ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፥ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፥  

ክርስቶስ ሕያው ነው ተስፋችን ነው! "በቤተሰብ ውስጥ የቀውሶች፣ የጭንቀቶችና የችግሮች መከሰት"

እዚህ ላይ ፍቅራቸው፣ እንደ ምርጥ ወይን፣ የራሱን ባሕርይ ስለተቀዳጀ ሰዎች መጥቀስ ይቻላል። ምርጥ ወይን በጊዜ ሂደት “መተንፈስ” እንደሚጀምር ሁሉ፣ በየዕለቱ መተማመንን ማዳበርም ለትዳር ሕይወት ድምቀትንና ‹”ሰውነትን›” ይሰጣል። መተማመን ከትዕግሥትና ከተስፋ ጋር የተያያዘ ነው። ደስታውና መሥዋዕትነቱም ፍሬ የሚያፈራው በዓመታት ሂደትና ጥንዶች የልጅ ልጆቻቸውን እያዩ በሚደሰቱበት ጊዜ ነው። የቆየ ፍቅር ይበልጥ ንቁ፣ የተረጋጋና የዳበረ ሊሆን የሚችለው ጥንዶቹ በየቀኑና በየዓመቱ እንደ አዲስ እርስ በርስ ሲተዋወቁ ነው። ቅዱስ ዮሐንስ ዘመስቀል እንደሚነግረን፡- “የቆዩ ፍቅረኛሞች የተፈተኑና እውነተኛ ናቸው። ከውጭ ሲታይ በኃይለኛ ስሜትና ውስጣዊ ግፊት ያልተቃጠሉ፣ አሁን ባሉበት ደረጃ የቆየና በልባቸው ውስጥ የተከማቸ የፍቅርን ጣፋጭ ወይን የሚያጣጥሙ ናቸው”። እነዚህን የመሰሉ ጥንዶች ፈተናዎችን ሳይሸሹ ወይም ችግሮችን ሳይሸፋፍኑ ቀውሶችንና መከራን በስኬት የተወጡ ናቸው።

የቀውስ ተግዳሮት
የእያንዳንዱ ቤተሰብ ሕይወት የተለያዩ ቀውሶች ያሉበት ቢሆንም፣ ቀውሶቹ የድንቅ ውበቱ አካል ናቸው። ጥንዶች ቀውስን ማሸነፍ ግንኙነታቸውን ማዳከም እንደሌለበት፣ ይልቁንም የኅብረታቸውን የወይን ጣዕም ለማሻሻል፣ ለማረጋጋትና ለማበልጸግ እንደሚረዳ ሊያውቁ ይገባል። የጋራ ሕይወታቸው እርካታቸውን መቀነስ ሳይሆን ማሳደግ አለበት፤ እያንዳንዱ አዲስ እርምጃ ጥንዶችን አዲስ ደስታን እንዲያገኙ ይረዳቸዋል። እያንዳንዱ ቀውስ ይበልጥ እርስ በርስ ለመቀራረብ ወይም ባለ ትዳር መሆን ማለት ምን እንደ ሆነ ይበልጥ ለማወቅ የሚረዳ ተሞክሮ ይሆናል። ጥንዶች ለማይቀረው ቁልቁለት ወይም ለሚታገሱት ልዝብነት ራሳቸውን ማጋለጥ የለባቸውም። ይልቁንም ጋብቻ እንቅፋቶችን ማስወገድን የሚያካትት ፈተና ስለሆነ፣ እያንዳንዱ ቀውስ የግንኙነታቸው ወይን እንዲበስልና እንዲሻሻል የሚያደርግ አጋጣሚ ይሆናል። ጥንዶች ቀውሶችንና ፈተናዎችን እንዲጋፈጡና የቤተሰብ ሕይወት አካል መሆናቸውን እንዲገነዘቡ በሚደረግላቸው ድጋፍ ተጠቃሚ ይሆናሉ። ጥንዶች በእነዚህ ቀውሶች እንዳይሸነፉ ወይም የተቻኮለ ውሳኔ ወደ ማድረግ ፈተና ውስጥ እንዳይገቡ ልምድ ያላቸውና የሠለጠኑ ጥንዶችን ምክር ማግኘት ይኖርባቸዋል። እያንዳንዱ ቀውስ የሚያስተምረን ትምህርት ስላለ እርሱን ከልብ ማዳመጥን መማር ያስፈልገናል።

