የደቡብ አፍሪካ ካቶሊክ የጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ብጹእ አቡነ ሲተምበል ሲፑካ የደቡብ አፍሪካ ካቶሊክ የጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ብጹእ አቡነ ሲተምበል ሲፑካ 

የደቡብ አፍሪካ ብጹአን ጳጳሳት የሞዛምቢክ ባለስልጣናት በምርጫው ውጤት “ደስተኛ ያልሆነውን” ህዝብ እንዲያረጋጉ ጠየቁ

የደቡብ አፍሪካ፣ ቦትስዋና እና ኢስዋቲኒ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት ለሞዛምቢክ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ አባላት በጻፉት ደብዳቤ በደቡብ አፍሪካዊቷ ሀገር ከምርጫ በኋላ የተፈጠረውን አለመረጋጋት ተከትሎ በተከሰተው ግጭት በአከባቢው ለሚገኘው ህዝበ-እግዚአብሔር ያላቸውን አጋርነት እና ጸሎታቸውን ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በደቡብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ሞዛምቢክ የመጀመሪያው የመድበለ ፓርቲ ምርጫ ከተካሄደ ከጎርጎሪያኑ 1994 ዓ.ም. ጀምሮ እያንዳንዱ የምርጫ ውጤት በተቃዋሚዎች ብቻ ሳይሆን በገለልተኛ ተንታኞችም ሳይቀር በከፍተኛ ሁኔታ አወዛጋቢ የሆነ ሲሆን፥ ዘንድሮም በሀገሪቱ በጥቅምት ወር አዲሱ ፕሬዝዳንት ዳንኤል ቻፖ ከተመረጡ ወዲህ የተቀሰቀሰው አለመረጋጋት እየተባባሰ ነው።

አርብ ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም. በተፃፈው ደብዳቤ ላይ ጳጳሳቱ ባለፈው መስከረም 29 ከተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ገዥው ፓርቲ ፍሬ-ሊሞ እጩ አሸናፊ መሆኑን ካወጀበት በኋላ የተከሰተውን ‘የተቃውሞ መንስኤዎችን ለይተው በማውጣት ለጉዳዩ ቶሎ መፍትሄ እንዲሰጡ’ ለሃገሪቱ ባለስልጣናት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የሞዛምቢክ ህዝብ ፍላጎት ይከበር
የደቡብ አፍሪካ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ (SACBC) ፕረዚዳንት በሆኑት ብጹእ አቡነ ሲተምበል አንቶን ሲፑካ በተፈረመ ደብዳቤያቸው ላይ ጳጳሳቱ እንደገለጹት ‘በሃገሪቷ በተካሄደው የምርጫ ውጤት የተበሳጨውን ህዝብ ችግር በጊዜ መፍታት እንደሚያስፈልግ እና የሞዛምቢክን ህዝብ ፍላጎት እንዲያከብሩ ለባለሥልጣናት በምታቀርቡት ጥሪ ከእናንተ ጋር እንተባበራለን’ በማለት ለሃገሪቱ ብጹአን ጳጳሳት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በአንዳንድ ዘገባዎች መሰረት ለሶስት ሳምንታት በተካሄደው ምርጫ ውጤት ተከትሎ በተቀሰቀሰ የተቃውሞ ሰልፍ ቢያንስ 30 ሰዎች እንደተገደሉ እና በመቶዎች የሚቆጠሩት ደግሞ እንደቆሰሉ ተዘግቧል። ጥቅምት 29 በተፃፈው ደብዳቤ ላይ የደቡብ አፍሪካ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ አባላት እንደዚህ አይነት ሰፊ ቅሬታዎች እያሉ የደቡብ አፍሪካ መንግስት ምርጫውን ለመደገፍ ባደረገው ውሳኔ ተጸጽተናል ብለዋል።

ተቃውሞውን ለማረጋጋት የቀረበ ጥሪ
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሃሙስ ጥቅምት 28 የሞዛምቢክ ዋና ከተማ በሆነችው የማፑቶ ጎዳናዎች ላይ በመውጣት “ፍሬ-ሊሞ መልቀቅ አለበት” የሚል ዜማ በማሰማት ተቃውሟቸውን የገለፁ ሲሆን፥ ይሄንንም ተከትሎ የደቡባዊ አፍሪካ ልማት ማህበረሰብ (SADC) ‘ግጭቱን’ እንዲፈታ ብጹአን ጳጳሳቱ ጠይቀዋል።

ሞዛምቢክ እንደ ጎርጎሳውያኑ በ1975 ከፖርቹጋል የቅኝ አገዛዝ ነፃ ከወጣች በኋላ ለሃምሳ ዓመታት አገሪቱን እየመራ ያለው የፍሬ-ሊሞ ፓርቲ የስልጣን ዘመን ማብቂያ ሊሆን ይችላል ተብሎ የተገመተ ሲሆን፥ ባለፈው ሀሙስ በዋና ከተማይቱ ማፑቶ ጎዳናዎች ላይ ተቃዋሚዎች ያስተባበሯቸው ታላላቅ ሰልፎች ከመካሄዳቸው በፊት በሞዛምቢክ የሚገኙ የካቶሊክ ጳጳሳት በምርጫው ሂደት እና በውጤቱ ምክንያት በተከሰተው ግጭት ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተሳተፉት ሁሉ ጥፋታቸውን አምነው ይቅርታ እንዲጠይቁ እና እውነታውን በድፍረት እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የሞዛምቢክ ጳጳሳት ጥቅምት 12 ያወጡት መግለጫ “ይህ መንገድ በህይወት መኖር እና ንቁ ተሳታፊ መሆን የሚፈልግ ብሎም ጥቃትን በመፍራት ዝም የማይል ህብረተሰብ በመፍጠር አንድን ሀገር ወደ መደበኛ አካሄድ የሚመልስ ነው” በማለት ይገልፃል።

ሞዛምቢክ እውነት፣ ሰላም እና መረጋጋት ይገባታል
ጥቅምት 29 ለሞዛምቢክ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ አባላት በተላከው ደብዳቤ የደቡብ አፍሪካ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ አባላት ወደ ደቡባዊ የአፍሪካ ሀገራት የአብሮነት ጉብኝት ለማድረግ ያላቸውን ፍላጎት በመግለጽ፥ በአስተዳደር ሂደት ውስጥ የትብብር አሰራሮችን መፍጠር እና የብሄራዊ አንድነት መንግስት ሊሆን እንደሚችል ግምት ውስጥ ማስገባት፥ አሁንም ሆነ ወደፊት በሀገሪቱ ውስጥ ብቁ እና ጠንካራ የሆኑ ተቋማትን በምርጫ ሂደቶች ውስጥ ማሳተፍ ለመጪው የሞዛምቢክ ህልውና ተስፋን እነደሚሰጥ አብራርተዋል።

መግለጫው በመጨረሻም ‘በዚህ የፈተና ጊዜያት ከሞዛምቢክ ህዝብ እና ከሞዛምቢክ ቤተክርስቲያን ጋር ያላቸውን አጋርነት ለመግለጽ በቅርቡ በሃገሪቱ ጉብኝት ለማድረግ እንዳሰቡ’ በመጥቀስ፥ “ለሞዛምቢክ እውነት፣ ሰላም፣ መረጋጋት እና መቻቻል ይገባታል” በማለት ይደመድማል።
 

11 November 2024, 15:03