የዛሬ 40 ዓመት  በፀረ-ኮምኒስት ሥራቸው የተገደሉት አባ ጄርዚ ፖፒሱዝኮ የዛሬ 40 ዓመት በፀረ-ኮምኒስት ሥራቸው የተገደሉት አባ ጄርዚ ፖፒሱዝኮ 

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እና ለነፃነት ብለው የተሰውት አባ ጄርዚ ፖፒሉዝኮ

ፖላንዳዊው ካህን አባ ጄርዚ ፖፒሉዝኮ ከ40 ዓመታት በፊት ፀረ-ኮሚኒስት አራማጆችን ይደግፋሉ በሚል ሰበብ ምክንያት የተገደሉ ሲሆን፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በወቅቱ በአውሮፓ ውስጥ የሚገኝ ፖላንዳዊ ጠባቂ ብለው ሰይመዋቸው እንደነበር ይታወሳል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እንደሚታወቀው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሃንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እና አባ ጄርዚ ፊት ለፊት ተገናኝተው አያውቅም። እ.አ.አ. በ 1983 ዓ.ም. ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የትውልድ አገራቸው የሆነችውን ፖላንድ እየጎበኙ በነበረበት ወቅት ሃገሪቱን ይገዛ የነበረው የኮሚኒስት መንግስት ካህኑ ብጹእነታቸውን እንዳይጎበኙ ልዩ ፈቃድ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።
አባ ጄርዚ እንደሌሎች የዘመናቸው ካህናት ሁሉ፣ ፖላንዳዊው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሃንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረውባቸው እንደነበር ይነገራል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ካህኑ በዋርሶ ውስጥ የሚገኙ ሰራተኞችን እንደሚያገለግሉ ያውቁ ስለነበረ የካህኑን ስብከቶች በሚገባ ያውቃሉ። በወቅቱም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለካህኑ ሰላምታ እና መቁጠሪያ ልከውላቸው የነበረ ሲሆን፥ ጥቅምት 24 ቀን 1977 ዓ.ም. ካህኑ ከዚህ ዓለም ድካም ባረፉበት ወቅት በሬሳ ሣጥን ውስጥ ሆነው በእጃቸው ላይ ተጠምጥሞ የነበረው መቁጠሪያም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የሰጧቸው መቁጠሪያ እንደነበር ተገልጿል።

ወደ ትንሣኤ የሚያደርሰው መስዋዕትነት
አባ ጄርዚ ጥቅምት 9 ቀን 1977 ዓ.ም. በመንግስት ሃይሎች ተጠልፈው በተወሰዱበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በሳምንታዊው ጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እና በመልአከ እግዚያብሄር ጸሎታቸው ወቅት ለካህኑ ጸሎት እንዲደረግ ጠይቀው፥ ጠላፊዎቹ ካህኑን እንዲለቁ ጥሪያቸውን አቅርበው ነበር።

የአባ ጄርዚ አስከሬን ከአስራ አንድ ቀናት በኋላ ሲገኝ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ይህ ሰማዕትነት በፖላንድ የነፃነት ትግል ውስጥ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ውዲያው ተገንዝበው እንደነበር ይነገራል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ጥቅምት 21 ቀን 1977 ዓ.ም. ባቀረቡት ሳምንታዊው ጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ላይ “ክርስቲያኖች በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል አሸናፊዎች እንዲሆኑ መጠራታቸውን በመግለጽ፥ “በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚመጣው ድል ደግሞ ከብርቱ ድካም አልፎ ተርፎም ከሥቃይ የማይለይ እንደሆነ፣ እንዲሁም የክርስቶስ ትንሳኤ ከመስቀል የማይለይ መሆኑን በመግለጽ፥ ምንም እንኳን ካህኑ ዛሬ ላይ አካላቸው መሬት ውስጥ ቢቀበርም፣ በክርስቶስ ድል አድርገዋል በማለት ሰብከው እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።

