የህዳር 08/2016 ዓ.ም ሰንበት ዘአስተምህሮ 1ኛ ወንጌል እና የዕለቱ መልዕክቶች አስተንትኖ የህዳር 08/2016 ዓ.ም ሰንበት ዘአስተምህሮ 1ኛ ወንጌል እና የዕለቱ መልዕክቶች አስተንትኖ  (©MPIX.TURE - stock.adobe.com)

የህዳር 08/2016 ዓ.ም ሰንበት ዘአስተምህሮ 1ኛ ወንጌል እና የዕለቱ መልዕክቶች አስተንትኖ

“ስትጸልዩ እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ እነርሱ ለሰዎች ለመታየት ሲሉ በየምኵራቡና በየመንገዱ ማእዘን ላይ ቆመው መጸለይ ይወዳሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ሙሉ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። አንተ ግን ስትጸልይ ወደ ክፍልህ ግባ፤ በሩንም ዘግተህ በስውር ወዳለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የተደረገውን የሚያይ አባትህም ዋጋህን ይከፍልሃል።

የዕለቱ ምንባባት

1.    ሮሜ 5፥10-21

2.   1ዮሐ. 2፥1-17

3.   ሐዋ. 22፥1-11

4.   ማቴ.6፥5-15

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ስለ ጸሎት

“ስትጸልዩ እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ እነርሱ ለሰዎች ለመታየት ሲሉ በየምኵራቡና በየመንገዱ ማእዘን ላይ ቆመው መጸለይ ይወዳሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ሙሉ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። አንተ ግን ስትጸልይ ወደ ክፍልህ ግባ፤ በሩንም ዘግተህ በስውር ወዳለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የተደረገውን የሚያይ አባትህም ዋጋህን ይከፍልሃል። ስትጸልዩ፣ ከንቱ ቃላት በመደጋገም ጸሎታቸው የሚሰማላቸው እንደሚመስላቸው አሕዛብ ነገራችሁን አታስረዝሙ። እነርሱን አትምሰሏቸው፤ አባታችሁ ከመለመናችሁ በፊት ምን እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃልና። “እናንተ ግን እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ፤ “ ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን።

የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን። እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፣ በደላችንን ይቅር በለን። ወደ ፈተናም አታግባን ከክፉው አድነን እንጂ፣ መንግሥት፣ ኃይል፣ ክብርም፣ ለዘለዓለሙ ያንተ ነውና፤ አሜን።  ’

እናንተ የበደሏችሁን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ ደግሞ እናንተን ይቅር ይላችኋል። ነገር ግን የሰዎችን ኀጢአት ይቅር የማትሉ ከሆነ፣ አባታችሁም ኀጢአታችሁን ይቅር አይልላችሁም።

የእለቱ አስተንትኖ

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

በዚህም ዕለት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በተለያዩ ንባቦች አማካኝነት ወደ እያንዳዳችን በመምጣት የሚያስፈልገንን ይሰጠናል የጎደለውን ሁሉ ይሞላልናል በእርሱም ቃል እንድንኖር ያበረታታናል።

የአምልኮ ሥርዓታችን ዘመነ ጽጌ (የአበባ ወቅት) የሚባለውን ወቅት ጨርሶ በዚህ ሰንበት ዘአስተምሕሮ የሚባለውንና ለመጪዎቹ አምስት ሳምንታት የሚዘልቀውን ወቅት ጀምረናል። የምሕረት ወይም (ዘአስትምሕሮ) የትምህርት ዘመን የሚል አንድምታ እንዳለው ቢነገርም ሁሉም ግቡ የእሱን ምሕረት ማዳረስ ስለሆነ የክርስቶስ ልደት ከመከበሩ በፊት ስለ እግዚአብሔር ምሕረት በተለያዩ መልኩ እንድናስተነትን ይጋብዘናል።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በዛሬው መልዕክቱ ላይ “በአዳም በኩል ሞት፥ በክርስቶስ በኩል ሕይወት መጣ” በሚለው ሃሳብ ቃሉን ያካፍለናል። በአንድ ሰው በአዳም ኃጢአት እና አለመታዘዝ ምክንያት ሞት እና ፍርድ መጣ (ዘፍ. 2፥15-17፤ 3፥1-3) “እንዲሁም በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መታዘዝ ምክንያት ለሰው ሁሉ ጽድቅና ሕይወት መጣ” (ፊል. 2፥8)። በአዳም በኩል “የሞት ሥልጣን” መጣ፤ በክርስቶስ በኩል “የሕይወት ሥልጣን” መጣ።

