በህንድ የቦምቤይ ሃገረስብከት የሃይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት ሲደረግ በህንድ የቦምቤይ ሃገረስብከት የሃይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት ሲደረግ  

በህንድ የሚገኙ ቤተክርስቲያናት በዚህ የገና ወቅት የተለያዩ ሃይማኖት ተቋማት የተሳተፉበት ዝግጅቶችን ማዘጋጀታቸው ተገለጸ

በህንድ ውስጥ እየጨመረ ለመጣው ሃይማኖታዊ ውጥረቶች ምላሽ ለመስጠት በሚል በመላ አገሪቱ የሚገኙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሃገረ ስብከቶች እና ድርጅቶች አሁን ባለንበት የገና ወቅት የተለያዩ ሃይማኖት ተቋማትን አንድነት ለማበረታታት የተለያዩ ዝግጅቶችን ማዘጋጀታቸው ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ህንድ ላለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ ሃይማኖቶች መሃከል የሚነሱ ግጭቶችን እና አለመግባባቶችን እያስተናገደች ሲሆን፥ በዚህም የተነሳ በያዝነው ዓመት ስደት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል። በተለይም ከአንድ ዓመት በፊት በማኒፑር ግዛት ከተካሄደው መጠነ ሰፊ ጥቃት ጀምሮ፣ የሌላ ሃይማኖት ተከታዮችን እምነት ለማስቀየር ሞክረዋል በሚል ሃሰተኛ ክስ በቁጥር አነስተኛ የሆኑ የክርስቲያን ማህበረሰብ ላይ የደረሰው ጥቃት በሃገሪቷ እየተበራከተ ለመጣው ሃይማኖታዊ ጥቃቶች ማሳያ ናቸው ተብሏል።

በዚህ የተነሳ በህንድ የሚገኙ ሀገረ ስብከቶች እና የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ተቋማት በተለያዩ የሀይማኖት ቡድኖች መካከል ሰላምና ስምምነትን ለማስፈን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተሰባስበዋል።

እነዚህ ስብሰባዎች በሃይማኖታዊ አለመቻቻል ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አጋርነታቸውን ለመግለጽ የታሰቡ ቢሆንም፥ በዋናነት በተለያዩ ሃይማኖቶች መካከል አንድነት እና የውይይት ባህልን ለማጎልበት እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ ከዚህም በዘለለ መጪው ጊዜ ሰላማዊ እንደሚሆን ተስፋ በማድረግ የገና በዓልን መንፈስ በህንድ ህገ መንግስት እይታ ለማክበር የታሰቡ ናቸው ተብሏል።

የኢምፋል ከተማ በማኒፑር ተጎጂዎች መሃል እርቅ እንዲፈጠር ጥሪ አቅርቧል
በሰሜን ምስራቅ ህንድ የምትገኘው እና የማኒፑር ግዛት ዋና ከተማ የሆነችው የኢምፋል ከተማ ሃገረስብከት በማኒፑር በደረሰው ሃይማኖታዊ ጥቃት ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን በመግለጽ፥ በተጋጩት ቡድኖች መሃል እርቅ ማስፈን እንደሚገባ አሳስቧል።

“ሀዘን እና ይቅርታ ለማኒፑር” በሚል ርዕስ በተካሄደው በዚህ ሀገር አቀፍ ተነሳሽነት በርካታ የሃይማኖት ተቋማት የተሳተፉበት ሲሆን፥ በዝግጅቱ ላይ በቅርብ ጊዜ በተፈጠረው ሁከት ምክንያት የተጎዱትን ሰዎች ለማስታወስ ያለመ ጸሎቶችን እና የአብሮነት መግለጫዎችን እንዳካተተ ተገልጿል።

ክዚህም በተጨማሪ ከስብሰባው ጉልህ ዓላማዎች ውስጥ አንዱ ወጣቱን ትውልድ በሰላም ግንባታ እና በግጭት አፈታት ላይ ለማስተማር ያለመ የማኒፑር የሰላም ፈንድን ማስጀመር እንደሆነ አዘጋጆቹ የገለጹ ሲሆን፥ ይህ የሰላም ፈንድ ተነሳሽነት በቀን አንድ ሩፒ ብቻ በማዋጣት በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ደጋፊዎች መጠነኛ መዋጮ እንዲያደርጉ በመጠየቅ፥ እንደዚህ አይነት የጋራ ጥረቶች የሰላም እና የመግባባት ባህልን በማጎልበት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በዴልሂ ከተማ ውስጥ ከሚገኙ የተለያዩ የክርስትና እምነት ተከታዮች የተውጣጡ ተወካዮች በማኒፑር እየተካሄደ ባለው የጎሳ ግጭት ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ለዓለም አቀፍ እና ለሀገራዊ የሰላም ውይይት መሰባሰባቸውም ተነግሯል።

የቦምቤይ ከተማ በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ውይይትን ታበረታታለች
ከነዚህ ሃገረ ስብከቶች በተጨማሪ የቦምቤይ ሃገረ ስብከት በመላ አገሪቱ እየጨመረ በመጣው ሃይማኖታዊ ውጥረትን ለማስቆም ያለመ ዓመታዊ የሃይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት በማዘጋጀት የገና በዓልን መንፈስ ወደ ሕይወት አምጥቷል።

ዝግጅቱ አንድነትን ለማጠናከር የጋራ በሆኑ እሴቶች እንዲሁም እምነት በቤተሰብ እና በህብረተሰብ ውስጥ በሚያመጣው ጉልህ የለውጥ ሃይል ላይ ያተኮረ ሲሆን፥ በዝግጅቱም ላይ የተለያዩ የእምነት ተቋማት ተወካዮች፣ ዲፕሎማቶች እና የህብረተሰብ ክፍሎች እንደተገኙ ተገልጿል።

የካርናታካ ግዛት የክርስቲያን ህብረትን አክብሯል
የካርናካታ ሃገረስብከትም በበኩሉ ከተለያዩ ቤተ እምነቶች የተውጣጡ በርካታ ክርስቲያኖች የተሳተፉበት እሁድ ዕለት በካርናታካ ግዛት ሥር ባለችው ቤላጋቪ ከተማ በክርስቲያኖች መካከል ያለውን የፍቅር እና የአንድነት መንፈስ ለማጠናከር በሚል ‘የተባበሩት የገና ክብረ በዓል’ መርሃ ግብርን በማዘጋጀት አክብረዋል።

ዝግጅቱ የተዘጋጀው ‘የካርናታካ የተባበሩት ክርስቲያን ፎረም ለሰብአዊ መብቶች’ ተቋም ከክርስቲያናዊ ህብረት ኮሚሽን እና ከማዕከላዊ ሜቶ-ዲስት ቤተክርስቲያን ጋር በመተባበር እንደሆነም ተነግሯል።

የቤልጋም ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ዴሪክ ፈርናንዴስ ዝግጅቱን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር የክርስቶስን ፍቅር በ“የተስፋ ነጋዲያን” ማካተት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት በመስጠት፥ ዓለም የ2025 የኢዮቤልዩ ዓመትን ለማክበር በዝግጅት ላይ ባለበት ወቅት የዘንድሮውን የገና በዓል ማክበር ልዩ ፋይዳ እንዳለው አመልክተዋል።
 

18 December 2024, 12:38