ቅዱስነታቸው ከ ‘Uniservitate’ (ዩኒሴርቪታቴ) መርሃ ግብር ተሳታፊዎች ጋር ቅዱስነታቸው ከ ‘Uniservitate’ (ዩኒሴርቪታቴ) መርሃ ግብር ተሳታፊዎች ጋር  

በአገልግሎት ትምህርት ላይ የሚወያይ ሲምፖዚዬም በሮም እየተካሄደ እንደሚገኝ ተነገረ

የካቶሊክ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የአገልግሎት ትምህርትን የሚያበረታታ የሁለት ቀን ሲምፖዚዬም በሮም እየተካሄደ እንደሚገኝ የቫቲካን ዜና አገልግሎት ከአስተባባሪዋን ዋቢ በማድረግ አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከመላው ዓለም የተወጣጡ እና በካቶሊክ ከፍተኛ ትምህርት የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ የሚመክሩ ምሁራን ከጥቅምት 28/2017 ዓ. ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት ሮም በሚገኝ “LUMSA” ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ስብሰባ መጀመራቸው ታውቋል።

‘Uniservitate’ (ዩኒሴርቪታቴ) በመባል የሚታወቀው እና በካቶሊክ ከፍተኛ ትምህርት ውስጥ የአገልግሎት ትምህርትን ለማስፋፋት ዓላማ ያለው መርሃ ግብሩ በ5ኛው ዓለም አቀፍ ሲምፖዚዬም ወጣቶችን፣ የተቋም መሪዎችን፣ ምሁራንን እና ባለሙያዎችን የአገልግሎት ትምህርትን ከአካዳሚክ ጥናት እና ማኅበረሰብ አገልግሎት ጋር በማጣመር በካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ስላላቸው ሚና ላይ እንደሚወያዩ ታውቋል።

የቫቲካን ዜና አገልግሎት ከጉባኤው ቀደም ብሎ የመርሃ ግብሩ አስተባባሪ የሆኑትን ወ/ሮ ማርያ ሮዛ ታፒያን እንዳነጋገረው፥ ሲምፖዚየሙ ከአምስት የተለያዩ አህጉራት የተውጣጡ ተማሪዎችን፣ ተመራማሪዎችን እና የዩኒቨርሲቲ ሠራተኞችን በማሰባሰብ በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ስለ አገልግሎት ትምህርት ለመማር ዕድል እንደሚሰጥ መናገራቸውን ገልጿል።

በተለይ እንደ ዩክሬን እና ፍልስጤም ባሉ ፈታኝ አካባቢዎች የአገልግሎት ትምህርት የሚያካሂዱ ተቋማት መኖራቸውን ገልጸው፥ ጉባኤው በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችን ካጋጠሟቸው ተሞክሮዎች የመማር ዕድል እንደሚፈጥር ወ/ሮ ማርያ ሮዛ ተናግረዋል።

ሌላው የሲምፖዚየሙ ገጽታ በአገልግሎት ትምህርት ውስጥ የመንፈሳዊነት ሚናን የሚጫወቱ ተመራማሪዎችን ማሰባሰብ እንደሆነ ወ/ሮ ማርያ ሮዛ ተናግረው፥ ከ “Uniservitate” በተገኘ አነስተኛ የገንዘብ ዕርዳታ የተደገፈው ይህን ጥናት ቀድሞውኑ መጀመሩን ተናግረዋል።

“የአገልግሎት ትምህርት በካቶሊክ አውድ ውስጥ በእርግጥ እያደገ ነው” ሲሉ አፅንኦት የሰጡት ወ/ሮ ማርያ ሮዛ፥ ይህም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጠየቁትን በተግባር የሚያውሉበት መንገድ እና የአካዳሚክ ዕውቀትን መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን ዕውቀትን ለሌሎች አገልግሎት መስጠት እንደሆነ አስረድተዋል።

ወ/ሮ ማርያ ሮዛ ሲምፖዚየሙ በ “ዩኒሰርቪት” ድረ-ገጽ ላይ በቀጥታ የሚተላለፍ በመሆኑ መከታተል የሚፈልጉትን ጋብዘዋል። ወ/ሮ ማርያ ሮዛ በመጨረሻም፥ በተመሳሳይ ጊዜ በጥሩ ሁኔታ መማር እና ማገልገል እንደሚቻል በማመልከት ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ደምድመዋል።

 


 

07 November 2024, 13:56