ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኢሳኦ ኪኩቺ ዓመታዊ በዓሉን በመስዋዕተ ቅዳሴ ባከበሩበት ወቅት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኢሳኦ ኪኩቺ ዓመታዊ በዓሉን በመስዋዕተ ቅዳሴ ባከበሩበት ወቅት   (Archdiocese of Tokyo)

እጩ ተመራጭ ካርዲናል ኪኩቺ፡ ቤተ ክርስቲያን በተስፋ እና በአንድነት መጓዝ እንዳለባት አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርቡ ለካርዲናልነት ማዕረግ ካጯቸው 21 ካርዲናሎች መካከል አንዱ የሆኑት የቶኪዮ ከተማ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኪኩቺ፥ ቤተ ክርስቲያን በተስፋ እና በኅብረት መጓዝ እንዳለባት አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቶኪዮ የሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካቴድራል ባዘጋጀው ዓመታዊ በዓል ከዚህም ጋር በማያያዝ በምያንማር ካለች ቤተ ክርስቲያን ጋር ለአሥርተ ዓመታት የቆየውን አጋርነት የሚገልጽ “የምያንማር ቀን” መከበሩ ታውቋል።

ዕጩ ካርዲናል እና የቶኪዮ ከተማ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኢሳኦ ኪኩቺ ዓመታዊ ክብረ በዓሉን በማስመልከት እሑድ ኅዳር 8/2017 ዓ. ም. የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴ የመሩ ሲሆን፥ ከእርሳቸው ጋር የነበሩት በምያንማር የሎይካው ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ ሴልሶ ባሼዌ እና እንዲሁም በቶኪዮ ከተማ ውስጥ የሚኖር የምያንማር ማኅበረሰብ ሥነ-ሥርዓቱን ተካፍሏል።

የቶኪዮ ሊቀ ጳጳስ በጀርመን ከሚገኘው ከኮሎኝ ሀገረ ስብከት ጋር ባለው አጋርነት ላይ የተመሠረተውን የዚህ ወግ አመጣጥ እጩ ካርዲናል አቡነ ኪኩቺ አብራርተዋል። “‘የምያንማር ቀን’ የጀመረው በካርዲናል ሺራያናጊ ዘመን ነው” ያሉት ጳጳሱ፥ “ከዚያም የሊቀ ጳጳስ አቡነ ኦካዳ ጊዜን አልፎ እስከ ዛሬ ድረስ ቀጥሏል” ሲሉ ተናግረዋል።

የሀገረ ስብከቱን ቁርጠኝነት በማስመልከት እንደተናገሩት፥ በቶኪዮ የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን በምያንማር የዘርዓ ክኅነት ትምህርትን ለማሳደግ እና ለትምህርት ቤቱ ግንባታ የምታደርገውን የረዥም ጊዜ ጥረት አጽንዖት ሰጥተዋል። በማከልም በአገሪቱ የተካሄደውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለሚያንማር ሰላም እና መረጋጋት በመጸለይ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል።

“በምያንማር ያለው የፖለቲካ ሁኔታ አሁንም ያልተረጋጋ ነው” ሲሉ የተናገሩት የቶኪዮ ከተማ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኢሳኦ ኪኩቺ፥ ከካቴድራሉ እና ከመኖሪያቸው ተገደው እንዲወጡ የተደረጉት አቡነ ሴልሶ ዛሬ ከተፈናቀሉት ሰዎች ጋር እንደሚኖሩ ተናግረው፥ ሰላምን የምትመኝ ቤተ ክርስቲያን ለጥቃት የተጋለጠች መሆኗን አስረድተዋል።

ሰፋ ያሉ ዓለም አቀፍ ቀውሶችን ያነሱት አቡነ ኪኩቺ፥ እነዚህን ክስተቶች ከቅዱስ ወንጌል የንቃት ጥሪ ጋር በማገናኘት፥ በምያንማር፣ በዩክሬን፣ በጋዛ እና በሌሎች አመጾች ምክንያት የሚፈጠሩትን ተግዳሮቶች በማብራራት፥ ችግሮቹ የዓለም አለመረጋጋት እና እርግጠኛ አለመሆን ስሜትን የሚጠቁሙ ናቸው” ሲሉ አስረድተዋል።

“ደስታ እና ተስፋ” የሚለውን የሁለተኛውን የቫቲካን ጉባኤ ሠነድ የጠቀሱት አቡነ ኪኩቺ፥ ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ተግዳሮቶች በወንጌል ብርሃን የመመልከት ግዴታ እንዳለባት ምዕመናኑን አስታውሰው፥ “ቤተ ክርስቲያን የዘመኑን ምልክቶች በየጊዜው መመርመርና በወንጌል ብርሃን የመተርጎም ግዴታ አለባት” ሲሉ ተናግሯል።

ተስፋን ከሌላ ቦታ ከየትም ማምጣት እንደማይቻል፥ ተስፋ የሚወለደው ከልብ እንደሆነ በማስገንዘብ ቤተ ክርስቲያን ተስፋን የሚፈጥር ማኅበረሰብ መሆን እንደምትፈልግ በማስረዳት፥ “እርስ በርሳችን የምንደጋገፍ፣ የምንደማመጥ እና አብረን የምንመላለስ ቤተ ክርስቲያን መሆን እንፈልጋለን” በማለት የጋራ ማስተዋልን እና ተግባርን ጠይቀዋል።

በዓሉ በምያንማር ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን፣ የቶኪዮ ሀገረ ስብከት በወንጌል ብርሃን የአብሮነት እና የተስፋ ጥሪ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት በማረጋገጥ በጸሎት ተጠናቋል።
 

19 November 2024, 16:28