ሁል ጊዜ ጸጋ በኃጢአት ላይ ይነግሣል ፤ ብርሃን በጨለማ ላይ ሥልጣን እንዳለው ሁሉ ጸጋም በኃጢአት ላይ ሥልጣን አለው። ኃጢአት ወደ ሞት ይመራል፤ ጸጋ ደግሞ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት ይመራል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢአትንና ሞትን በሚገባ አሸንፏል (ሮሜ. 8፥1-21፤ 1ቆሮ. 15፥56)።

በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ሦስት ታላላቅ ደረጃዎች ማለትም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሰጠንን ሦስት ታላላቅ ስጦታዎች እንመለከታለን። የመጀመሪያው ጸጋ ሲሆን ሁለተኛው በጸጋ በኩል የሚገኘውን ጽድቅ እንዲሁም በሦስተኛ ደረጃ በጽድቅ በኩል የሚገኘው ዘለዓለማዊ ሕይወት ናቸው። በዚህም መንገድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአዳም በኩል የመጣውን ጉዳት ማስወገድ ብቻ ሳይሆን ከዚያም የበለጠ እንዳደረገ እናያለን። እኛ ሁላችንን የእግዚአብሔር ልጆች እና የመንግሥተ ሰማይ ሀብት ሁሉ ወራሾች አደረገን።

ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መታዘዝ ማለት በብርሃን መኖር ማለት ነው (1ዮሐ. 1፥7) “ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ እርስ በርሳችን ኅብረት አለን፥ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያድነናል”። በብርሃን ስንኖር ክርስቶስን እናየዋለን፤ እናውቀዋለን። የማንታዘዝ ከሆነ ግን የምንኖረው በጨለማ ስለሚሆን ክርስቶስን ልናውቀው አንችልም (ማቴ. 7፡21)። “በሰማያት ያለውን ፈቃድ የሚፈጽም እንጂ ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት አይባልም”። አንዳንዶቻችን በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን እንል ይሆናል ሆኖም ግን አንታዘዝም። ለእግዚአብሔር ቃል የምንታዘዝ ከሆነ ፍቅሩ በእኛ ፍፁም ይሆናል። የእግዚአብሔር ቃል፤ ሰው በፍፁም ነፍሱ፣ በፍፁም ሃሳቡ፣ በፍፁም ኃይሉ እግዚአብሔርን መውደድ ይገባዋል የሚል ነው (ማር. 12፥30)። ስለዚህም ለእግዚአብሔር ቃል መታዘዝ ማለት እርሱን መውደድ ማለት ነው።

ለእግዚአብሔር ስንታዘዝ፥ እርሱ ወደ እኛ ይመጣል፤ ከእኛም ጋር ይሆናል (ዮሐ. 14፥23)። እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ ይኖራል፤ እኛም በእግዚአብሔር እንኖራለን። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደኖረው ከኖርን፥ በእርሱ መሆናችንን እናውቃለን፤ በፍቅሩም ውስጥ እንኖራለን ።

በተለይም በእዚሀ ወቅት በቅዱስ ወንጌሉ አማካኝነት ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ግንኙነት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማድረግ አንዳንድ ጊዜ በተለመደው ተግባራችን ውስጥ ትንሽ ለውጥ ማድረግ አለብን። በዚህም መሰረት የእግዚአብሔር ምሕረት ነፍሳችን ላይ ጠብ እንዲልና የረሰረሰ መንፈሳዊ ሕይወት እንዲኖረን በዋነኝነት የሚያግዘን የጸሎት ሕይወታችን ነው። በዚህም መሠረት የዛሬው ወንጌል ስለ ጸሎት የሚለን ነገር አለው። መጀመሪያ ላይ "ስትጸልዩም እንደ ግብዞች አትሁኑ ፤ ለሰው ይታዩ ዘንድ በምኩራብና በመንገድ ማዕዘን ቆመው መጸለይን ይወዳሉና" ሲል እንዳንጸልይ ሰበብ የሚያዘጋጅልን ይመስላል። ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን ተሰባስቦ መጸለዩ ፣ በየመንገዱ ማማተቡና መስገዱን ትርጉም የለሽ እያደረግን ከጸሎት ለማፈግፈግ ይዳዳን ይሆናል። ነገር ግን ክርስቶስ በሕዝብ ፊት መጸለይን በራሱ አላወገዘም ፤ የተቃወመው የምንጸልይበት ሀሳብን ነው:- "ስትጸልዩም እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ ለሰው ይታዩ ዘንድ በምኩራብና በመንገድ ማዕዘን ቆመው መጸለይን ይወዳሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል"። የሚጸልዩበት ዓላማ በሰው ይታዩ ዘንድ ስለሆነ ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘትን አላሰቡም ስለዚህም ይህ ዓይነቱ ጸሎት ዋጋ እንደሌለው ነው ወንጌሉ የሚያስተምረን።