ቀውስ ሲያጋጥመን፣ መጀመሪያ ወደ መከላከል እናዘነብላለን፣ ምክንያቱም ነገሩን መቆጣጠር ያቃተን ወይም ስህተት የሠራን መስሎ ስለሚሰማን እንቅበጠበጣለን። ችግሩን ወደ መካድ፣ ወደ መደበቅ ወይም ወደ መናቅና በራሱ ጊዜ ይጠፋል ብለን ወደ ማሰብ እንዞራለን። ነገር ግን፣ ይህ አካሄድ ነገሮችን ያባብሳል፣ ጉልበትን ያባክናል፣ መፍትሔውን ያዘገያል እንጂ አይጠቅምም። ከዚህም የተነሣ ጥንዶች ይራራቃሉ፣ የተግባቦት ችሎታቸው ይቀንሳል። ችግሮች በአግባቡ ካልተያዙ፣ መጀመሪያ የሚጠፋው ተግባቦት ነው። “የምወደው ሰው” ቀስ በቀስ “ባልንጀራዬ”፣ ከዚያም “የልጆቼ አባት ወይም እናት” ብቻ፣ በመጨረሻም እንግዳ ይሆናል። ስለዚህ፣ ቀውስን በጋራ መጋፈጥ ያስፈልጋል። ሰዎች አንዳንዴ የሚሰማቸውን ከመናገር ወደ ኋላ ስለሚሉና በፍርሃት ዝምታ ስለሚዋጡ ይህን ማድረግ ይከባዳቸዋል። ቀውስ አልፎ አልፎ ልብ ለልብ ለመነጋገር መልካም አጋጣሚዎችን ሊፈጥር ይችላል። ጥንዶች ይህን ማድረግን ካላወቁበት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከበደ ይሄዳል። ተግባቦት በችግር ጊዜያት ለመለማመድ በሰላም ጊዜያት የሚማሩት ጥበብ ነው። ጥንዶች ውስጣዊ ሐሳባቸውንና ስሜቶቻቸውን ለማወቅና ለመግለጽ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። እንደ ምጥ፣ ይህም አዲስ ሀብት የሚያመጣ አስጨናቂ ሂደት ነው። ለቅድመ ሲኖዶስ ምክክር የተሰጡ መልሶች እንዳመለከቱት፣ አብዛኞቹ ሰዎች በአስቸጋሪ ወይም በወሳኝ ሁኔታዎች ወቅት ሐዋርያዊ እርዳታን አይሹም፤ ምክንያቱም ይህ እርዳታ ለእያንዳንዱ ሁኔታ የሚጠቅም ተጨባጭ ወይም ተፈላጊ መስሎ አይታያቸውም። ይህም ከሚያሳድሩት ጉዳትና ሥጋት አንጻር የጋብቻ ቀውሶችን በታላቅ ጥንቃቄ እንድንይዝ ያደርገናል።
አንዳንድ ቀውሶች ማንኛውንም ትዳር የሚያጋጥሙ ናቸው። አዲስ ተጋቢዎች ልዩነቶቻቸውን እንዴት አምነው እንደሚቀበሉና ከወላጆቻቸው እንዴት መላቀቅ እንደሚገባቸው ማወቅ አለባቸው። የአዲስ ልጅ መወለድ አዳዲስ ስሜታዊ ፈተናዎችን ይዞ ይመጣል።

ሕጻናትን ለማሳደግ የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ ማድረግን ይጠይቃል፤ የጉርምስና ዕድሜ ደግሞ ከፍተኛ ልፋትን፣ ተስፋ መቁረጥንና እንዲያውም በወላጆች መካከል ውጥረትን ሊያስከትል ይችላል። “ባዶ ጎጆ” ጥንዶች ግንኙነታቸውን እንደገና እንዲፈትሹ ያስገድዳቸዋል፤ አረጋውያንን መንከባከብ ደግሞ በእነርሱ ስም ከባድ ውሳኔዎች ማድረግን ያካትታል። እነዚህ ሁሉ ፍርሃትን፣ የበደለኛነት ስሜትን፣ ድብርትንና ድካምን የሚያስከትሉና በጋብቻ ላይም ትልቅ ጫናን የሚያሳድሩ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ፣ የጥንዶችን ሕይወት የሚነኩ፣ ብዙውን ጊዜ ገንዘብን፣ የሥራ ቦታ ውጥረትን፣ እንዲሁም ስሜታዊ፣ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ችግሮችን ያካተቱ ግላዊ ቀውሶችም አሉ። ያልተጠበቁ፣ የቤተሰብን ሕይወት ሊያውኩና የይቅርታና የእርቅ ሂደትን የሚጠይቁ ሁኔታዎች ሊከሰቱ ይችላሉ። ሌላውን ሰው ከልብ ይቅር ለማለት፣ እያንዳንዱ ሰው ሌላውን ሰው ወደ ስህተት ውስጥ እንዲገባ ሁኔታዎችን ላለማመቻቸቱ ራሱን በጸጥታና በትህትና መመርመር አለበት። አንዳንድ ቤተሰቦች የሚለያዩት ጥንዶቹ እርስ በርሳቸው ሲወነጃጀሉ ነው። ነገር ግን “ተሞክሮ እንደሚያሳየው፣ በተገቢ እርዳታና በእርቅ እንዲሁም በእግዚአብሔር ጸጋ በመታገዝ፣ አብዛኞቹ ችግር ያለባቸው ጋብቻዎች በአጥጋቢ ሁኔታ መፍትሔ ያገኛሉ። ይቅር ማለትንና ይቅር መባልን ማወቅ በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ መሠረታዊ ነገር ነው”። “የእግዚአብሔር ጸጋ ያለበት አድካሚ የማስታረቅ ጥበብ፣ የዘመዶችንና የጓደኞችን ለጋስ ትብብርና አንዳንዴም የውጭ እርዳታና የሙያ ድጋፍ ጭምር ያስፈልገዋል”።

