የመጀመሪያዎቹን የጋብቻ ዓመታት ስለ ማላመድ የሚገልጹ አንዳንድ ምንጮች
የሲኖዶሱ አባቶች እንዳመለከቱት፣ የመጀመሪያዎቹ የጋብቻ ዓመታት ጥንዶች የትዳር ሕይወትን ተግዳሮቶችና ትርጉም በይበልጥ የሚያውቁበት ዋናና አሳሳቢ ወቅት ነው። ስለሆነም፣ ለጥንዶቹ የሚሰጠው ምክር ከምሥጢረ ተክሊል ሥነ ሥርዓት ብቻ የዘለለ መሆን ይኖርበታል (ፋሚሊያሪስ ኮንሶርሲዮ፣ ክፍል 3)። በዚህ ረገድ፣ ተሞክሮ ያላቸው ጥንዶች የሚጫወቱት ትልቅ ሚና አላቸው። ቁምስና እነዚህን የመሰሉ ልምድ ያላቸው ጥንዶች፣ በማኅበራት፣ በቤተክርስቲያን እንቅስቃሴዎችና በአዳዲስ ማኅበረሰቦች ትብብር፣ ወጣት ባለትዳሮችን የሚረዱበት ስፍራ ነው። ወጣት ተጋቢዎች ታላቅ የልጆች ስጦታን ለመቀበል ዝግጁ እንዲሆኑ ሊበረታቱ ይገባል። ስለ ቤተሰብ መንፈሳዊነት፣ ስለ ጸሎትና በእሁድ መሥዋዕተ ቅዳሴ ስለ መሳተፍ አስፈላጊነትም ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል። ጥንዶችም በመንፈሳዊ ሕይወት ለማደግና ሕይወት ለሚጠይቀው የጋራ ጥቅም ለመሥራት አዘውትረው እንዲገናኙ መበረታታት ይኖርባቸዋል።
ሥርዓተ አምልኮዎች፣ መንፈሳዊ ተግባራት በተለይ በጋብቻ ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ ለቤተሰብ የሚደረጉ ሥርዓተ አምልኮዎች፣ ጸሎቶችና መሥዋዕተ ቅዳሴ በቤተሰብ አማካይነት ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት በዋና ምክንያትነት ተጠቃሽ ናቸው”። ይህ ሂደት በእርግጥ ጊዜ ይወስዳል። ፍቅር ደግሞ ጊዜና ቦታ ይፈልጋል፤ ሌላው ነገር ሁሉ በሁለተኛ ደረጃ የሚታይ ነው። ስለ አንዳንድ ነገሮች ለመወያየት፣ ለመረጋጋትና ለመተቃቀፍ፣ አብሮ ለማቀድ፣ እርስ በርስ ለመደማመጥና ዐይን ለዐይን ለመተያየት፣ እርስ በርስ ለመደናነቅና ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር ጊዜ ያስፈልጋል። አንዳንድ ጊዜ የኅብረተሰባችን የጥድፊያ ሩጫና የሥራ ቦታ ጫና ችግር ይፈጥራሉ። በሌላ ጊዜ ደግሞ፣ አንድ ክፍል ውስጥ እየኖሩ ነገር ግን አንዱ የሌላውን መኖር እንኳ የማያውቅበትና በጋራ የሚያሳልፉት ጥሩ ጊዜ ያለመኖር ችግር አለ። ስለዚህ፣ ወጣት ወይም ለችግር የተጋለጡ ጥንዶች እነዚያን ወቅቶች በጥሩ ሁኔታ እንዲያሳልፉ፣ ትርጉም ያለው የጸጥታ ጊዜ እንዲጋሩና እርስ በርስ እንዲቀራረቡ ለመርዳት የሐዋርያዊ ሥራ ሠራተኞችና የባለትዳሮች ቡድኖች የተለያዩ ዘዴዎችን መቀየስ ይኖርባቸዋል።
ይህን እንዴት ማድረግ እንደሚገባቸው የተረዱ ጥንዶች ጠቃሚ የመሰሉአቸውን አንዳንድ ተጨባጭ ምክረ ሐሳቦች ሊያቀርቡ ይችላሉ፤ ለምሳሌ፣ ትርፍ ጊዜን ፣ ከልጆች ጋር የመዝናኛ ወቅቶችን፣ ዋና ዋና ሁኔቶች የማክበሪያ የተለያዩ መንገዶችን፣ እንዲሁም ለመንፈሳዊ እድገት የሚረዱ አጋጣሚዎችን እንዴት በጋራ ማሳለፍና ማቀድ እንደሚቻል ልምዳቸውን ማካፈል ይችላሉ። እንደዚሁም እነዚህ ወቅቶች ለወጣት ጥንዶች ትርጉም ያላቸውና አስደሳች እንዲሆኑ ለማድረግና ተግባቦታቸውን ለማሻሻል የሚጠቅም እርዳታ መለገስ ይችላሉ። ይህም በተለይ የጋብቻ ተሐድሶ በሚደበዝዝበት ደረጃ እጅግ አስፈላጊ ነው። ጥንዶች ጊዜያቸውን እንዴት በጋራ ማሳለፍ እንዳለባቸው ካላወቁ፣ አንዳቸው ወይም ሁለታቸውም ራሳቸውን በኤሌክትሮኒክ መዝናኛ መሣሪያዎች ውስጥ ወደ መደበቅ፣ ሌሎች የቀጠሮ ምክንያቶችን ወደ መፈለግ፣ የሌላውን ሰው እቅፍ ወደ መሻት፣ ወይም ምቾት የማይሰጥ ቅርበትን መሸሻ አማራጮችን ወደ መመልከት ሊያዘነብሉ ይችላሉ።
