በሙምባይ የሚገኘው የሮዛሪ ቤተክርስቲያን ዓመታዊ ክብረ በዓል በሙምባይ የሚገኘው የሮዛሪ ቤተክርስቲያን ዓመታዊ ክብረ በዓል  

የህንድ ቤተክርስቲያን ‘ከማርያም ጋር ወደ ሲኖዶሳዊ ቤተ ክርስቲያን ጉዞ’ በሚል መሪ ቃል ዓመታዊ ክብረ በዓል አከበረች

በሙምባይ የሚገኘው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ሮዛሪ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የበለጠ ሲኖዶሳዊ ቤተክርስቲያን መሆን ይገባታል ብለው ያቀረቡትን ጥሪ ለመቃኘት በተዘጋጁ ልዩ ልዩ ክንውኖች ዓመታዊ የሰበካ በዓሉን አክብሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በህንድ ሃገር ሙምባይ ከተማ የሚገኘው የሮዛሪ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰኞ ዕለት በተከበረው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ የሲኖዶሱን ሂደት በበዓሉ የአከባበር መርሃግብሮች ውስጥ በማካተት እንደተከበረ ተነግሯል።

የቤተክርስቲያኑ ካህን የሆኑት አባ ኒጄል ባሬት የብጹአን ጳጳሳት ሲኖዶስ መደበኛ ጉባኤ ሁለተኛው ምዕራፍ በሮም እየተካሄደ ባለበት በአሁኑ ወቅት ማህበረሰቡ ሲኖዶሳዊነትን እንደሚቀበል ያላቸውን እምነት ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ገልጸዋል።

“የቁምስና ዓመታዊ በዓላችንን ስናከብር ‘ከማርያም ጋር ወደ ሲኖዶሳዊ ቤተ ክርስቲያን ጉዞ’ በሚል መሪ ሃሳብ ላይ እያሰላሰልን ነው” ያሉት ካህኑ፥ “የእኛ የኖቬና ጸሎቶች የሰበካውን ማህበረሰብ በእምነት፣ በምስጋና እና በተስፋ አንድ ላይ አምጥቷቸዋል” ካሉ በኋላ፣ “የሮዛሪ ቤተ ክርስቲያን አባላት ጠባቂያችን በሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ተባርከናል” በማለት የገለጹ ሲሆን፥ ችግሮች ወይም ጥርጣሬዎች ሲያጋጥሙን ወይም በቀላሉ ወደ ጌታችን መቅረብ ስንፈልግ የመቁጠሪያ ጸሎት በምናደርግበት ወቅት ጥልቅ በሆነ እምነት የመኖር በር እንደሚከፈትልን፣ ከጌታችን እና ከቅድስት እናቱ ጋር እንደምንቀራረብ፣ እንዲሁም የበለጸገ የደቀ መዝሙርነት ሕይወት መኖር እንደምንችል ከተባረከች እናታችን ማረጋገጫ አለን” በማለት አብራርተዋል።

ይህ ለሳምንት የሚቆየው ክብረ በዓል ለሲኖዶሱ ሂደት መሳካት በሚፀልዩ፣ የግል ሃሳቦቻቸውን በሚያቀርቡ እና ለበዛው በረከታቸው ምስጋና በሚያቀርቡ በአነስተኛ የክርስቲያን ማህበረሰቦች የሚመራ የምሽት ዝግጅትን እንደሚያካትትም ካህኑ ገልፀዋል።

በማግስቱም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥያቄና መልስ፣ ስለ መቁጠሪያ ጸሎት እና የቁምስናው ታሪክ የሚዳሰስበት መርሃ ግብር ይካሄድና፥ ከሀገረ ስብከቱ የተለያዩ ክፍሎች የተውጣጡ ሰዎች እንደ ህብረተሰቡ አካል የምስጋና ጸሎት በማድረግ ክብረ በዓሉ ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ይጠናቀቃል ተብሏል።

አባ ባሬት የሰበካው ማህበረሰብ በቤተክርስቲያን ህይወት እና ተልዕኮ ውስጥ የሚሳተፍ ንቁ እና ደስተኛ ማህበረሰብ እንደሚሆን፣ እንዲሁም ራቅ ባለ አከባቢ ላሉትም እንደሚደርስ ያላቸውን ተስፋ በመግለጽ፣ “በተጨነቀው ዓለም ውስጥ የብርሃን ቀንዲሎች” ለመሆን ሰበካችን የመቁጠሪያዋን እመቤታችንን እንደ መሪ ትመለከታለች” ብለዋል።

አባ ባሬት በመጨረሻም፣ በሙምባይ ዶክያርድ የሚገኘው የካቶሊክ ማህበረሰብ፣ ቁሳዊ እርዳታ ለሚፈልጉ አንዳንድ አባላቱ ሰብዓዊ እገዛ በማድረግ፣ ከመንፈሳዊ ሥራ በተጨማሪ መንቀሳቀስ እንደሚፈልግ በመጥቀስ፥ በቁምስናው እየተከናወኑ ያሉ የምገባ ፕሮጀክት እና የህክምና ዕርዳታ ያሉ ተነሳሽነቶች ምዕመናን የወንጌል እሴቶችን እንዲያሳድጉ እንደሚረዷቸው፥ ይህም ሁሉም ምዕመናን በሕይወታቸው ውስጥ ድጋፍ፣ ክብር እና እንክብካቤ እንዲያገኙ ያደርጋል በማለት አጠቃለዋል።
 

09 October 2024, 13:30