ከትዳር አጋሮች አንዱ ወይም ሁለቱም እርካታ ካልተሰማቸው፣ ወይም ሁኔታዎች እነርሱ በፈለጉት መንገድ ካልሄዱላቸው፣ ጋብቻን ለማፍረስ በቂ ምክንያት አለ ብሎ መገመት ይበልጥ እየተለመደ መጥቷል። እውነታው ይህ ቢሆን ኖሮ፣ ዘላቂ ጋብቻ ባልኖረም ነበር። አልፎ አልፎ፣ ሁሉ ነገር አብቅቶለታል ብሎ ለመወሰን ትንሽ ቅሬታ፣ በተፈለገ ጊዜ የአንዱ አለመገኘት፣ ለምን ተነካሁ ማለት፣ ወይም ድብቅ ፍርሃት ብቻ በቂ ነው። ከዚህም የተነሣ ሰብአዊ ድክመቶችን ያካተቱ ሁኔታዎች ሊፈጠሩና እነዚህም ሁኔታዎች ስሜትን ሊጎዱ ይችላሉ። ከጥንዶቹ አንዱ ሙሉ ለሙሉ ተቀባይነት አጥቻለሁ የሚል ስሜት ሊያድርበት ወይም በሌላ ሰው ሊማረክ ይችላል። በዚህም ምክንያት ቅናትና ውጥረት ይፈጠራል፣ ወይም የሌላውን ጊዜና ትኩረት የሚጠይቅ አዲስ ፍላጎት ይከሰታል። አካላዊ ለውጦች በተፈጥሮ በሁሉም ላይ ይደርሳሉ። እነዚህ ለውጦችና ሌሎችም ብዙ ነገሮች፣ ለፍቅር ሥጋት ከመሆን ይልቅ ፍቅርን ለማደስና እንዲያንሰራራ ለማድረግ ብዙ አጋጣሚዎችን ይፈጥራሉ።

እነዚህን የመሰሉ ሁኔታዎች ሲኖሩ፣ አንዳንዶች፣ የግንኙነት ውስንነት ቢኖርም፣ ሌላውን ሰው የሕይወት ጉዞአቸው አጋር አድርገው መምረጣቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል ብስለት አላቸው፤ ሕልሞቻቸውንም ሙሉ ለሙሉ ሊያሟላ እንደማይችል በተጨባጭ አምነው ይቀበላሉ። እነዚህን የመሰሉ ሰዎች ራሳቸውን እንደ ሰማዕታት አድርገው አያስቡም። የቤተሰብ ሕይወት የሚሰጣቸውን ማንኛውንም ዕድል ይጠቀማሉ፣ የጋብቻ ትስስራቸውንም ለማጠናከር በትዕግሥት ይሠራሉ። ማንኛውም ቀውስ ቢሆን፣ አዲስ “አዎን” እንደሚሆን፣ ፍቅርን ሊያድስ፣ ሥር እንዲሰድና ውስጣዊ ጥንካሬ እንዲኖረው ሊያደርግ እንደሚችል ይገነዘባሉ። ቀውስ ሲከሰት፣ የቀውሱን መነሻ ምክንያት ለመመርመር፣ እንደ ገና ለመደራደር፣ አዲስ መደላድል ለመፍጠርና በጋራ ወደ ፊት ለመራመድ አይፈሩም። ይህን በመሰለ ቀጣይ ግልጽነት ማናቸውንም አስቸጋሪ ሁኔታ ለመጋፈጥ ይችላሉ። በማናቸውም ሁኔታ ዕርቅ ማውረድ እንደሚቻል እናውቃለን፣ “አሁን ያለው አንገብጋቢው ጉዳይ የትዳር ግንኙነታቸው ለፈረሰባቸው ሰዎች ክብካቤ መስጠት›› መሆኑን እንገነዘባለን”።

ምንጭ:- ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርእስ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 231-239 ላይ የተወሰደመሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።

አዘጋጅ አባ ዳንኤል ኃይለ

 

 

 

14 December 2024, 16:45