ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፤  ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፤  

ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፥ "የመጀመሪያዎቹን የጋብቻ ዓመታት ስለ ማላመድ"

ጋብቻ እርስ በርስ በነጻ ፈቃድ የተመራረጡና የሚዋደዱ ሰዎች ብቻ የሚመሠርቱት የፍቅር ሥራ እንደ ሆነ መረዳት ያስፈልጋል። ፍቅር የአካላዊ መሳሳብ ወይም ደብዛዛ ፍቅር ብቻ ከሆነ፣ ጥንዶች በተለይ ይህ ፍቅር ሲደበዝዝ ወይም አካላዊ ውበት ሲረግፍ ለሥጋት ተጋላጭ ይሆናሉ። ይህ የሚሆንበት የጊዜ ድግግሞሽ ሲታይ፣ ጥንዶች በትዳር ሕይወት የመጀመሪያ ዓመታት ዕድሜ ልካቸውን በአንድነትና በፍቅር ተሳስረው ለመኖር አውቀውና ፈቅደው ያደረጉትን ውሳኔ ይበልጥ ማዳበርና ማጽናት እንደሚያስፈልጋቸው ያመለክታል። ብዙውን ጊዜ የመተጫጨት ጊዜ በቂ አይሆንም፣ ውሳኔው በተለያዩ ምክንያቶች ይዘቅጣል፤ ይባስ ብሎ ጥንዶቹ ራሳቸው በቂ ብስለት አይኖራቸውም። ከዚህም የተነሣ፣ አዲስ ባለትዳሮች በመተጫጨት ወቅት መከናወን ያለበትን ሂደት መፈጸም ያስፈልጋቸዋል።

ሌላው ከጋብቻ ዝግጅት ጋር የተያያዘ ትልቁ ተግዳሮት ጋብቻ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተደርጎ የሚያበቃ ነገር አለመሆኑን ጥንዶቹ እንዲገነዘቡ የመርዳት ጉዳይ ነው፡፡ የእነርሱ ኅብረት እውነተኛና የማይታጠፍ፣ በምሥጢረ ተክሊል የተረጋገጠና የተቀደሰ ነው፡፡ ሆኖም፣ ጥንዶቹ ሕይወታቸውን በአንድነት ሲያጣምሩ፣ በረጅም ጊዜ ዕቅድ ውስጥ ንቁና ፈጠራ ያለበትን ሚና ይወስዳሉ፡፡ አሁን የእነርሱ እይታ በእግዚአብሔር ጸጋ በመታገዝ በየዕለቱ እንዲገነቡት በተጠሩበት በወደፊት ሕይወታቸው ላይ ማተኮር አለበት፡፡ በዚህ ምክንያት፣ ማንኛቸውም ሌላውን ፍጹም እንዲሆን መጠበቅ አይችልም፡፡ እያንዳንዳቸው ቅዠትን ትተው ሌላውን እንዳለ፣ እንዳልተጨረሰ፣ ማደግ እንዳለበትና በሂደት ላይ እንዳለ ሥራ አድርገው መቀበል አለባቸው፡፡ የትዳር አጋርን ሁልጊዜ መተቸት፣ ትዳርን በአንድነት፣ በትዕግሥት፣ በመግባባት፣ በመቻቻልና በልግስና የሚተገብሩት ዕቅድ ተደርጎ ላለመታየቱ አንዱ ምልክት ነው፡፡ ከዚያም ቀስ በቀስ፣ ነገር ግን፣ በእርግጠኝነት፣ ፍቅር ለማያበራ ጥያቄና ትችት ቦታውን ይለቃል፤ አንዱ ወገን በሌላው በጎና መጥፎ ነጥቦች ላይ ያተኩራል፤ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል፤ በፉክክርና ራስን ትክክለኛ አድርጎ በማሳየት ላይ ይጠመዳል። ያን ጊዜ ጥንዶቹ የዳበረ ኅብረት ለመፍጠር ይቻል ዘንድ እርስ በርስ መረዳዳት ከማይችሉበት ደረጃ ይደርሳሉ፡፡ ሰርግ ‹‹ገና ጅማሮ›› መሆኑን ይረዱ ዘንድ ይህን እውነታ ከመነሻው ለአዲስ ተጋቢዎች ማስገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ‹‹ቃል እገባለሁ›› ሲሉ ወደ ግባቸው እንዳይደርሱ መንገድ ላይ የሚገጥሙአቸውን መሰናክሎች ሁሉ ማስወገድን የሚጠይቅ ጉዞ ይጀምራሉ፡፡ የሚቀበሉት የጋብቻ ቡራኬ ለዚህ ጉዞ የሚረዳ ጸጋና ማበረታቻ ነው፡፡ የሚጠቀሙት ቁጭ ብለው፣ ግባቸውን በተጨባጭ ማሳካት በሚችሉበት መንገድ ላይ እርስ በርስ ሲወያዩ ብቻ ነው፡፡

