በሕመም የሚሰቃዩ ሕሙማንን በሕክምና ድጋፍ ማሳረፍ በሕመም የሚሰቃዩ ሕሙማንን በሕክምና ድጋፍ ማሳረፍ   (AFP or licensors)

የእንግሊዝ የሃይማኖት መሪዎች በእገዛ ራስን ማጥፋት የሚጻረር የጋራ ስምምነት ተፈራረሙ

ዌስት ሚኒስተር ፈውስ በሌለው ሕመም የሚሰቃዩ ሕሙማንን በሕክምና ድጋፍ ለማሳረፍ የሚያስችል አዋጅ ሊያወጣ ሲዘጋጅ በብሪታንያ ያሉ የሃይማኖት መሪዎች በረቂቅ ሕጉ ላይ ያላቸውን ጠንካራ ተቃውሞ በድጋሚ በማረጋገጥ ነፍስን ከማጥፋት ይልቅ የተሻለ እንክብካቤ ለማድረግ የሚያስችል የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የብሪታንያ ፓርላማ በ ‘እገዛ ራስን ማጥፋት’ በሚለው አዲስ አወዛጋቢ አዋጅ ላይ ዓርብ ኅዳር 20/2017 ዓ. ም. ድምጽ እንደሚሰጥበት ታውቋል።

በሌበር ፓርቲ የፓርላማ አባል በሆኑት ሊድቢተር የቀረበው ረቂቅ የአዕምሮ ብቃት ያላቸው እና ፈውስ በሌለው ሕመም የሚሰቃዩ ሰዎች በሁለት ዶክተሮች ፍቃድ እና በከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ውሳኔ ሕይወታቸው እንዲያልፍ ማድረግን ያስችላቸዋል። ጉዳዩ በብሪታንያ በተለይም በሃይማኖት ቡድኖች በኩል ሰፊ ክርክር እና ተቃውሞ ማስነሳቱ ይታወቃል።

ባለፉት ወራት የአገሪቱ ካቶሊክ ጳጳሳት ከሌሎች የእምነት መሪዎች ጋር በመሆን በዘጋጀው ሕግ ሥነ-ምግባራዊ፣ ተግባራዊ እና ማኅበረሰባዊ አንድምታ ላይ ስጋታቸውን ደጋግመው ገልጸዋል።

በዚህ ሳምንት በተደጋጋሚ በታዩት ስጋቶች፥ የእንግሊዝ እና የዌልስ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ካርዲናል ቪንሴንት ኒኮልስ፣ የለንደን የአንግሊካን ጳጳስ ሳራ ሙላሊ፣ የአይሁድ እምነት ዋና መምህር ኤፍሬም ሚርቪስን እና የመስጂዶች እና የኢማሞች ብሔራዊ አማካሪ ቦርድ ሰብሳቢ ኢማም ቃሪ አሲምን ጨምሮ በተለያዩ ዋና ዋና የሃይማኖት መሪዎች የጋራ ስምምነት መፈረማቸው ታውቋል።

መሞት “መብት” ወይስ “ግዴት”?
በተለይም ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች፣ አካል ጉዳተኞች እና በቂ ማኅበራዊ እንክብካቤ የሌላቸው አዛውንቶች ነፍሳቸው ያለ ጊዜ እንዲያልቅ ማድረግ የበደል እና የማስገደድ ጫና ሊሆንባቸው እንደሚችል ፈራሚዎቹ በድጋሚ አስጠንቅቀዋል

አሁን ያለው የሕግ ማዕቀፍ የተሻለ ጥበቃ እንደሚያደርግ እና ተመሳሳይ ሕግ ያወጡት ዳኞች ልምድ እንደሚያሳየው፥ “ተስፋ የተገባላቸው ጥበቃዎች ተጋላጭ እና የተገለሉ ሰዎችን ሁልጊዜ አይከላከሉም” ሲሉ ይከራከራሉ።

ከፍተኛ ጥራት ላለው የማስታገሻ እንክብካቤ ቅድሚያን መስጠት
እንደ የእምነት መሪዎች ገለጻ፥ የፓርላማ አባላት የታገዘ ሞትን ሕግ ከማውጣት ይልቅ ከፍተኛ ጥራት ላለው ማስታገሻ እንክብካቤ ቅድሚያ መስጠት አለባቸው” ብለው ይህም የገንዘብ እጥረት ሊያጋጥመው እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።

የካቶሊክ ሕክምና ማኅበር በተጨማሪም፥ የቀረበው ሕግ ለሕመም ማስታገሻ እንክብካቤ እና ዶክተሮች ከታካሚው ጋር ላላቸውው ግንኙነት አደገኛ እንደሚሆን ጠቁሞ፥ ይህም ለኅሊና ተቃውሞ ደካማ ጥበቃን እንደሚያደርግ እና በካቶሊክ የሚተዳደሩ እንክብካቤ መስጫ ተቋማት ሕጉን ሳይወዱ በግድ እንዲያከብሩት ሊገደዱ እንደሚችሉ ገልጿል። የብሪታንያ የሕክምና ማኅበር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2021 ጀምሮ በ ‘እገዛ ራስን ማጥፋት’ ላይ ገለልተኛ አቋም ይዞ ቆይቷል።

ሁለት የሠራተኛ ጉዳይ ሚኒስትሮች አዋጁን ተቃውመዋል
ረቂቅ ሕጉ በጠቅላይ ሚኒስትር ኬይር ስታርመር የተደገፈ ቢሆንም ከሁለት ቁልፍ የሠራተኛ ሚኒስትሮች፡ ጠንካራ የክርስትና እምነት ተከታይ እና የጤና ጉዳይ ዋና ጸሐፊ ዌስ ስትሪትዲንግ፣ እንዲሁም የእስልምና እምነት ተከታይ እና የፍትህ ጉዳይ ፀሐፊ ሻባና ማህሙድ ተቃውሞ ገጥሞታል። የሕዝብ አስተያየቶች እንደሚያመለክቱት አብዛኛው የብሪታንያ ዜጎች በማይድን ሕመም የሚያሰቃዩት ራስን በሕክምና ዕርዳታ ማጥፋትን የሚደግፉ ቢሆንም በጉዳዩ በጥንቃቄ እንደሚመለከቱት ታውቋል።

በ ‘እገዛ ራስን ማጥፋት’ የሚለው ይህ ተመሳሳይ የፓርላማ ክርክር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2015 ወዲህ የተካሄደ የመጀመሪያ ክርክር ሲሆን በወቅቱ 300 ለ 118 በሆነ ከፍተኛ ድምጽ ውድቅ መደረጉ ይታወሳል። ረቂቀ ሕጉ በመጀመሪያው ዙር የሚጸድቅ ከሆነ እስከ ጎርጎሮሳውያኑ 2025 ጸደይ ድረስ ተጨማሪ ክርክር ከተደረገበት በኋላ መጽደቅ እንዳለበት ይጠበቃል።

በዌስት ሚኒስተር ያለው ውሳኔ በስኮትላንድ ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር እንደሚችል እና ተመሳሳይ ሕግ በሊበራል ዲሞክራት የፓርላማ አባል ሊያም ማክ አርቱር እየታየ እንደሚገኝ ታውቋል።

 

28 November 2024, 19:33