ብጹዕ ካርዲናል ባልዶ ሬይና የቅዱስ ዮሐንስ ዘላተራን ባዚሊካ ቅዱስ በር ከፈቱ

የሮም ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ባልዶ ሬይና በሮም ከሚገኙ አራቱ ጳጳሳዊ ባዚሊካዎች እንዱ የሆነውን የቅዱስ ዮሐንስ ዘላተራን ባዚሊካ ቅዱስ በር እሁድ ታኅሳስ 20/2019 ዓ. ም. ከፍተዋል። የላቲን የአምልኮ ሥርዓት በሚከተሉ ካቶሊካውያን ዘንድ እሑድ በተከበረው የቅዱስ ቤተሰብ ቀን ባሰሙት ስብከት፥ በችግር እና በመከራ ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦችን በጸሎት እንድናስታውሳቸው አደራ ብለዋል። “ምንም ያህል ከእርሱ ብንርቅም እግዚአብሔር የፍቅር ምንጫችን እና የማይናወጥ ተስፋች ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እሁድ ታኅሳስ 20/2019 ዓ. ም. የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴን የመሩት ብጹዕ ካርዲናል ባልዶ ሬይና፥ ዓለም የጣለባቸው ሸክም የከበዳቸው መንፈሳዊ ነጋዲያን እና ሌሎችም ሸክማቸውን ከላያቸው ለማውረድ ወደ ባዚሊካው የእንደሚመጡ አስታውስው፥ በኢዮቤልዩ ዓመት መባቻ ላይ የቅዱስ ዮሐንስ ላተራን ባዚሊካ ቅዱስ በር ከፍተዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ባልዶ ሬይና የቅዱስ ዮሐንስ ዘላተራን ባዚሊካ ቅዱስ በር ሲከፍቱ

የሮማ ከተማ ከንቲባም አቶ ሮቤርቶ ጓልቴሪ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ከባዚሊካው ፊት ለፊት የሚገኘውን አደባባይ እና ደረጃ መርቀው ከፍተዋል። በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የልዩ ልዩ እምነት ተከታዮች፣ እናቶች እና ልጆቻቸው፣ ወጣቶች፣ ምእመናን፣ ተማሪዎች እና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ አገር ጎብኚዎች ተገኝተው በዓለማችን ደስታ እና ተስፋ ላይ አስተንትነዋል።

“እዚህ መሆን ትልቅ ክብር ነው” ስትል የገለጸች አንዲት የሥነ-ሥርዓቱ ተካፋይ ወጣት፥ በሥፍራው ለመገኘት እየሚፈልጉ ነገር ግን ያልቻሉ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን ገለልጻለች። ከሜክሲኮ የመጡት አንድ ገዳማዊ እንደገለጹት፥ ለቅድስና የተጠራን በመሆናችን ወደዚህ ሥፍራ መምጣታችን ሕይወታችንን ለመለወጥ አስፈላጊ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ከአራት ልጆቻቸው ጋር ወደ ሮም የመጡት የኒው ዮርክ ከተማ ባልና ሚስትም እንደዚሁ፥ “ያለ እግዚአብሔር ዕርዳታ ምንም ማድረግ አንችልም” ሲሉ ተናግረዋል። ከሰሜን ጣሊያን የመጡት አንዲት እናትም በበኩላቸው፥ “እግዚአብሔር ተስፋን ሰጥቶን ቃሉን ለሌሎች እንድናደርስ ይርዳን!” ብለዋል።

በካቴድራላቸው በመገኘት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመተባበር
በቅዱስ ዮሐንስ ዘላተራን ባዚሊካ ውስጥ እሁድ ታኅሳስ 20/2019 ዓ. ም. የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴ ወደ ሦስት ሺህ የሚጠጉ ምእመናን የተካፈሉት ሲሆን ሌሎች በርካቶችም በቀጥታ የሚተላለፈውን ከባዚሊካው ውጭ ሆነው ተከታትለዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ባልዶ ሬይና ቅዱስ በርን ሲከፍቱ ባቀረቡት ጸሎት፥ በሩን ተሻግረው የሚያልፉትን የእግዚአብሔር ቸርነት እንዲያጅባቸው ጠይቀው፥ “እንደ መንጋ አንድ ላይ የሚሰበሰቡት በሙሉ የኢዮቤልዩ ቅዱስ ዓመትን በፍሬያማነት ይኖሩ ዘንድ ተመኝተዋል። በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ካቴድራል ውስጥ የተገኙት ምእመናን መንፈሳዊ ድጋፋቸውን እና ደስታን እንደሚያገኙ በማረጋገጥ ከቅዱስነታቸው ጋር አብረው ጸሎታቸውን እንዲያደርጉ ተጋብዘዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ባልዶ ሬይና በቅዱስ ዮሐንስ ዘላተራን ባዚሊካ ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴን ሲመሩ
ብጹዕ ካርዲናል ባልዶ ሬይና በቅዱስ ዮሐንስ ዘላተራን ባዚሊካ ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴን ሲመሩ

ከሚሰቃዩ ሰዎች ጋር መሆን
ብፁዕ ካርዲናል ሬይና በስብከታቸው በተለይ መገለል የሚሰማቸው አቅመ ደካሞችን እና በልባቸው ከባድ እና ጥልቅ ምሬትን የተሸከሙትን መኖራቸውን አስታውሰዋል። ሕሙማንን፣ እስረኞችን፣ በሥቃይ፣ በብቸኝነት፣ በድህነት እና በችግር ውስጥ የሚገኙትንም አስታውሰዋል። በተስፋ መቁረጥ ወይም የሕይወት ትርጉም በማጣት ተስፋን ላጡ፣ የእግዚአብሔርን ጥበቃ መፈለግ ላቆሙት ብቸኝነት እንዳይሰማቸው የማበረታቻ ምክራቸውን ለግሠው፥ ጦርነት፣ ጥላቻ እና የኑሮ አለመመጣጠን በሚታይበት ዓለም ውስጥ ለሁሉ ሰው ልባችንን እንክፈትላቸው” ብለዋል። 

