስጥ አለ፥ የነዚህን ሚስዮናውያን ስራ በማስቀጠል ዛሬ ምስጋናችንን እንገልፃለን” በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ቤተክርስቲያን “ክፍት፣ ሚስዮናዊ እና ሁሉን አካታች የሆነ ቤተ ክርስቲያን” እንድትሆን ያቀረቡትን ጥሪ አስተጋብተዋል።
 

17 October 2024, 13:43