ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፥ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፥   (Vatican Media)

ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፥ "የሕማምና የደም መንገድ"

በመዝ. 128 ላይ የቀረበው ምሳሌ በመላው የመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካለው መራራ እውነት፣ ማለትም ቤተሰቦችንና የሕይወትና የፍቅር ሱታፌያቸውን ከሚያፈርስ ሥቃይ፣ ክፋትና ብጥብጥ ጋር የሚጣረስ አይደለም። ኢየሱስ ስለ ጋብቻ ያስተማረው ትምህርት (ንጽ. ማቴ. 19፡ 3-9) ከፍቺ ክርክር ውስጥ ተካቶ የቀረበው ምክንያት ስላለው ነው። የእግዚአብሔር ቃል ከጥንት ጀምሮ፣ በኃጢአት ምክንያት በወንድና በሴት መካከል ያለው የፍቅርና የንጽሕና ግንኙነት ወደ መበላለጥ የሚዞርበት አሳዛኝ ሁኔታ መኖሩን ሲያረጋግጥ፣ “ፍላጎትሽ ወደ ባልሽ ይሆናል፤እርሱም የበላይሽ ይሆናል” (ዘፍ. 3፡ 16)።

ቃየን አቤልን ከገደለበት ጊዜ ጀምሮ ያለው ይህ የሥቃይና የደም መፋሰስ ሐረግ በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች ውስጥ ተያይዞ ይገኛል። በአበው በአብርሃም፣ በይስሐቅና በያዕቆብ ልጆችና ሚስቶች መካከል ውዝግቦች እንደ ነበሩ፣ በዳዊት ቤተሰብ ውስጥ አሳዛኝ ሁኔታዎችና ብጥብጦች እንደ ተከሰቱ ፣ በጦቢያስ ታሪክ ውስጥ የቤተሰብ ችግሮች እንደ ነበሩ፣ እንዲሁም ኢዮብ “ወንድሞቼን ከእኔ አርቆአል፤ … ዘመዶቼ ትተውኛል፣ ወዳጆቼም ረስተውኛል… እስትንፋሴ ለሚስቴ እንኳ የሚያስጠላት ሆነ፤ የገዛ ወንድሞቼም ተጸየፉኝ” (ኢዮብ 19፡ 13-14፣ 17) እስከ ማለት ድረስ አማርሮ እንደ ተናገረ እናነባለን።

ኢየሱስ ራሱ ወደ ባእድ አገር ከተሰደደ ድሃ ቤተሰብ ተወለደ፡፡ አማቱ የታመመችበትን የጴጥሮስን ቤት ጎበኘ (ማር. 1፡ 30-31)፤ በኢያኢሮስና በአልአዛር ቤት በደረሱ የሞት መርዶዎች ምክንያት ኀዘኑን ገለጸ (ማር. 5፡ 22-24፣ 35-43፤ ዮሐ. 11፡ 1-44)። በናይን ከተማ የምትኖር አንዲት መበለት በልጅዋ ሞት አምርራ ስታለቅስ ሰማ (ሉቃ. 7፡ 11-15)፤ በትንሽ ከተማ ውስጥ የሚኖር አባት የሚጥል በሽታ ስላለበት ልጁ ሲማጸን አየ (ማር. 9፡ 17-27)። ወደ ቀረጥ ሰብሳቢዎቹ ወደ ማቴዎስና ዘኬዎስ ቤት ሄደ (ማቴ. 9፡9-13)፣ በፈሪሳዊው በስምኦን ቤት ላገኛት ኃጢአተኛ ሴት ተናገረ (ሉቃ. 7፡ 36-50)። ስለዚህ፣ ኢየሱስ ቤተሰቦች የሚያጋጥሙአቸውን ሥጋቶችና ውጥረቶች ያውቃል፣ በምሳሌዎቹም ውስጥ ይጠቅሳቸዋል፤ ለምሳሌ ጀብዱ ፍለጋ ቤታቸውን ትተው ስለሚሄዱ (ሉቃ. 15፡ 11-32)፣ ወይም ስለማይታዘዙ (ማቴ. 21፡ 28-31) ወይም ለሁከት ስለሚጋለጡ ልጆች (ማር. 12፡ 1-9) ምሳሌ ተናገረ፡፡ በሠርግ ግብዣ ላይ ወይን በማለቁ ለደረሰው ለውርደት የተቃረቡበትን ሁኔታ (ዮሐ. 2፡ 1-10)፣ ለግብዣ ተጠርተው ስላልመጡ እንግዶች (ማቴ. 22፡ 1-10) እንዲሁም አንድ ሳንቲም ስለጠፋበት ድሃ ቤተሰብ ጭንቀት (ሉቃ. 15፡ 8-10) ያወሳል፡፡