ችግር ውስጥ ለሚገኙ ቤተሰቦች መጸለይ
የናዝሬቱ ቅዱስ ቤተሰብ በእያንዳንዱ ማኅበረሰብ ውስጥ የቤተሰብ ምሳሌነት የቅድስት ሥላሴን አንድነት የሚገልጽ መሆኑን ጠቅሰው፥ “ሁሉም ሰው የእግዚአብሔር ቤተሰብ አካል መሆኑን በማወቅ በአንድነት እና በሕብረት እንዲያድግ” በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል። ብፁዕ ካርዲናል ባልዶ ሬይና በጸሎታቸው በተለይም በችግር እና በስቃይ ውስጥ ያሉ ቤተሰቦችን በማስታወስ፥ ወደፊት የተከበረ ሕይወት እንዲኖራቸው ለማድረግ የሲቪል መሪዎች ትኩረት እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ባልዶ ሬይና የቅዱስ ዮሐንስ ዘላተራን ባዚሊካ ቅዱስ በር በከፈቱበት ወቅት
ብጹዕ ካርዲናል ባልዶ ሬይና የቅዱስ ዮሐንስ ዘላተራን ባዚሊካ ቅዱስ በር በከፈቱበት ወቅት

እግዚአብሔርን በልባችን እና በቤታችን ውስጥ መቀበል
ብፁዕ ካርዲናል ባልዶ ሬይና በስብከታቸው እንደገለጹት፥ “የተሻገርነው ቅዱስ በር የቤታችንን በር ስንሻገር የምናደርገውን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ያስታውሰናል” ብለው፥ ይህ አሁን የተከፈተው በር የእግዚአብሔርን ቤት ብቻ ሳይሆን የልቡን ጥልቅነት ይገልጻል” ብለዋል።

ከቅዱስ ቁርባን ጸሎት በፊት ለቤተሰቦች በሚደረገው ጸሎት ላይ የልጆች ሰብዓዊ እና ክርስቲያናዊ ዕድገት በቤተሰብ ሕይወት ድጋፍ እንዲያገኝ እና በፍቅር ማሰሪያ የተቀደሰ እንዲሆን እና የትዳር ጓደኞችን ድርጊት እንዲመራ ወደ መንፈስ ቅዱስ ጸሎታቸውን አቅርበው፥ ጋብቻ ማንኛውንም ድክመት እና ቀውስ በማሸነፍ የበለጠ ጠንካራ ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል። “የቤቶቻችንን በሮች ስንሻገር እግዚአብሔርን ወደ ቤተሰባችን፣ ወደ ዕለታዊ ሕይወታችን፣ ከልጆች ጋር ወዳለን ግንኙነት እና እንዲሁም ለትዳር ትኩረት በመስጠት እንክብካቤ ለማድረግ እንጥራለን” ብለዋል።

የእግዚአብሔር ልጆች የመሆን ስጦታ
ብፁዕ ካርዲናል ባልዶ ሬይና በስብከታቸው፥ የጠፋው ልጅ ምሳሌ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን እንደገና እንድናውቅ የሚጋብዘን መሆኑን በመግለጽ፥ ስለ እግዚአብሔር አባትነት ያለን ሰብዓዊ አመለካከት የተዛባ ሊሆን እንደሚችል አስረድተው፥ እግዚአብሔር እኛ እንድንመሠርት የሚፈልገው ግንኙነት በስጦታ የሚገኝ መሆን አለበት” ሲሉ ተናግረዋል።

ቅዱስ በሮች የእግዚአብሔር የተከፈቱ ክንዶች ናቸው!
የእግዚአብሔር የተከፈቱ ክንዶች ሙሉ ርህራሄ እና የማይናወጥ ተስፋ ክብራችንን ሊመልሱልን እንደሚችሉ ጠቁመው፥ ከጠፋው ልጅ ታሪክ አንጻር እነዚያ የተከፈቱ ክንዶች ቅዱሱ በር መሆናቸውን
በታላቅ መጽናናት በመመልከት ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ለመመለስ ስንወስን የሚቀበለን እና የሚባርከንን እንጂ የተዘጋ በር አናገኝም” ብለዋል።

“ከእነዚያ ከተከፈቱ ክንዶች ቤተ ክርስቲያን መሆንን፣ ቅዱሳት ምስጢራትን፣ ነፃነታችንን ወደ በጎነት የሚለውጠውን የእግዚአብሔር ቤተሰብ መሆንን የምንማር በመሆናችን ሁሉም ሰው በቅዱስ በር እንዲያልፍ፣ የጌታን ቸርነት እንዲቀምስ እና እንዲያስብ፣ ደስታውንም እንዲለማመዱ እና በዓለማችን ውስጥ ብርቱ የተስፋ ዘሮች እና ወንድማማችነትን እንድናጎለብት ብርታትን ተመኝተዋል።

የቅዱስ ዮሐንስ ዘላተራን ባዚሊካ ቅዱስ በር የመክፈት ሙሉ ሥነ-ሥርዓት

 

30 December 2024, 16:12