በጸሎት ብዙ ቃላትን ማባከን አያስፈልግም፡ ጌታ ለእርሱ የምንናገረውን ያውቃል። ዋናው የጸሎታችን የመጀመሪያ ቃል "አባታችን" የሚለው መሆኑ ነው። ስለዚህም ወንጌላዊው ማቴዎስ (6፣ 7-15) ታሪክ እንደሚለው ሐዋርያቱን አባታችን ሆይ የሚለውን ጸሎት ሲያስተምር የኢየሱስን ምክሮች በድጋሚ ያገኛሉ።

ለመጸለይ ድምጽ ማሰማት ወይም ብዙ ቃላትን ማውጣት የተሻለ እንደሆነ ማመን አያስፈልግም። በጩኸት መታመን የለብንም፣ ኢየሱስ "መለከትን በመንፋት" ወይም "በጾም ቀን እንደ ጿሚ ሆኖ በመታየት" ተለይቶ የታወቀው የዓለማዊነት ድምጽ እንደ ማያስፈልግ የገለጸ ሲሆን ለመጸለይ ከንቱ ድምጽ አያስፈልግም፡ ኢየሱስ ይህ የአረማውያን ባህሪ እንደሆነ ተናግሯል።

ጸሎት እንደ ምትሃታዊ ቀመር ተደርጎ መወሰድ የለበትም "ጸሎት አስማታዊ ነገር አይደለም፣ በጸሎት አስማት ማድረግ አትችልም። አስማተኛ ቃል ወደ ሚሰጡ አስማተኞች አልተመለሰም ነገር ግን ከእንደዚህ ዓይነት ገጠመኞች ምን እንደሚፈጠር በማወቁ በአስማት እርዳታ "አሁን ፈውስ አሁን ሌላ ነገር" ለማግኘት ብዙ ቃላት ጥቅም ላይ ይውላሉ። ነገር ግን ይህ አረማዊ መንፈስ ነው።

ታዲያ ሰው እንዴት መጸለይ አለበት? ይህንን ያስተማረን ኢየሱስ ነው፡- “በሰማይ ያለው አባቴ “ሳትለምኑት በፊት የምትፈልጉትን ያውቃል” ብሏል። ስለዚህ የመጀመሪያው ቃል "አባት" የሚለው ነው። ይህ የጸሎት ቁልፍ ሐሳብ ነው። ሳይነገር፣ ይህን ቃል ሳይሰማ መጸለይ አይችልም። ራሳችንን እንጠይቅ ፡- “ለማን ነው የምጸልየው? ሁሉን ቻይ አምላክ? ከእኔ በጣም ሩቅ ለሆነ አምላክ ነው የምጸልየው? ይህ ሐሳብ አይመቸኝም፥ ኢየሱስ እንኳ አልተሰማማውም። ለማን ነው የምጸልየው? የጠፈር አምላክ ለሆነው ለእርሱ? በዚህ ዘመን ትንሽ የተለመደ ነው አይደል? ወደ ጠፈር አምላክ መጸለይ። ይህ ከአጉል ባህል ጋር የሚመጣ ነገር ነው።

ይልቁንም ወደ ፈጠረን ወደ አብ መጸለይ አለብን። ነገር ግን ይህ ብቻ አይደለም፡ ወደ “አባታችን” መጸለይ ያለብን፣ ማለትም የሁሉም እና በጣም ስም የለሽ “የሁሉም አባት” ሳይሆን “የፈጠረህን፣ የሰጠን፣ የእኔ፣ የአንተ” ወደ ሆነው አምላክ አባት መጸለይ አለብን። አብ "በጉዞህ ላይ አብሮህ የሚሄድ" ነው፣ "ህይወትህን በሙሉ፣ ሙሉ ህይወትህን የሚያውቅ"፣ ጥሩ እና ጥሩ ያልሆነውን የሚያውቅ አባት እርሱ ነው። እሱ ሁሉንም ነገር ያውቃል። " ነገር ግን አሁንም በቂ አይደለም" ጸሎት ካልጀመርን - ይህ ቃል በከንፈር ያልተነገረ፣ ነገር ግን ከልብ በመነገሩ እንደ ክርስቲያኖች መጸለይ አንችልም።

