‘ዳይሌክሲት ኖስ’ የተሰኘው የር.ሊ.ጳ. ፍራንቺስኮስ ሃዋሪያዊ መልዕክት በዓለም ዙሪያ ለኢየሱስ ቅዱስ ልብ መሰጠትን ያስፋፋል ተባለ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ጥቅምት 30 ቀን 2017 ዓ.ም. የአሜሪካ ግዛት በሆነችው ኦሃዮ፣ ዌስተር-ቪል ከተማ በተካሄደው የቅዱስ ልበ ኢየሱስ ኮንግረስ ወይም ጉባኤ ላይ 1,200 ተሳታፊዎች ዝግጅቱን አስመልክቶ በተካሄደው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ የተሳተፉ ሲሆን፥ ይህ በዚህ ርዕስ የተዘጋጀ በዓለም የመጀመሪያ የሆነው ጉባኤ የተካሄደው በኢየሱስ ክርስቶስ ልብ ውስጥ ስላለው ሰብዓዊ እና መለኮታዊ ፍቅር የሚገልጸውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሃዋሪያዊ መልዕክት የሆነው ‘ዳይሌክሲት ኖስ’ መታተምን ተከትሎ እንደሆነ የጉባኤው አስተባባሪ የሆኑት አባ ጆናታን ዊልሰን ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።
ለጌታችን ቅዱስ ልብ መሰጠት ለኢየሱስ እና ለፍቅሩ መሰጠት ማለት እንደሆነ እና ኢየሱስ ለአባቱ እና ለእኛ ያለውን መለኮታዊ እና ሰብዓዊ ፍቅር ምልክት መሆኑ፥ ይህም ስለ እኛ ነፍሱን አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ የሆነውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ውስጣዊ ሕይወት ያመለክታል ተብሏል።
ከካህኑ በተጨማሪ ከቫቲካን ዜና ጋር ቆይታ የነበራቸው በኮሎምበስ የኦሃዮ ሀገረ ስብከት ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ኤርል ፈርናንዴዝ፣ ይህ ጉባኤ ለቅዱስ ልበ ኢየሱስ ከተሰጡ ጥቂት ጉባኤዎች አንዱ መሆኑን ጠቁመው፥ “በዚህ በዌስተርቪል ኦሃዮ በሚገኘው በቅዱሳን ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ በማዘጋጀታችን በጣም ደስ ብሎናል” በማለት ደስታቸውን ገልጸዋል።
ሃዋሪያዊ መልዕክቱ በቤተሰብ ሕይወት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ
ብጹዕ አቡነ ፈርናንዴዝ እንደተናገሩት ለቅዱስ ልበ ኢየሱስ የተሰጠው ጉባኤ በቅርቡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በፃፉት ‘ዳይሌክሲት ኖስ’ በተሰኘው መጽሐፋቸው እንደገና እንደታደሰ ገልጸው፥ ‘ይህ የብጹእነታቸው ሃዋሪያዊ መልዕክት የሆነው መጽሃፋቸው አስደናቂ እንደሆነ፥ ምክንያቱም ፅሁፉ በአብዛኛው ከቅዱሳት መጻሕፍት፣ ከቤተክርስቲያን አባቶች እና ከቀደምት ሊቃነ ጳጳሳት ጽሑፎች እንደተወሰደ፥ በተጨማሪም ለተለያዩ ቅዱሳን ቅርብ እንዲሆኑ እንደሚያደርጋቸው ጠቅሰው፥ ይህ ሁሉ ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር በተለይም ለቅዱስ ልቡ ያለንን ፍቅር ያጎለብታል ሲሉ አብራርተዋል።
“ሀገረ ስብከቱን ለማደስ እና ለማነቃቃት እየሰራን ነው” ያሉት ብጹዕ አቡነ ፈርናንዴስ፥ በተለይም የቅዱስ ልበ ኢየሱስ እና የንጽሕተ ንጹሐን ልበ ማርያም ምስሎች በየቤቱ የማድረግ ልምድ በኩል በርካታ ሥራዎችን እየሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የህይወታችን ማዕከል ማድረግ እና ከኢየሱስ ልብ የሚፈሰውን ምህረት የሚያንፀባርቁ ቤቶችን መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው በመግለጽ፥ “በዚህ መንገድ ቤተሰቦች ከወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው፥ በተለይም በእኛ ማህበረሰብ ውስጥ ከድሆች እና ችግረኞች ጋር በምሕረት ማደግ ይችላሉ” ሲሉ ገልጸዋል።
በቤት ውስጥ እምነትን ማጠናከር
የጉባኤው ምክትል አስተባባሪ የሆኑት የሰባት ልጆች እናት እና የቅዱስ ልበ ኢየሱስ ትስስር ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ኤሚሊ ጃሚኔት ይህ ጉባኤ ልዩ ትርጉም እንዳለው ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አፅንዖት ሰጥተው በመግለጽ፥ ‘ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ልብ ሰብዓዊ እና መለኮታዊ ፍቅር ላይ ተመርኩዘው ጳጳሳዊ መልዕክታቸውን እንደፃፉ’ ጠቅሰው፥ ከዚህም በላይ ዘንድሮ ቅድስት ማርጋሬት አላኮክ የተገለጠችበትን 350ኛ ዓመት እንደሚከበር አስታውሰዋል።
‘በርካታ ሰዎች ለመጸለይ፣ ንስሃ ለመግባት እና ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ብለው እዚህ አንድ ላይ ተሰብስቦ ማየት በጣም የሚያበረታታ ነው’ ያሉት ወይዘሮ ኤሚሊ፥ በእውነት የመታደስ ጊዜ እንደሆነ፣ የእንቅስቃሴው ዓላማ የኢየሱስን ቅዱስ ልብ ምስልን በየቤቱ ውስጥ ማድረግ የሰዎችን ልብ ለማደስ፣ ብሎም የቤተሰብን እምነት ለማጠናከር እንደሚረዳ ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል።
ምክትል አስተባባሪዋ በማከልም ይህ ተሞክሮ በቁጥር አናሳ መሆናችንን እንደሚያስታውሰን፥ ነገር ግን ፍቅር ፍቅርን ይወልዳልና ልባችንን ከክርስቶስ ጋር ስናገናኝ የምናገኘውን ጥንካሬ ያሳያል ብለዋል።
በዌስተርቪል የሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ ቁምስና ካህን የሆኑት አባ ጆናታን ዊልሰን ይህ የኢየሱስ ቅዱስ ልብ ጉባኤ ለ13ኛ ጊዜ የተካሄደ መሆኑን ገልጸው፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሶስተኛ ሃዋሪያዊ መልዕክት የሆነው ‘ዳይሌክሲት ኖስ’ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለቅዱስ ልበ ኢየሱስ ያላቸውን ቁርጠኝነት በማስፋፋት ረገድ ያላቸውን ጠንካራ ተሳትፎ እና ጉልህ አስተዋፅዖ በማጉላት አጠቃለዋል።