ከዚህም በተጨማሪ በሚቀጥለው ረቡዕ ዕለት በተካሄደው ጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አክለው እንደተናገሩት “የአባ ጄርዚ ሞት ለትውልድ የሚሸጋገር ምስክር ነው፥ መስቀል የትንሳኤ ፍሬ እንዳፈራ ሁሉ ይህ ሞት የደግነት እና የመልካምነት ፍሬ እንዲያፈራ እንዲሁም ነፍሳቸው በሰላም እንድታርፍ አጥብቄ እጸልያለው” ብለዋል።

በነጻነት ጊዜ ምስክር
ከአምስት ዓመታት በኋላ ፖላንድ ከኮሚኒስት አገዛዝ ሥር ነፃነቷን በማስመለስ የመጀመሪያዋ አገር ነበረች። በእነዚህ አዳዲስ ሁኔታዎች፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የአገራቸው ሰው ስለሆኑት ስለ አባ ጄርዚ ጽኑ ተምሳሌትነት በማስታወስ፥ “ጊዜ የማይሽረው እና ትናንት ብቻ ሳይሆን ምናልባትም ዛሬ ላይ የበለጠ የሚሰራው የዚህ ካህን ህይወት የሁላችንም ጥሪ ይሁን” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በጵጵስና ዘመናቸው ሁሉ የፖላንድ ህዝብ በአውሮፓ አህጉር ላይ እየመጣ ያለውን ለውጥ እንዴት መቀበል እንዳለበት የአባ ጀርዚን ምስክርነት እንደ ምሳሌ ሲያቀርቡ ኖረዋል።

የካቲት 7 ቀን 1983 ዓ.ም. ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በወቅቱ የፖላንድ ፕሬዚዳንት የነበሩት ለች ዋሽሳ በተገኙበት “ፖላንድ አውሮፓን ክዳ እንደማታውቅ” በማሳሰብ፥ “ፖላንድ ለአውሮፓውያን ማህበረሰብ ትልቅ ኃላፊነት ይሰማታል፥ ሃገሪቷ ከአውሮፓ እርዳታ ብትጠብቅም ለዚህች አህጉር እንዴት መሞት እንዳለባትም ጠንቅቃ ታውቃለች” ብለዋል።

በዚህ አውድ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አውሮፓን በአዲስ መልክ ባደራጀው የያልታ ጉባኤ ወቅት የተገኘውን ኢፍትሐዊ ሰላም አስታውሰዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የፖላንድ ሕዝብ ከወቅቱ አስተሳሰብ ጋር ተስማምቶ እንደማያውቅ ወይም በእሱ ላይ ለተጫነው ርዕዮተ ዓለም እና አምባገነናዊ አገዛዝ እጅ እንዳልሰጠ በመጠቆም፥ “የፖላንድ ሕዝብ ለክብሩና ለመብቱ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሏል፥ ለዚህም አባ ጄርዚ የዚህ ትግል ምልክቶች አንዱ ማሳያ ናቸው” በማለት አብራርተዋል።

በአውሮፓ ውስጥ የፖላንድ መገኘት
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ከጥቂት ወራት በኋላ ወደ ፖላንድ ባደረጉት ጉዞ የካህኑን መስዋዕትነት እንደገና አንስተው የነበረ ሲሆን፥ ‘ቀድሞውንም ከአውሮፓ ስላልወጣን መመለስ አያስፈልግም’ በሚል በወቅቱ ፖላንድ ወደ አውሮፓ እንድትመለስ ከሚሟገቱት ጋር ግልጽ የሆነ ክርክር አካሂደው ነበር።

“ፖላንድ ከአውሮፓ መስራቾች ውስጥ አንዷ ሆና እያለች ወደ አውሮፓ ትመለስ” የሚል ክርክር ዬትም እንደማያደርስ ያነሱት ብጹእነታቸው፥ "የሮም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት እንደመሆኔ ይህንን አውሮፓዊ እንዲሁም ምዕራብ አውሮፓዊ የመሆን መመዘኛ መቃወም እፈልጋለሁ” ካሉ በኋላ፥ “ይህ ለታላቁ የባህል፣ የክርስትና ባህል ባለቤት ሃገር ትልቅ ስድብ ነው” የአውሮፓ ባህል በምስራቅ ሰማዕታት በኩል ባለፉት አሥርተ ዓመታት እንደተፈጠረው፣ በመጀመሪያዎቹ የሦስት መቶ ዓመታት ሰማዕታት እና በአገራችንም ከቅርብ አሥርተ ዓመታት በፊት የተፈጠረ ነው። አባ ጄርዚ በዚህ መልኩ ነው አስተዋጽዖ ያበረከቱት፥ እንደ ክርስቶስ የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል ነው ለአውሮፓ አንድነት የተሰውት፥ ይህ በአውሮፓ የመገኘታችን በረከት ነው” ካሉ በኋላ፥ እንደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለም ላይ ብሎም በአውሮፓ የዜግነት መብት አላቸው፣ ምክንያቱም ህይወታቸውን ስለ ሁላችንም አሳልፈው ሰጥተዋል” በማለት በስብከታቸው ውስጥ አብራርተዋል።

