በሕንድ የባንጋሎር ሃገረ ስብከት ለስደተኞች የሚሆን አስተማማኝ መጠለያ ለማቅረብ መዘጋጀቱ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የባንጋሎር ሃገረ ስብከት በአገልግሎትና በአካታችነት ተልእኮው ውስጥ ትልቅ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያመላክት ለስደተኞች መጠለያ ለማቅረብ “የስደተኞች መቀበያ እና የአጭር ጊዜ ማቆያ ማዕከልን” ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ አስቀምጧል።
ማዕከሉ በማቲከር ከተማ ውስጥ በሚገኝ ዬሽዋንትፑር ባቡር ጣቢያ አቅራቢያ የሚገኝ ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት ይህ ማዕከል ለተቸገሩ ወገኖች በቀላሉ ተደራሽ ይሆናል ተብሏል።
በህንድ የካርና-ታካ ዋና ከተማ የሆነችው ባንጋሎር በርካታ ስደተኞች የሚኖሩባት ከተማ ስትሆን፥ እንደ ኢንዲያ ታይምስ ዘገባ መሰረት ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ግማሽ ያህሉ ስደተኞች መሆናቸውን መረጃው ያመለክታል።
ይህንን እውነታ በመገንዘብ እና ችግሩን ለመቅረፍ ብሎም የበኩሉን አስተዋጽዖ ለመወጣት የባንጋሎር ሃገረ ስብከት ለዚህ ወሳኝ አገልግሎት በርካታ ገንዘብ በማውጣት ስደተኞች የሚያርፉበት መጠለያ ለማቋቋም ዝግጁነቱን አሳይቷል።
የምስረታ ሥነ ሥርዓት
ህዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም. በህንድ እና በኔፓል የቅድስት መንበር ሃዋሪያዊ ተወካይ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ሊዮፖልዶ ጊሬሊ ይህንን ተነሳሽነት ከሚደግፉ ሊቀ ጳጳስ ፒተር ማቻዶ፣ ረዳት ጳጳስ አሮኪያ ራጅ ኩመር፣ የደብሩ ካህናት እና የክርስቶስ ንጉሥ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ምዕመናን በተገኙበት የማዕከሉን የመሠረት ድንጋይ በመባረክ ሥራ አስጀምረዋል።
ሊቀ ጳጳስ ጊሬሊ ለፕሮጀክቱ ያላቸውን አድናቆት ገልፀው የስደተኞችን ክብር ለማስጠበቅ የተደረገ ጥረት መሆኑን በማንሳት፥ “ስደተኞች እንደ እግዚአብሔር ናቸው፥ በመሆኑም በክብር ልንቀበላቸው ይገባል” ካሉ በኋላ፥ የባንጋሎር ሃገረ ስብከት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የስደተኞችን ችግር መቅረፍ እንደሚገባ ካላቸው ራዕይ ጋር በመስማማት እንዲሁም የሕንድ ባህላዊ ሥነ-ምግባር የሆነውን 'አቲቲ ዴቮ ባህቫ' (Atithi Devo Bhava) ወይም ‘እንግዳ በእግዚአብሔር ይመሰላል’ የሚለውን የህዝቡን ትሁፊት በእውነት እና በተግባር በመኖር ሥራውን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ሊቀ ጳጳሱ በማከልም ይህ የስደተኞች ማዕከል የስደተኞቹን ክብር ለማረጋገጥ እና በድርጊታችን የክርስቶስን ፍቅር ለእነሱ ለማሳየት የሚያስችለን አንድ እርምጃ ነው ብለዋል።
በዝግጅቱ ላይ ሐዋርያዊ የቤተ ክርስቲያን ተወካዮች፣ ካህናት፣ የሃይማኖት አባቶች እና የምዕመናን ተወካዮች ተገኝተዋል።
ሊቀ ጳጳስ ማቻዶ የቫቲካን የተቀናጀ የሰው ልጅ ልማት ቢሮ እና ለቢሮው ዋና ጸሃፊ ዕጩ ካርዲናል ፋቢዮ ባጊዮ ላደረጉት ትልቅ አስተዋጽዖ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ብጹዕነታቸው ከዚህም ባለፈ “የስደተኞች መቀበያ እና የአጭር ጊዜ ማቆያ ማዕከልን” ለሚያስተዳድሩ የስካላ-ብሪኒያ ሚስዮናውያን ድጋፍ ዕውቅና በመስጠት፥ ፕሮጀክቱ በባንጋሎር ሁለገብ ማህበራዊ አገልግሎት ድርጅት ሥር እንደሚተዳደር ጠቁመዋል።
የወንጌል እሴቶች ማረጋገጫ
ፕሮጀክቱ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን ቃል እንደሚያስታውስ ያነሱት ሊቀ ጳጳሱ፥ “በራችንን የሚያንኳኳ እንግዳ ሁሉ፣ በየዘመናቱ አቀባበል የተደረገላቸውን እና የተገለሉትን እንግዶችን ለይቶ ከሚያውቀው ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የመገናኘት እድልን ይሰጣል” ብለዋል።
እንደ ጋዜጣዊ መግለጫው ከሆነ፥ ይህ ተነሳሽነት የባንጋሎር ሃገረ ስብከት የወንጌል እሴቶች ለሆኑት ለፍቅር፣ ለአገልግሎት እና ለአካታችነት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል የተባለ ሲሆን፥ “የስደተኞች መቀበያ እና የአጭር ጊዜ ማቆያ ማዕከሉ” የቤተክርስቲያኗ ተልእኮ የሆኑትን የተገለሉትን እና አቅመ ደካሞችን የመንከባከብ እና ሌሎችን በርህራሄ የመውደድ እና የማገልገል ዘላቂ ጥሪን ለማስታወስ መንገድ ይከፍታል ተብሏል።