የረጋ ውሃ አይረባም የሚል የቆየ ብሂል እንዳለ አስታውሳለሁ፡፡ በትዳር የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የጥንዶቹ የፍቅር ሕይወት እንቅስቃሴ ከሌለው፣ ወደ ፊት የሚያራምደውን የስሜት ኃይል ያጣል፡፡ ወጣት ፍቅር በደስታና በታላቅ ተስፋ ጉዞውን መቀጠል ያስፈልገዋል፡፡ ተስፋ በእነዚያ የመጀመሪያ የትጭጭትና የትዳር ዓመታት ከጭቅጭቅ፣ ከግጭትና ከችግሮች ባሻገር መመልከትንና ነገሮችን አስፍቶ ማየትን የሚያመቻች እርሾ ነው፡፡ ተስፋ እድገት እንዲኖር ጥርጣሬያችንና ጭንቀታችንን ይገታል፡፡ ከዚህ ሌላ፣ ተስፋ የአሁኑን ጊዜ በሙላት እንድንኖር፣ ሁለንተናችንን ለቤተሰብ ሕይወት እንድናውል ያደርገናል፤ ምክንያቱም ለነገ ጠንካራ መሠረት መጣል የሚቻለው ዛሬን በሚገባ በመኖር ነው፡፡

ይህ ሂደት ልግስናንና መሥዋዕትነትን በሚጠይቁ በተለያዩ ደረጃዎች ውስጥ ይከሰታል፡፡ የመጀመሪያዎቹ ብርቱ ማራኪ ስሜቶች ሌላኛው የትዳር አጋሬ አሁን የሕይወቴ አካል ሆኖአል ለሚለው ግንዛቤ ቦታቸውን ይለቃሉ፡፡ አንዱ የሌላው የመሆን ደስታ ሕይወትን የጋራ እቅድ አድርጎ ወደ ማየት፣ የሌላውን ደስታ ከራስ ደስታ ወደ ማስቀደም፣ ይህ ትዳር ኅብረተሰብን ያዳብራል ወደሚል አስደሳች ግንዛቤ ያደርሳል። ፍቅር እየዳበረ ሲሄድ፣ “መደራደርንም” ይማራል፡፡ ይህ ድርድር ከራስ ወዳድነት ወይም ለራስ ጥቅም ከመፈለግ የሚመነጭ ሳይሆን፣ ለቤተሰብ ጥቅም ሲባል የጋራ ፍቅርን የሚተገብርና የመስጠትና የመቀበል መስተጋብር ያለው ነው፡፡ በእያንዳንዱ የትዳር ሕይወት ደረጃ ሁለት አሸናፊዎች እንጂ አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ እንዳይሆን፣ ቁጭ ብሎ በተደረሰባቸው ስምምነቶች ላይ እንደ ገና መደራደር ያስፈልጋል፡፡ በቤት ውስጥ፣ ውሳኔዎች በተናጠል ሊወሰዱ አይችሉም፤ ምክንያቱም እያንዳንዱ የትዳር አጋር የቤተሰብ ኃላፊነትን ይጋራል፤ ሆኖም፣ እያንዳንዱ ቤት ልዩ ነው፣ እያንዳንዱ ትዳርም ለራሱ የሚበጀውን መንገድ ያመቻቻል።