የእግዚአብሔር ቃል ተራ ረቂቅ ሐሳብ ሳይሆን፣ ችግርና መከራ ለደረሰበት ለእያንዳንዱ ቤተሰብ የመጽናናትና የወዳጅነት ምንጭ እንደ ሆነ ከዚህ አጭር ግምገማ መረዳት እንችላለን። ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቃል የጉዞአቸውን ግብ ያሳያቸዋል፤ እግዚአብሔር “እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም” (ራእይ 21፡ 4)።

የእጆችሁ ሥራ
በመዝሙር 128 መጀመሪያ ላይ፡- “የድካምህን ፍሬ ትበላለህ፤ ትባረካለህ፤ ይሳካልሃልም” (መዝ. 128፡ 2) የተባለለት አባት በራሱ የእጅ ሥራ የቤተሰቡን አካላዊ ደህንነትና ሰላም የሚጠብቅ ታታሪ ሠራተኛን ይመስላል። ከመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ ገጾች አንሥቶ ሥራ የሰው ልጅ ክብር ዋና አካል እንደ ሆነ መረዳት ይቻላል። በእነዚህም ገጾች ላይ “እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ወስዶ እንዲያለማትና እየተንከባከበ እንዲጠብቃት በዔድን የአትክልት ስፍራ አስቀመጠው” (ዘፍ. 2፡ 15) ተብሎ የተጻፈውን እናነባለን። ሰው ምድርን የሚያለማ፣ የተፈጥሮ ኃይሎችን የሚቆጣጠርና “የዕለት ጉርሱን ለማግኘት የሚጥር” (መዝ. 127፡ 2)፣ እንዲሁም የራሱን ስጦታዎችና ክህሎቶች የሚያዳብር ሠራተኛ ሆኖ ቀርቦአል።

“እግዚአብሔር በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ፣ የኢየሩሳሌምን ብልጽግና ያሳይህ። የልጅ ልጅ ለማየትም ያብቃህ” (መዝ. 128፡ 5-6) ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ ሥራ የኅብረተሰብን ዕድገት ያመቻቻል፣ ለቤተሰብም ምግብን፣ መረጋጋትና ፍሬያማነትን ያስገኛል። መጽሐፈ ምሳሌም በቤተሰብ ውስጥ የእናቶችን ልፋት ያስረዳል፤ የእነርሱ የዕለት ተዕለት ሥራ በባሎቻቸውና በልጆቻቸው ዘንድ እንደሚያስመሰግናቸው በዝርዝር ይናገራል (ንጽ. 31፡ 10-31)። ሐዋርያው ጳውሎስም በሌሎች ላይ ሸክም ሳይሆን በራሱ እጆች እየሠራ መተዳደሪያውን በማግኘቱ ይመካ ነበር (የሐዋ. 18፡ 3፤ 1 ቆሮ. 4፡ 12፤ 9፡ 12)። ጳውሎስ የሥራን አስፈላጊነት ስለ ተረዳ ፣ ለሚያስተምራቸው ክርስቲያን ማኅበረሰቦች “ሊሠራ የማይወድ አይብላ” (2 ተሰ. 3፡ 10፤ ንጽ. 1 ተሰ. 4፡ 11) የሚል ጥብቅ ትእዛዝ ሰጣቸው፡፡

በመጽሐፈ ሩት ውስጥ እንደተጻፈው፣ በሥራ አጥነትና በkሚ ሥራ አጥነት ምክንያት የሚደርሰውን ሥቃይ መረዳት እንችላለን፤ ኢየሱስም ሥራ ፈትተው በገበያ ቦታ ስለ ቆሙ ሠራተኞች በምሳሌ ተናግሮአል (ማቴ. 20፡ 1-16)፤ እርሱ ራሱ በድኅነትና በረሀብ የሚሠቃዩ ሰዎችን በአካል ያውቃቸዋል። ዛሬም በብዙ አገሮች ውስጥ የሥራ ዕድል መጥፋት በቤተሰብ ሕይወት ላይ ሥጋት ማስከተሉ አሳዛኝ እውነታ ነው።

ከዚህ ሌላ በኃጢአት ምክንያት እየታየ ያለውን ማኅበራዊ ውድቀት፣ ለምሳሌ፣ ሰዎች ተፈጥሮን እንደ ፈለጉ ሲያወድሙ፣ በስግብግብነትና በጭካኔ ሲበዘብዙት እያየን ዝም ማለት አንችልም። ይህ ድርጊት ምድሪቱን ወደ ባድማነት (ዘፍጥ. 3፡ 17-19) እና ከኤልያስ ጀምሮ ነቢያት ወደኮነኑት ማኅበራዊና ኢኮኖሚአዊ ኢ-ሚዛናዊነት (1ኛ ነገሥ.21) እንዲሁም ኢየሱስም ራሱ ወደ ነቀፈው ኢ-ፍትሐዊነት (ንጽ. ሉቃ. 12፡ 13፤ 16፡ 1-31) ያመራል።

ምንጭ፡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርእስ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 18-24 ላይ የተወሰደ።

አዘጋጅ አባ ዳንኤል ኃይለ


 

28 December 2024, 13:46