ወጣት ጥንዶች ዕለታዊ ሁኔታዎችን በመጋራት ጤናማ የቅርርብ ስሜትና መረጋጋት የሚፈጥር የዘወትር ልምድ እንዲያዳብሩ ሊበረታቱ ይገባል። እነዚህም ልምዶች ጠዋት መሳሳምን፣ ምሽት ላይ ደህና እደሩ መባባልን፣ ወደ ቤት የሚመለሰውን ሰው ደጅ ጠብቆ መቀበልን፣ አብሮ ሽርሽር መሄድንና በቤተሰብ የዕለት ተዕለት ሥራ መሳተፍን ያካትታሉ። ይህም ከተለመደው ሁኔታ ወጣ ብሎ ጊዜን በመዝናናት ለማሳለፍና የቤተሰብ ዓመታዊ ክብረ በዓላትንና ልዩ ሁነቶችን በደስታ ለማክበር ይረዳል። የእግዚአብሔርን ስጦታዎች የምንንከባከብባቸውና ለሕይወት ያለንን ጉጉት የምናድስባቸው እነዚህን የመሰሉ ወቅቶች ያስፈልጉናል። መደሰት እስከቻልን ድረስ ፍቅራችንን ለማቀጣጠል፣ ከድግግሞሽ ነጻ ለማድረግና እያንዳንዱን ቀን በተስፋ ለመሙላት እንችላለን።
እኛ ጳጳሳት በእምነት እንዲያድጉ ቤተሰቦችን ማበረታታት አለብን። ይህም ማለት አዘውትረው ንስሐ እንዲገቡ፣ በመንፈሳዊ አቅጣጫ እንዲጓዙና አልፎ አልፎ ሱባኤ እንዲገቡ ማበረታታት ማለት ነው። እንዲሁም ‹‹አብሮ የሚጸልይ ቤተሰብ አብሮ ይኖራል›› እንዲሉ በሳምንት ውስጥ የቤተሰብ ጸሎት እንዲኖር ማበረታታት ማለት ነው። የሕዝባችንን ቤቶች ስንጎበኝ፣ የቤተ ሰብ አባላትን ሁሉ መሰብሰብና ቤተሰቡን ለጌታ አሳልፎ በመስጠት ለእርስ በርስ አጭር ጸሎት ማድረግ ይኖርብናል። እያንዳንዳቸው የሚሸከሙት የየራሳቸው ምሥጢራዊ መስቀሎች ስላሏቸው፣ ከእግዚአብሔር ጋር ለብቻቸው የሚጸልዩበትን ጊዜ እንዲያገኙ ጥንዶችን ማበረታታት ጠቃሚ ነው። እኛስ ብንሆን ችግሮቻችንን ለምን ለእግዚአብሔር አንነግረውም? ፈውስንና በታማኝነት ለመኖር የሚያስፈልገንን እርዳታ እንዲሰጠን ለምን አንለምነውም? የሲኖዶሱ አባቶች እንዳመለከቱት፣ “የእግዚአብሔር ቃል ለቤተሰብ የሕይወትና የመንፈሳዊነት ምንጭ ነው። በቤተሰብ ውስጥ የሚደረግ ማንኛውም ሐዋርያዊ ሥራ ቤተክርስቲያን በጸሎት መንፈስ በምታነበው መጽሐፍ ቅዱስ አማካይነት፣ ሰዎችን የቤት ውስጥ ቤተክርስቲያን አባላት ሆነው እንዲቀረጹና እንዲታነጹ የሚረዳ መሆን አለበት። የእግዚአብሔር ቃል በግለሰብ ሕይወት ውስጥ የምስራች ቃል ብቻ ሳይሆን የጥበብ መመዘኛና ጥንዶችና ቤተሰቦች የሚያጋጥሙአቸውን የተለያዩ ተግዳሮቶች መለያ ብርሃን ነው” ።
ምንጭ፡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርእስ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 223-227 ላይ የተወሰደመሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።
አዘጋጅ አባ ዳንኤል ኃይለ