ለትዳር መፍረስ ምክንያት ከሚሆኑ ነገሮች መካከል ስለ ጋብቻ ያልተገባና የተጋነነ ተስፋ ማድረግ ይገኝበታል፡፡ እውነታው ከተገመተው በላይ ውስንና ፈታኝ መሆኑ ሲታወቅ፣ መፍትሔው ፈጥኖና ኃላፊነት በጎደለው መንገድ መለያየትን ማሰብ ሳይሆን፣ የትዳር ሕይወት እያንዳንዱ የትዳር አጋር ሌላውን በእውቀት እንዲበስል የእግዚአብሔር መሣሪያ የሚሆንበት የዕድገት ሂደት እንደ ሆነ መገንዘብ ነው፡፡ ለውጥ፣ መሻሻል፣ በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ ያሉ መልካም ባሕርያት ማበብ፣ እነዚህ ሁሉ የሚቻሉ ነገሮች ናቸው። እያንዳንዱ ትዳር፣ ከደካማ መሠረት ተነሥቶ በእግዚአብሔር ስጦታና በራሳችን ፈጠራ የታከለበትና ለጋስ ምላሽ በጊዜ ሂደት ወደ ውድና ዘላቂ ነገር የሚያድግ “የድኅነት ታሪክ” ይመስላል፡፡ የሁለት ፍቅረኛሞች ትልቁ ተልእኮ አንዱ ሌላውን ይበልጥ ወንድና ይበልጥ ሴት እንዲሆኑ እርስ በርስ መረዳዳት አይደለምን? እድገትን ማነቃቃት ማለት አንድን ሰው የራሱን ወይም የራስዋን ማንነት እንዲቀርጽ ወይም እንድትቀርጽ መርዳት ነው፡፡ ስለዚህ፣ ፍቅር ጥበበኛነት ነው ማለት ይቻላል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ወንድና ስለ ሴት መፈጠር ስናነብ፣ እግዚአብሔር መጀመሪያ አዳምን ሲሠራ እናያለን (ዘፍጥ. 2፡7)። ከዚያም አንድ አስፈላጊ ነገር እንደ ጎደለ ስለ ተረዳ ሔዋንን ይሠራል፣ ሰውየውም አዳምም፥ “እነሆ፣ ይህች አጥንት ከአጥንቴ፣ ሥጋም ከሥጋዬ ናት” ብሎ በአድናቆት ሲናገር እግዚአብሔር ሰማ፡፡ እኛም ሰውየውና ሴቲቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲተዋዋቁ ያደረጉትን አስደናቂ ጭውውት መስማት እንችላለን፡፡ በባለ ትዳሮች ሕይወት ውስጥ፣ በአስቸጋሪ ወቅቶች ጭምር፣ አንዱ ሰው ሌላውን ሁልጊዜ እንደሚያስደንቅ፣ እና ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገናኙ ይመስል የግንኙነታቸው አዲስ በሮች ወለል ብለው እንደሚከፈቱ መገመት ይቻላል፡፡ በእያንዳንዱ አዲስ ደረጃ፣ እርስ በርሳቸውን ‹‹ማነጻቸውን›› ይቀጥላሉ፡፡ ፍቅር አንዱ ሌላውን በጥበበኛ ትዕግሥት፣ ከእግዚአብሔር በሚመጣ ትዕግሥት እንዲጠባበቁ ያደርጋቸዋል፡፡

