የአሜሪካ የ 2024 (እ.አ.አ) ምርጫ የምሽት ዝግጅት የአሜሪካ የ 2024 (እ.አ.አ) ምርጫ የምሽት ዝግጅት  (ANSA)

የአሜሪካ ካቶሊክ ጳጳሳት ለአንድነት እና አዲስ ለተመረጡት መሪዎች ጸሎት አቀረቡ

የአሜሪካ የዜና አውታሮች ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫን እንደሚያሸንፉ በመግለጽ ላይ በነበሩበት ወቅት ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቆይታ ያደረጉት የአገሪቱ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቲሞቲ ብሮሊዮ፥ ጉባኤው ከሁሉም በላይ ለአደጋ የተጋለጡትን፣ ገና ያልተወለዱትን፣ የድሆችን እና የስደተኞችን ሰብዓዊ ክብር ለማስጠበቅ እንደሚፈልግ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

አሜሪካውያን ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በወጡበት ማግሥት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቲሞቲ ብሮሊዮ ጳጳሳቱ ለተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና በብሔራዊ፣ በክልል እና በአከባቢ ደረጃ ሕዝቡን ወክለው ለተመረጡት አባላት በሙሉ ጸሎት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቲሞቲ ብሮሊዮ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ከየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ጋር እንደማትተባበር ገልጸው ካቶሊክ ጳጳሳት አዲስ ከተመረጡት ተወካዮች ጋር ለጋራ ጥቅም ተባብረው ለመሥራት ከልብ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

“ክርስቲያኖች እና አሜሪካውያን እንደመሆናችን መጠን ምንም እንኳን በሕዝብ ፖሊሲ አተግባበር ላይ ባንስማማም በበጎ አድራጎት ሥራ፣ በሰብዓዊ ክብር ማስጠበቅ እና በግብረገብ እርስ በርስ የመተሳሰብ ግዴታ አለብን” ብለዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ብሮሊዮ በተጨማሪም፥ የአሥር ግዛቶች ነዋሪዎች ፅንስ ማስወረድን ለመከልከል ወይም ለመፍቀድ በክልላዊ ሕገ መንግሥት ማሻሻያዎች ላይ ድምጽ በሰጡበት ወቅት የአሜሪካ ካቶሊክ ጳጳሳት ፅንስን ጨምሮ ሁሉንም የሰው ልጅ መብት ለማስከበር ጥረት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

“አሜሪካ ውስጥ በዲሞክራሲያዊ ሥራዓት ውስጥ በመኖራችን ዕድለኞች ነን” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ብሮሊዮ፥ ዜጎች ፕሬዚዳንታቸውን ለመምረጥ ምርጫ ማካሄዳቸውን ተናግረው፥ ፕሬዚዳንት ትራምፕን እና ሕዝብን በመወከል ቅስቀሳ ላደረጉት የብሔራዊ፣ ክልላዊ እና የአካባቢ ባለስልጣናት “እንኳን ደስ አላችሁ!” ካሉ በኋላ የቅስቀሳ ሂደቱ ተጠናቆ ወደ አስተዳደር መሸጋገራቸውን ተናግረዋል።

ከአንድ መንግሥት ወደ ሌላኛው በሰላማዊ መንገድ ለመሸጋገር በመቻላችን ደስተኞች መሆናቸውን ገልጸው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንም ሆነ የጳጳሳት ጉባኤ ከየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ጋር ጥምረት እንደሌለው አስረድተው፥ ማንም ዋይት ሃውስን ቢይዝ ወይም በካፒቶል ሂል አብላጫውን ወንበር ቢይዝ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮዎች የማሳይቀር መሆኑን ተናግረዋል።

“አሜሪካ በብዙ ስጦታዎች የተባረከች እንደመሆኗ ከድንበራቸው ውጭ ላሉትም ጭምር ዕርዳታ ለማድረግ መነሳሳት ይገባል” ብለው፥ “ለተመራጩ ፕሬዚዳንት ትራምፕ እና ማኅበራዊ ሕይወትን የሚጋሩት ባለ ሥልጣናት የወከላቸውን ሕዝብ ለማገልገል የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት እንዲወጡ እንጸልይ” ብለዋል።