እናም "አባት" የሚለውን ቃል ትርጉም በተሻለ ሁኔታ ለማስረዳት ይስሐቅ የነበረው በራስ የመተማመን መንፈስ እንመልከት - "ይህ የሃያ ሁለት ዓመት ልጅ ሞኝ አልነበረም" ወደ አባቱ ዞር ብሎ የሚሠዋ በግ እንደሌለ ሲያውቅና እኔ ራሴ የመሥዋዕቱ ሰለባ ነኝ የሚል ጥርጣሬ በእርሱ ላይ ይነሳል፡- “ጥያቄውን መጠየቅ ነበረበትና መጽሐፍ ቅዱስ “አባት ሆይ የሚሰዋው በግ የት አለ” እንዳለ ይነግረናል። እርሱ ግን አጠገቡ ያለውን አምኗል። አባቱ ነበር። ጭንቀቱ ማለትም "ምናልባት እኔ ትንሽ በግ ነኝ?" ሲል ወደ አባቱ ልብ ጥያቄ ያቀርባል።

ርስቱን የሚያባክን ልጅ በሚናገረው ምሳሌ ላይም የሆነው ይህ ነው “ወደ ቤትም መጥቶ፡- አባት ሆይ፥ በድያለሁ” ይላል። ለእያንዳንዱ ጸሎት ቁልፍ የሆነ ሐሳብ ነው: በአባት የመወደድ ስሜት፣ እናም "የሚያስፈልገንን ያውቃል" እና "የሚያስፈልገንን ስለሚያውቅ ጭንቀታችንን ሁሉ የምንተወው በጣም ቅርብ ወደ ሆነ አባት" ነው።

እሱ የእኔ ብቻ አባት አይደለም፣ አባታችን ነው፤ ምክንያቱም እኔ አንድ ልጅ አይደለሁም። ማናችንም አይደለንም። ወንድም መሆን ካልቻልኩ የዚህ አባት ልጅ ልሆን አልችልም፣ ምክንያቱም እርሱ በእርግጥ የወንድሞቼ አባት ነውና፤ ከዚህ በመነሳት "ከወንድሞቼ ጋር ካልታረቅሁ፥ አብን አባት ልለው አልችልም። ይህም ኢየሱስ “አባታችን ሆይ” የሚለውን ጸሎት ካስተማረን በኋላ ወዲያውኑ “የሰዎችን ኃጢአት ይቅር ብትሉ በሰማያት ያለው አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋል” በማለት የተናገረው እንዴት እንደሆነ ይገልጻል። ሌሎችን ይቅር ባትሉ ግን አባታችሁ እንኳን ኃጢአታችሁን ይቅር አይልላችሁም።

አሁን ደግሞ “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ውስጥ የሚገኙትን 7 የመማጸኛ ቃላትን እንመልከት። 

በሰማይ የምትኖር” የሚለው ቃል ደግሞ ሰማያት በሁሉም ማለትም በክፉዎች እና በደጎች፣ በፍትሃዊ እና ኢፍታዊ በሆኑ ሰዎች ላይ የምትወጣው ጸሐይ መገኛ” እንደ ሆነ ስለሚታወቅ እኛ በምድር ላይ ልናመጣው ያልቻልነውን ሰላምና ኅበረት ማስፈን እንችል ዘንድ የሚያሳስበን ነው፣ ይህንንም ለማድረግ እንችል ዘንድ በሰማይ ቤት የሚገኙትን በእምነት አባት እና እናት የሆኑትን የቅዱሳንን አማላጅነት መማጸን ይገባል።
ስምህ ይቀደስ” የሚለው መማጸኛ ደግሞ በሰማይ ቤተ ከሚገኙ ከቅዱሳን ጋር በጋራ በመሆን የእኛ ስም ሳይሆን የእርሱ፣ በጎ ሥራዎችን እንድናከናውን የሚረዳን እና የምያንቀሳቅሰን የእግዚኣብሔር ስም የተቀደሰ ይሁን የሚለውን ትርጉም ይገልጻል።

መንግሥትህ ትምጣ” የሚለው መማጸኛ ደግሞ የአንተ መንግሥት ትመጣ ዘንድ በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን፣ የእግዚኣብሔር መንግሥት ይመጣ ዘንድ በናፍቆት እንጠባበቃለን፣ ምክንያቱም አሁን በዓለም ውስጥ የሚታዩ ሁኔታዎች የእግዚኣብሔር መንግሥት መምጣትን የማይደግፉ በመሆናቸው የተነሳ የሰማያዊ አባታችን መንግሥት ይመጣ ዘንድ በመማጸን በዓለም ውስጥ የሚታዩ” ያልተገቡ ድርጊቶችን በመልካም ይቀይርልን ዘንድ የምንማጸንበት የጸሎት ክፍል ነው።