ሕሊናችን በሻጋታ አይሸፈን
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ከማርክሲስት አምባገነንነት ውድቀት በኋላ በብዙ ምክንያቶች የአባ ጄርዚ መስዋዕትነት ለአውሮፓ ያደረገውን አስተዋጽዖ ይጠቅሱ የነበረ ሲሆን፥ በ 1982 ዓ.ም. ባደረጉት ሳምንታዊው ጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ወቅት ሰማዕቱ ካህን የተናገሯቸውን በርካታ ንግግሮች ይጠቅሱ እንደነበር በማስታወስ፥ “አንድ ሰው መንፈሳዊ እና ነፃ ሆኖ ለመኖር በእውነት ውስጥ መኖር አለበት፥ በእውነት ውስጥ መኖር ማለት በተግባር መመስከር፣ እውቅና መስጠት እና በሁሉም ሁኔታዎች ውስጥ ይሄንን ማረጋገጥ ነው። እውነት አይለወጥም፣ እውነት በአንድ ወይም በሌላ ውሳኔ እንዲሁም በዬትኛውም ህግ ሊጠፋ አይችልም፣ ሕሊናችን በሻጋታ እንዲሸፈን ካልፈለግን በእውነት ውስጥ መኖርን እናስቀድም” በማለት መክረዋል።

የቫቲካን ሚዲያ ለጉዳዩ ትኩረት መስጠቱ 
የቫቲካን መገናኛ ብዙኃን ከዚህ በፊት ተደርጎ የማይታወቀውን የአባ ጄርዚን ጠለፋ እና ሞት በስፋት ሲዘግቡ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፥ ከጥቅምት 12 ቀን 1984 ዓ.ም. ጀምሮ ላ’ ኦዜርቫቶሬ ሮማኖ ጋዜጣ እያንዳንዱን የታሪኩን ሂደት በየዕለቱ የፊት ገፁ ላይ ይዘግብ እንደነበር እና ከጠለፋው በኋላ በነበሩት የመጀመሪያ ቀናት የወጡ አርዕስቶችም ስለ ካህኑ ሲያወሱ የነበሩ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ “ሁሉም ፖላንዳዊ ስለ ካህኑ ያሳስበዋል” ፣ “አንድ ካህን ከተጠለፈ በኋላ በፖላንድ ውስጥ የነበሩ አስፈሪ ጊዜያት” ፣ “ሙሉ ፖላንድ በአባ ጄርዚ ጉዳይ ላይ በጋራ ተንቀሳቅሷል” የሚሉትን ጨምሮ በርካታ ይዘቶችን ይዘው ወጥተው ነበር።

ከዚህም ባለፈ ጥቅምት 15 የቫቲካን ጋዜጣ ስለ ጠላፊዎቹ መታሰር የሚያበስር መረጃን በፊት ገጹ ላይ አሳትሞ የነበረ ሲሆን፥ ላ ኦዘርቫቶሬ ሮማኖ በሌላ እትሙ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሃንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የተደረጉ ጥሪዎችን እና የፓሪስ ሊቀ ጳጳስ ብጹእ ካርዲናል ዣን ማሪ ሉስቲገር “እኛ እየኖርን ያለነው በነፍሰ ገዳዮች ዘመን ላይ ነው” ያሉትን ጨምሮ ዓለም በጉዳዩ ላይ የሰጠውን ምላሽ አሳትሞ እንደነበር ይታወሳል።
 

22 October 2024, 13:55