በስደት ላይ ያሉ ክርስቲያኖችን ለማስታወስ በ ‘ቀይ ረቡዕ’ ዕለት የተለያዩ ሃውልቶች እና ህንፃዎች በቀይ መብራት ደምቀው ውለዋል
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
እርዳታ ለሚያስፈልጋት ቤተክርስቲያን ድጋፍ የሚያሰባስበው (Aid to the Church in Need - ACN) በተባለው ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የቀይ ረቡዕ ዓመታዊ ዘመቻ አካል በመሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ ካቴድራሎች፣ አብያተ ክርስቲያናት፣ ሀውልቶች እና ህዝባዊ ህንጻዎች በዓለም ዙሪያ በቀይ ቀለም አሸብርቀው መዋላቸው ተገልጿል።
ይህ ተነሳሽነት የፀረ-ክርስቲያን ስደት እውነታ ላይ ብርሃን ለማፈንጠቅ እና የሃይማኖት ነፃነት እንደ አንድ መሰረታዊ ሰብአዊ መብት አስፈላጊነትን ለማጉላት በ 2008 ዓ.ም. በካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅት እንደ ተጀመረ የተገለጸ ሲሆን፥ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ፣ ክርስቲያኖች ስደት ለደረሰባቸው ወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው በእምነት ለመጸለይ በመላው ዓለም በመሰብሰብ በዘመቻው ውስጥ ያለው ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።
ታዋቂ ሕንፃዎች በቀይ ቀለም ያሸበርቃሉ
ከህዳር 9 እስከ 15 ባሉት ቀናት ውስጥ ከሚካሄዱት 300 የሚሆኑ ክስተቶች ውስጥ ከ20 በሚበልጡ አገሮች የተለያዩ ዝግጅቶች የሚካሄዱ ሲሆን፥ ከነዚህም ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴዎች፣ ውይይቶች፣ የቀጥታ ስርጭቶች፣ ኮንሰርቶች እና የፓርላማ ውይይቶች እንደሚደረጉ ተገልጿል።
ዩናይትድ ኪንግደም፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያ፣ ፈረንሳይ፣ ስፔን፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ፊሊፒንስ፣ ሜክሲኮ፣ ቺሊ እና ኮሎምቢያ በዝግጅቱ ላይ ከሚሳተፉ ሃገራት መካከል ይገኙበታል።
አየርላንድ 26 ካቴድራሎቿን በቀይ መብራት ለማድመቅ ያቀደች ሲሆን፥ በተመሳሳይ በፈረንሣይ በሚደረግ ዝግጅት ላይ ስደትን በትዕግስት እና በጥንካሬ ያሳለፉ ስደተኞች ምስክርነት የሚሰማበት መርሃ ግብር እንደሚያካትት እንዲሁም ኤ.ሲ.ኤን ጀርመን በበኩሉ በቀጥታ ስርጭት የሚተላለፍ ኮንሰርት ለማዘጋጀት አቅዷል።
በዩናይትድ ኪንግደም ለሚሰደዱ ክርስቲያኖች መጸለይ
በብሪታንያ የዌስትሚኒስተር ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም የእንግሊዝ እና የዌልስ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ቪንሰንት ኒኮልስ ዘመቻውን በመደገፍ፣ በዚህ ጉዳይ ስቃይ ለሚደርስባቸው ክርስቲያኖች ግንዛቤ ለማስጨበጥ እና ለመጸለይ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ቁምስናዎች እና ግለሰቦች እንዲሳተፉ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት ጋብዘዋል።
ለንደን ውስጥ በሚገኘው ብሮምፕተን ኦራቶሪ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ልዩ ቅዳሴ በሚካሄድበት እንደ ዌስት-ሚኒስተር ፓርላማ ያሉ ታዋቂ ሕንፃዎች በቀይ ቀለም የሚደምቁ ሲሆን፥ በዕለቱም በመላው ሀገሪቱ ያሉ ምእመናንም የሰማዕታትን ደም የሚያመለክተውን ቀለሙ ቀይ ቀለም የሆነ ልብስ እንዲለብሱ አበረታተዋል።
ኤሲኤን-ዩኬ በዕለቱ በሚቀርበው ዝግጅት ላይ ተሳታፊዎች የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ በግብር ከፋዩ የተደገፈ የውጪ ሃገራት የልማት ዕርዳታን መስጠት እንዲችሉ የሚጠይቅ ግልጽ ደብዳቤ ላይ እንዲፈርሙ ጠይቋል።
የዘንድሮው ዘመቻ የሚያተኩረው በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅ እና በሌሎችም አካባቢዎች በስደት እና በግጭት ምክንያት በተፈናቀሉ ክርስቲያን ልጆች እና ወጣቶች ላይ ነው ሲሉ የኤሲኤን ብሔራዊ ዳይሬክተር ካሮሊን ሃል አስረድተዋል።
የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ዘመቻውን ተቀላቅላለች
ከዚህም በተጨማሪ በዚህ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የእንግሊዝ ቤተክርስቲያን ዘመቻውን የተቀላቀለች ሲሆን፥ 'ሲኦኢ' የተሰኘው የቤተ ክርስቲያኗ ድረ-ገጽ ግለሰቦች፣ ደብሮች እና ድርጅቶች የሚሰደዱ ክርስቲያኖችን ጉዳይ ለመከታተል እና ለመደገፍ ሊጠቀሙባቸው የሚችሏቸውን የተለያዩ ግብዓቶችን አቅርቧል።
በድህረ ገጹ ላይ ክርስቲያኖች በጭንቀት ውስጥ ላሉ ወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው ሲጸልዩ የሚጠቀሟቸው ጸሎቶች እና የተወሰኑ ቀናት የተዘረዘሩ ሲሆን፥ ከእነዚህም መካከል ጥር 7 የሰማዕታት ቀን፣ ነሃሴ 16 በሃይማኖት ወይም እምነት ላይ የተመሰረተ ጥቃት ሰለባዎች የሚታወሱበት ቀን እንዲሁም በመጪው ዓመት ህዳር በገባ የመጀመሪያ እሁድ ለተሰደደችው ቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፍ የጸሎት ቀን ተደርጎ እንዲከበር ገልጿል።
እ.አ.አ. ከ2022-2024 መካከል ስደት እየተባባሰ ነው
በጥቅምት ወር የታተመው እና “የተሰደዱ እና የተረሱ?” በሚል ርዕስ ኤሲኤን በቅርብ ጊዜ ያወጣው የሁለት ዓመት ሪፖርት መሠረት፣ እ.አ.አ. በ2022 እና 2024 መካከል በተደረጉ ጥናቶች በአብዛኛዎቹ አገሮች የክርስቲያን ስደት በከፍተኛ ሁኔታ መባባሱን ተገልጿል።
ሪፖርቱ መፈናቀልን፣ የሴቶች እና ልጃገረዶችን የግዳጅ ጋብቻን እና ፀረ ለውጥ ህጎችን አጉልቶ አሳይቷል።