ፍቃድህ ይሁን” የሚለው መማጸኛ ደግሞ “የእግዚኣብሔር ፈቃድ ሁሉም ይድኑ ዘንድ ነው” የሚለውን ትርጉም የሚያሰማ ሲሆን አድማሳችንን በማስፋት ውስጣችንን በእርሱ በአባታችን ምሕረት ውስጥ በማስገባት ሁሉም የሰው ልጆች ይድኑ ዘንድ በመመኘት የምንጸልየው የመማጸኛ ጸሎት ነው።

“የእለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን” የሚለው የመማጸኛ ጸሎት ደግሞ እግዚአብሔር የሕይወት እንጀራ መሆኑን እና ይህም የተወደድን የእግዚኣብሔር ልጆች መሆናችንን እንድናስተውል ያደርገናል፣ ወላጅ አልባ ሕጻናት እንዳልሆንም እንድንረዳ ያደረገናል” የሚለውን ትርጉም ይሰጠናል። የሕይወት እንጄራ በመሆኑ የተነሳ እኛም እርስ በእርሳችን አንዱ አንዱን እንድያገልግል ይረዳን ዘንድ የምንጸልየው የመማጸኛ ጸሎት ነው።
በተመሳሳይ መልኩም ዛሬ በዚህ አባታችን ሆይ በሚለው ጸሎት ውስጥ “የእለት እንጀራችንን ስጠን” ብለን የምንማጸነው ጸሎት በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ውስጥ በቂ የሆነ የምግብ ክምች ቢኖርም ቅሉ የሚቀመስ ምግብ አጥተው የሚሰቃዩ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እግዚኣብሔር ያስባቸው ዘንድ የምንማጸንበት የጸሎት ክፍል ነው።  በተለይም ደግሞ ከምግብ ባሻገር ፍቅር የተራቡ ብዙ ሰዎች በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ስለሚገኙ እግዚአብሔር በበረኩት ያጠግባቸው ዘንድ በማሰብ የምንጸልየው የመማጸኛ ጸሎት ነው።
በደላችንን ይቅር በልልን” የሚለው የመማጸኛ ጸሎት ደግሞ እግዚአብሔር አጢአታችንን ይቅር ይለን ዘንድ በማሰብ የምንጸልየው ጸሎት ነው።  እኛም በበኩላችን የበደሉንን ሰዎች በደል ይቅር ማለት እንደ ሚጠበቅብን የሚያሳስብ የጸሎት ክፍል ነው። በተጨማሪም ይህ የጸሎት ክፍል ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ይቅር ማለት እንችል ዘንድ ብርታቱን እግዚኣብሔር ይሰጠን ዘንድ የምንማጸንበት የጸሎት ክፍል ነው። እግዚኣብሔር ይቅር እንደ ሚለን እኛም እርስ በእርሳችን ይቅር መባባል እንችል ዘንድ እንዲረዳን፣ እንዲያነሳስን የምንጸልየው ጸሎት ነው።

ወደ ፈተና አታግባን “ የሚለው የመማጸኛ ጸሎት ደግሞ እግዚኣብሔር ከፈተና ውስጥ ያወጣን ዘንድ በተለይም ክፉ የሆነ መንፈስ ከልባችን ውስጥ ያስወግድልን ዘንድ በማሰብ የምንጸልየው የመማጸኛ ጸሎት እንደ ነው። በተለይም ደግሞ ወደ ፈተና ውስጥ ለመግባት በከፍተኛ ሁኔታ በምንፈተንበት ወቅት እግዚኣብሔር ከእዚህ ፈተና ያወጣን ዘንድ፣ ከአጢአት ቀንበር ሥር ያላቅቀን ዘንድ እና ሁሉም ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን መሆናቸውን በመገንዘብ በጋራ እና በመተጋገዝ ወደ እርሱ ወደ እግዚአብሔር መጓዝ እንችል ዘንድ እንዲረዳን የምንጸልየው የመማጸኛ ጸሎት ነው፥ እግዝአብሔርን ሁል ጊዜ አባት ብለን መጥራት እንችል ዘንድ ጸጋውን እንዲሰጠን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንድትረዳን አማላጅነቷን ልንማጸን ይገባል።

የሰማነውን በልቦናችን ያሳድርልን፣ መልካም እለተ ሰንበት ለሁላችን።

በአባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ የተዘጋጀ ቫቲካን 

 

16 November 2024, 10:36