ካርዲናል ቡስቲሎ፥ “የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የኮርሲካ ጉብኝት ‘የገና ስጦታ’ ነው!” ሲሉ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ካርዲናል ቡስቲሎ በቃለ ምልልሳቸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሚቀጥለው ታኅሳስ ወር በኮርሲካ ደሴት የሚያደርጉት የአንድ ቀን ሐዋርያዊ ጉብኝት “ውድ የገና ስጦታ” ሲሉ ገልጸው፥ የደሴቲቱ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ይህን ልዩ ስጦታ የምትቀበለው “እንደ ልዩ መብት ሳይሆን ትውስታችንን ለማክበር እና የወደፊት ሕይወታችንን ለማበረታታት ነው” ብለዋል። ከዚህም ጋር የቅዱስነታቸውን የሐዋርያዊ ጉብኝት ዓላማ እና ስለ ኮርሲካ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን የእምነት ጥንካሬን በማስመልከት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የሜዲትራኒያን ባሕር አካባቢ አገራት ከሆኑት ሲሲሊ፣ ሰርዲኒያ፣ ስፔን እና ፈረንሳይ ከመጡት ጳጳሳት ጋር በታወቁት ሃይማኖታዊ ወጎች ላይ ጉባኤ ማድረጋቸውን የገለጹት ካርዲናል ቡስቲሎ፥ “በየአገሮቻቸው የሚገኙ ታዋቂ ሃይማኖታዊ ወጎች የያዟቸውን የራስ ማንነትን እና ገጠመኞችን በመካከላቸው ለመክርፋፈል የሚፈልጉበት ጊዜ እንደሆነ ተናግረው፥ “ሥነ-መለኮታዊ ይዘትን ማምጣት አስፈላጊ ነው፤ አንዳንድ ወጎችን እንደ ቀላል ከመመልከት ይልቅ ቅድመ አያቶቻችን ባስተላለፉት በእነዚህ ወጎች አማካይነት ወንጌልን በመስበካችን ዕድለኞች ነን” ብለዋል።
እነዚህ ዘዴዎች ሐዋርያዊ ተልዕኮውን እንደሚያበረታቱ የገለጹት ካርዲናል ቡስቲሎ፥ ስለ ወንጌል ተልዕኮ ሲታሰብ አንዳንድ ጊዜ ስለ ስልቶች እንደሚያስቡ እና የአጥቃቀም መንገዶችን ማጥናት እንዳለባቸው ተናግረው፥ ወጎቹ ቀላሉ እና ልዩ ስልቶችን የማይጠይቁ፣ ነገር ግን ወደ ሕዝቡ ዘንድ መሄድን፣ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያላቸውን አክብሮት መግለጽ፣ በኅብረት መዘመር እና መጓዝ፣ አማኞች መሆናቸውን ብቻ መናገር እንዳለባቸው የሚያሳስቡ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የወንጌል ተልዕኮ ሁለት ገጽታዎች እንዳሉት የገለጹት ካርዲናል ቡስቲሎ፥ እነርሱም አስተንትኖ እና ተስማሚ ምላሽ መስጠት እንደሆኑ ተናግረው፥ ቀጥሎም ተልዕኮውን አስቀድመው በነበሩ ታዋቂ ወጎች አማካይነት ማከናወን የጉባኤው ትኩረት መሆኑን አክለው አስረድተዋል።
በኮርሲካ የምትገኝ ቤተ ክርስቲያናቸው ከካቶሊካዊ ወጎች ጋር በቅርበት የተሳሰረች መሆኗን የገለጹት ካርዲናል ቡስቲሎ፥ ኮርሲካ ትናንሽ ማኅበረሰቦች የሚኖሩባት ደሴት ስለሆነች ከቅዱሳን፣ ከሰማዕታት እና ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጋር የተገናኙ ወጎችን ጠብቃ ማቆየቷን ገልጸዋል።
ቤተ ክርስቲያናቸው ባሕላዊ፣ መንፈሳዊ እና ሃይማኖታዊ ገጽታዋን የጠበቀች መሆኗን ተናግረው፥ በውጫዊ ወጎች ላይ ብቻ መቆየት ሳይሆን ነገር ግን እነዚህን ወጎች በተሟላ ሁኔታ እንዴት መኖር እንደሚገባ መመልከት እንደሚያስፈልግ በማስረዳት “የወንጌል መልዕክትም ይህ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
“ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ሁለት ሁለት ሆናችሁ ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ’ ይለናል” ያሉት ካርዲናል ቡስቲሎ፥በዚህም ከሌሎች ጋር መገናኘት እንደሚገባ መጋበዙን እና በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ከሌሎች ጋር መገናኘት እንደሚቻል፣ ከሁሉም የሕይወት ዓይነት የተውጣጡ ሰዎች፣ የቀኝ እና የግራ ክንፍ የፖለቲካ ደጋፊዎች፣ ጓደኛሞች እና ጠላቶችም በእምነት አንድ መሆናቸውን አስረድተዋል።
እነዚህ ወጎች በአገራቸው እና በሀገረ ስብከታቸው ውስጥ ሰዎችን አንድ እንደሚያደርጓቸው ተናግረው፥ በከተማቸው ጎዳናዎች ላይ ሳይቀር የቁምስና ካኅን ወይም ጳጳስ ይህን እንቅስቃሴ እንዲቀላቀሉት እና እንዲያከብሩት ሕዝቡ የሚጠብቅ መሆኑን አስረድተዋል።
የኮርሲካ ደሴት ካቶሊካዊ ምዕመናን ከዋናው የፈረንሳይ አገር ካቶሊካዊ ምዕመናን ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሲገልጹ፥ በሁለቱ መካከል ያለው ግንኙነት የተረጋጋ መሆኑን ተናግረው፥ የሀገረ ስብከታቸው ካቶሊካዊ ምዕምናን ከሲቪል ባለስልጣናት ጋር፣ ከፓርላማ አባላት፣ ከከንቲባ አባላት ጋር ባላቸው ግንኙነት ውስጥ ብዙ ችግር እንደማይገጥማቸው አስረድተዋል። እያንዳንዱ በከተማው የራሱን ኃላፊነት በመወጣት በተረጋጋ መንፈስ እና ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ሕይወቱን እንደሚኖር እና ለሁሉ የሚሆን የሕዝብ ደህንነትን እንደሚፈልግ አክለው ገልጸዋል።
በምድራዊ አቀማመጧ የኮርሲካ ደሴት በስልታዊ ቦታ ላይ እንደሚትገኝ የገለጹት ካርዲናል ቡስቲሎ፥ ደሴታቸው ሰርዲኒያ ለተባለች የጣሊያን ደሴት ቅርብ መሆኗን ተናግረው፥ ባሕሎቻቸውን ከደሴታቸው ውጪ ማስፋት አስፈላጊ መሆኑን በማስረዳት፥ “በሌሎች አካባቢዎች ካሉት ሰዎች ጋር የተገናኘ ደኅነቱን የጠበቀ ሰላማዊ ሕይወትን ወደ ሲቪል ባለስልጣናት እና ወደ ሃይማኖት መሪዎች ማስተላለፍ መቻል ጥሩ የሆነው ለዚህ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
“በሜዲትራኒያን ባሕር አካባቢ አገራት ውስጥ እንኳን ብዙ ጦርነቶች መኖራቸውን እናያለን” በማለት የተናገሩት ካርዲናል ቡስቲሎ፥ ሰላማዊ፣ ወንድማዊ እና የተረጋጋ ሕይወትን በወጋቸው አማካይነት እንዴት ማስተላለፍ እንደሚችሉ ጠቀው፥ በዚህም ምክንያት ከሲቪል እና ከቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጋር መወያየት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
“ዛሬ ተቋማዊ ጠላቶች መሆን አንችልም” ያሉት ካርዲናል ቡስቲሎ በማከልም “ከሕዝባችን ጋር የምንቆይ ከሆነ ማኅበረሰባችንን ሳንዘነጋ የሚጠቅመውን ነገር ለመሥራት ያለንን ቁርጠኝነት ለማረጋገጥ ኃላፊነት ሊኖረን ይገባል” ብለዋል።
እያንዳንዱ ባለስልጣን የራሱ ሚና ቢኖረውም ማኅበረሰቡ የራሱ እሴቶች፣ ሃሳቦች እና የጋራ ራዕይ እንዳለው የሚያሳስብ እና ለደህንነት የሚተጉ የሲቪል ባለስልጣናት እና ስለ ነፍስ የሚያስቡ መንፈሳዊ መሪዎች አንደሚያስፈልጉት አስረድተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ታኅሳስ 6/2017 ዓ. ም. በኮርሲካ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት መልካም የብርሃነ ልደቱ ስጦታ እንደሚሆን እና እግዚአብሔርም መልካም እንደሆነ የገለጹት ካርዲናል ቡስቲሎ፥ “ይህን ስጦታ እንደ መብት ሳይሆን ነገር ግን የወደፊት ሕይወታችንን ለማነቃቃት የተሰጥ ሃላፊነት አድርገን መመልከት ያስፈልጋል” ብለዋል።