“የሁሉ ሰው የጋራ ተጠቃሚነት ለማስጠበቅ እና በተለይም በመካከላችን ገና ያልተወለዱትን፣ የድሆችን፣ በእንግድነት የመጡትን፣ የአረጋውያንን፣ የአቅመ ደካሞችን እና የስደተኞችን ሰብዓዊ ክብር ማጎልበት እንድንችል የእናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት እንለምን” ብለዋል።

“በእርግጥ በመሠረታዊነት ዋነኛ ትኩረታቸው የሰው ልጅ ክብር ነው” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቲሞቲ ብሮሊዮ፥ “የሰው ልጅ ከማኅፀን እስከ መቃብር ድረስ ሁሉን ቻይ በሆነው በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጠረ” የሚለውን ሐረግ እንደሚያከብሩት ገልጸዋል።

“አሜሪካ ሃብታም ሀገር በመሆኗ ተባርከናል” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቲሞቲ ብሮሊዮ፥ በኅብረተሰቡ መካከል ያለውን የድሃ ማኅበረሰብ ችግር መፍታት እንዳለባቸው እና በአንዳንድ ትላልቅ የአሜሪካ ከተሞች ውስጥ መጠለያ የሌላቸው ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነ በማስታወስ እነዚህን ስጋቶች እና ችግሮች ከሥር መሠረቱ መቅረፍ የሁሉ ሰው ሃላፊነት መሆኑን እንደሚገነዘቡት ተናግረዋል።

እንደ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት በአገሪቱ ያለው የስደተኛ ሕጎች እንዲሻሻሉ ለአሥርተ ዓመታት ሲወተውቱ መቆየታችን በማስታወስ፥ የተበላሸውን ሥርዓት ለማስተካከል እና ለሰዎች ፍላጎት ተገቢ ምላሽ ለመስጠት አንድ ነገር ማድረግ እንደሚቻል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ከዚህ ጋር ተዳምሮ ሰዎች የሚሰደዱባቸውን አገራት መርዳት ኃላፊነታቸው እንደሆነ ተናግረው፥ ብዙ ጊዜ ሰዎች ከትውልድ አገራቸው የሚሰደዱት በድህነት እና ሌሎች አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ሲገኙ እንደሆነ ተናግረው፥ ውጤታማ የለውጥ መንገድ የሚሆነው እነዚያ አገራት ራሳቸውን እንዲያሻሽሉ መርዳት እንደሆነ አስረድተዋል።

ፅንስ ማስወረድን ሕጋዊ ካደረገው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ መጀመሪያ አንስቶ በሰው ሕይወት ላይ የሚደርሰውን አደጋ ማስወገድ እንደሚገባ ድምጽ ማሰማታቸውን እና በተቻለ መጠን በዚህ መንገድ ለመሟገት መሞከራቸውን ገልጸው፥ አስፈላጊው መንገድ ያልተወለደ ሕፃን በሕይወት የመኖር መብት እንዳለው ሰዎችን ማሳመን እንደሆነ ተናግረዋል።

አሜሪካ ውስጥ ውርጃን የሚፈቅዱ ሕጎችን ያጸደቁ ሰባት ግዛቶች መኖራቸውን ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቲሞቲ ብሮሊዮ፥ ተግዳሮቱ በእነዚያ ግዛቶች ውስጥ የሚገኙ ጳጳሳት ብቻ ሳይሆን የአገሪቱ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ጭምር እንደሆነ በመግለጽ የሰው ልጅ ክብርን በግንባር ቀደምትነት ለማቆየት የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚቀጥሉበት አስረድተዋል።

በኅብረተሰባቸው ውስጥ ያለውን ሁከት ሲመለከቱት፥ “ማን በሕይወት መኖር እንደሚችል ወይም ማን መቼ ሊሞት እንደሚችል ሰዎች መወሰን ይችላሉ” ከሚለው እውነታ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው እና ይህ ደግሞ የሰው ልጅ ክብርን የሚቀንስ በመሆኑም ሰዎች የወንጌል ብርሃን እንዲያዩ የማስተማር እና የማሳመን ሃላፊነት እንዳለባቸው የአሜሪካ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቲሞቲ ብሮሊዮ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።

 

07 November 2024, 12:20