ለአዲስ ባለትዳሮች የሚደረግ ሐዋርያዊ ጥበቃ ሕይወትን ለመስጠት ለጋስ እንዲሆኑ ማበረታታትንም ያካትታል፡፡ ‹‹ከጋብቻ ፍቅር ግላዊና ሙሉ በሙሉ ሰብአዊ ከሆነ ባሕርዩ አንጻር፣ የቤተሰብ ዕቅድ በተገቢው መንገድ ሊፈጸም የሚችለው በባልና ሚስት መካከል በሚደረግ ስምምነትና ውይይት፣ ጊዜያትን በማክበርና የትዳር አጋርን ክብር በመጠበቅ ይሆናል፡፡ በዚህ ረገድ፣ ብዙውን ጊዜ ለሕይወት ጸር የሆነውን አስተሳሰብ ለመቃወም እንዲቻል ሁማኔ ቪቴ በሚል ርእስ የሚታወቀው ሐዋርያዊ መልእክት (ንጽ. 1014) እና ፋሚሊያሪስ ኮንሶርሲዮ የተሰኘው ሐዋርያዊ ማበረታቻ አስተምህሮ (ንጽ. 14፤ 2835) እንደገና ግምት ውስጥ መግባት አለበት፡፡ ኃላፊነት የሚሰማው ወላጅነትን የሚያካትቱ ውሳኔዎች “የአንድ ሰው እጅግ የተቀደሰ ምሥጢራዊ ማእከልና መጠለያ የሆነውን›› ኅሊና ማነጽን ይጠይቃል፡፡ ‹‹በዚያ እያንዳንዱ ሰው ድምጹ ከልብ ጥልቅ ጓዳ ከሚያስተጋባው ከእግዚአብሔር ጋር ብቻውን ይሆናል” (ጋውዲዩም ኤት ስፔስ፣ 16)፡፡ ጥንዶቹ በበለጠ ንቃተ ኅሊና እግዚአብሔርንና የእርሱንም ትእዛዛት ለመስማት በጣሩ (ንጽ. ሮሜ 2፡15) እና መንፈሳዊ ድጋፍ ባገኙ ቁጥር፣ ውሳኔአቸው ከተለመዱ ማህበራዊ አስተሳሰቦች ተገዥ ከሆነ ግላዊ ምክንያትና ይሉኝታ ይበልጥ ነጻ ይሆናሉ››፡፡ ‹‹ጥንዶች በጋራ ምክርና ጥረት ውሳኔ ያደርጋሉ፡፡ ስለዚህ፣ ሁለቱም የራሳቸውንና አስቀድመው የተወለዱትንም ሆነ ወደፊት የሚወለዱ ልጆቻቸውን ደህንነት በአስተውሎት ግምት ውስጥ ያስገቡ፡፡ ለዚህ ስሌት ደግሞ የዘመኑን ቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ ሁኔታዎች እንዲሁም የኑሮ ሁኔታቸውን ማገናዘብ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በመጨረሻም፣ የቤተሰብ ቡድንን፣ የዓለማዊ ኅብረተሰብንና የራስዋን የቤተክርስቲያንን ፍላጎቶች መረዳት አለባቸው፡፡ በስተ መጨረሻ በእግዚአብሔር ፊት ይህን ዳኝነት የሚሰጡት ወላጆች ራሳቸው እንጂ ሌላ ማንም አይደለም››፡፡ በተጨማሪ፣ “ ‘በተፈጥሮ ሕግጋትና በተዋልዶ ሁኔታ› ላይ የተመሠረቱ ዘዴዎችን መጠቀም ( ሁማኔ ቪቴ፣ 11) ሊበረታታ ይገባል። ምክንያቱም “እነዚህ ዘዴዎች የጥንዶቹን አካላዊ ክብር የሚጠብቁ፣ በእነርሱም መካከል ርኅራኄን የሚያበረታቱና የእውነተኛ ነጻነት ትምህርትን የሚደግፉ ናቸው’ (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ፣ 2370)፡፡ ስለዚህ፣ ልጆች የእግዚአብሔር ድንቅ ስጦታና ለወላጆችና ለቤተክርስቲያን የደስታ ምንጭ ስለ መሆናቸው የበለጠ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፡፡ በእነርሱ አማካይነት ጌታ ዓለምን ያድሳል”።

ምንጭ፡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርእስ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 218-221 ላይ የተወሰደመሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።
 

09 November 2024, 17:07