አባ ፓቨል ፕታዝኒክ፥ በቅዱስ ቶማስ አኳይናስ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ (አንጀሊኩም) ተገኝተው ንግግር ሲያደርጉ አባ ፓቨል ፕታዝኒክ፥ በቅዱስ ቶማስ አኳይናስ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ (አንጀሊኩም) ተገኝተው ንግግር ሲያደርጉ 

በሮም የሚገኙ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲዎች አዲስ ትውልድን የሚያበረታቱ ዝግጅቶችን አቀረቡ

“የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ቀናት” በሚል መጠሪያ በሮም የሚገኙ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲዎች ከኅዳር 17-20/2017 ዓ. ም. ለአራት ቀናት የሚቆዩ የመጀመሪያ ዝግጅቶቻቸን አቅርበዋል። በቅርቡ በተሰጠው ማብራሪያ መሠረት፥ በሮም የሚገኙ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲዎች በ “ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ቀናት” ዝግጅቶችን እንደሚያቀርቡ አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅድስት መንበር የባሕል እና የትምህርት ጉዳዮች ጳጳሳዊ ምክር ቤት አስተባባሪነት ዝግጅቱን ያቀረቡት በቫቲካን የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ፋውንዴሽን፣ በፖላንድ ክራኮቪያ የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ እና በሮም የሚገኝ የቅዱስ እስታንስላውስ ቁምስና መሆናቸው ታውቋል።ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ ኅዳር 18/2017 ዓ. ም. ባቀረቡት ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው ለዝግጅቱ ተካፋዮች ሰላምታ አቅርበዋል።

‘የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ቀናት’ ዝግጅት ተነሳሽነቱን ያገኘው ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በየዓመቱ በክራኮቪያ ከሚካሄድ ምሁራዊ የካሮል ዎይቲላ አስተምህሮ እንደሆነ ታውቋል።አዘጋጆቹ እንደገለሱት፥ ዝግጅቱ በሮም በሚገኙ ሦስት ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲዎች ማለትም በቅዱስ ቶማስ አኳይናስ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ (አንጀሊኩም)፣ በቅዱስ መስቀል ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ እና በጳጳሳዊ ግረጎሪያን ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚካሄድ ታውቋል። የዘንድሮው ዝግጅት መሪ ሃሳብ፥ “እምነት እና ምክንያታዊነ በቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ አስተሳሰብ” የሚል እንደሆነ ታውቋል።

የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ውርስ ለዘመናችን
በቅዱስ ቶማስ አኳይናስ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ባልደረባ የሆኑት እህት ሜሪ አንጄላ ዎከርስ፥ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በተከራከሩበት በአንጄሊኩም ዩኒቨርሲቲ እነዚህን ቁልፍ ርዕሦች በመቅረባቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

እህት ሜሪ አንጄላ በንግግራቸው፥ “‘እነዚህ የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ቀናት’ በእርሳቸው ትሩፋት ላይ አብረን እንድናሰላስል፣ ማስተዋልን እንድናሳድግ እና የእርሳቸውን ግንዛቤዎች በዘመናችን እንድንጠቀማቸው ተጨማሪ ዕድል ይሰጡናል” ሲሉ አክለዋል።

በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የነበሩት ሪቻርድ ስዊንበርን ርዕሡን መሠረት በማድረግ በእግዚአብሔር ህልውና እና በእምነት ጉዳዮች ላይ የውይይት ሃሳቦችን አቅርበዋል። ፕሮፌሰር ሪቻርድ ስዊንበርን ርዕሡን መሠረት በማድረግ ያቀረቡት ገለጻ በተማሪዎች መካከል ሰፊ የውይይት ዕድል የፈጠረ ሲሆን፥ መልካም ሥራዎች በመዳን አውድ ውስጥ ስላለው ሚና እንዲሁም በሰው ሕይወት ውስጥ መልካምን ማድረግ ወይም ላለማድረግ መነሳሳትን በተመለከተ ጥያቄዎችን አስነስቷል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ ከወጣቶች ጋር ያላቸው ግንኙነት
“በተማሪዎች የተነሱት ጥያቄዎች ወጣቶች ስለ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሥነ-መለኮታዊ እና ፍልስፍናዊ አስተሳሰብ ጥልቅ እና ልባዊ ፍላጎት እንዳላቸው ያሳያል” ሲሉ በቫቲካን የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ፋውንዴሽን ፕሬዝዳንት አባ ፓቨል ፕታዝኒክ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸው፥ የ “ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ቀናት” በሮም እንዲዘጋጅ የተደረገበት ዓላማ ወጣቶች የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ትምህርት እና ትሩፋት እንዲያጠኑ ለማነሳሳት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

በቅዱስ ቶማስ አኳይናስ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ (አንጀሊኩም) በተዘጋጀው ጉባኤ ላይ በሉብሊን የዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ የተጋበዙት ፕሮፌሰር ጄሰክ ዌጅቲሲያክ ስለ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የእምነት አስተሳሰብ ተግባራዊ ገጽታ ላይ ንግግር አድርገዋል።

ካሮል ዎይቲላ (ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ) ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳስና ከመመረጣቸው በፊት በሉብሊን ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ምግባር ፋካልቲ ሊቀ መንበር ሆነው ማገልገላቸውን የገለጹት ፕሮፌሰር ጄሰክ ዌጅቲሲያክ፥ በጉባኤው ላይ ያቀረቡት ንግግራቸው ያተኮረው በካሮል ዎይቲላ የመጀመሪያዎቹ ጽሑፎች ላይ እንደሆነ ገልጸው፥ ይህም በሉብሊን ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ በነበሩበት ወቅት ከእኩዮቹ ጋር በመወያየት ያዳበሩት ፍልስፍናዊ አመለካከት እንደሆነ አስረድተዋል።

ፕሮፌሰር ጄሰክ ዌጅቲሲያክ አክለውም፥ ካሮል ዎይቲላ በሉብሊን ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ተጽዕኖ ፈጣሪ በነበሩበት ወቅት ድጋፍ በማድረግ ረገድ ጓደኞቻቸው ሚና መጫወታቸውን ገልጸው፥ “ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ታላቅ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ብቻ ሳይሆኑ ታላቅ አሳቢም መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም” ብለዋል.

በጉባኤው የተገኙ ታዋቂ ምሁራን
በጉባኤው ንግግር ካደረጉት መካከል ፕሮፌሰር ሪቻርድ ስዊንበርን (የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ)፣ ፕሮፌሰር ሃና ባርባራ ገርል-ፋልኮቪትዝ (የ2021 ራትዚንገር ሽልማት አሸናፊ)፣ ፕሮፌሰር ሃና ሱቹካ (የፖላንድ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር እና በቅድስት መንበር የቀድሞ የፖላንድ አምባሳደር)፣ አባ ፌዴሪኮ ሎምባርዲ SJ (የቀድሞው የቫቲካን ቃል አቀባይ) እና ፕሮፌሰር ጄሰክ ዌጅቲሲያክ (ሉብሊን ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ) እንደሚገኙ ታውቋል።

በቫቲካን የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ፋውንዴሽን ፕሬዝዳንት አባ ፓቨል ፕታዝኒክ በንግግራቸው መደምደሚያ፥ “የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ አስተምህሮዎችን እንደገና ማየት ብቻ ሳይሆን በዘመናዊው ዓለምም የበለጠ ሊዳብሩ ይገባል” ሲሉ አስገንዝበዋል።

 

28 November 2024, 13:52