የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ያስተላለፉትን ለአጭር ጊዜ የዘለቀው የማርሻል ህግ አዋጅን በመቃወም ህዝቡ በሴኡል በተካሄደው የሻማ ማብራት ሥነ ስርዓት ላይ ሲሳተፍ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ያስተላለፉትን ለአጭር ጊዜ የዘለቀው የማርሻል ህግ አዋጅን በመቃወም ህዝቡ በሴኡል በተካሄደው የሻማ ማብራት ሥነ ስርዓት ላይ ሲሳተፍ   (AFP or licensors)

የደቡብ ኮሪያ ብጹአን ጳጳሳት የማርሻል ህግ ዲሞክራሲን የመናድ አደጋ አለው አሉ

የደቡብ ኮሪያ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ዩን ሱክ ያኦል ባለፈው ማክሰኞ ዕለት ያስተላለፉትን ወታደራዊ ህግ (ማርሻል ሎው) አዋጅን “ሥርዓታዊ ሕገ-ወጥነት” ነው በማለት አውግዘው፥ ፕረዚዳንቱ ለዚህ ተግባራቸው ኃላፊነቱን እንዲወስዱ አሳስበዋል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንት ዲሞክራሲ የሰፈነባት አገራቸው በወታደራዊ ሕግ (ማርሻል ሎው) ስር እንድትሆን በድንገት ማክሰኞ፣ ኅዳር 24/2017 ዓ.ም. ማወጃቸው አገሪቱን ያስደነገጠ ክስተት ሆኗል።

ወታደራዊ ሕግ (ማርሻል ሎው) የሲቪል ባለሥልጣናት ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን እንደማይችሉ በሚቆጠርበት ጊዜ ወታደራዊ ባለሥልጣናት እንዲመሩ የሚደረግበት ጊዜያዊ አገዛዝ ነው።

ፕሬዚዳንት ዩን ሱክ የዎል አገሪቱ በአምስት አስርት ዓመታት አይታው የማታውቀውን ይህንን አስደንጋጭ ውሳኔ ለመወሰን ምክንያታቸው “ፀረ መንግሥት ኃይሎች” እና የሰሜን ኮሪያን ስጋት በመጥቀስ ነው።

ነገር ግን ወታደራዊ ሕጉ በታወጀ ሁለት ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የፓርላማ አባላቱ ፕሬዚዳንቱን ተቃውመው በምክር ቤት ከተሰበሰቡ በኋላ አስቸኳይ ድምጽ በመስጠት ከ300 የፓርላማ አባላት 190ዎቹ በፓርላማ በመገኘት በሙሉ ድምጽ ውሳኔውን አግደዋል።

ይሄንን ክስተት አስመልክተው የኮሪያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ ህዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም. በሰጡት በጠንካራ ቃላት በታጀበ መግለጫቸው ዴሞክራሲን ጠብቆ የማቆየትን አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥቶ በመግለጽ፥ ፕሬዚዳንት ዩን ሱክ የዎል የማርሻል ሕግ ማወጃቸውን በተመለከተ ማብራሪያ እና ይቅርታ እንዲጠይቁ ጥሪ አቅርበዋል።

ውሳኔያቸው በፓርላማ አባላት የታገደባቸው ፕሬዚዳንት ዩን የምክር ቤቱን ድምጽ ተቀብያለሁ እንዲሁም ሕጉን አንስቻለሁ በማለት ህጉ ከታወጀ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ የገለጹ ሲሆን፥ በአገሪቱ ወታደራዊ አገዛዝ በድንገት መጀመሩን ተቃውመው ከፓርላማ ውጭ ተሰባስበው የነበሩ ሰልፈኞች ሕጉ እንደገና በአጭር ጊዜ መቀልበሱን በማስመልከት ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል።

የጳጳሳቱ መግለጫ ማክሰኞ ዕለት ማምሻው ላይ የታወጀው ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ብዙ ኮሪያውያንን ያለ እንቅልፍ ያሳደረ ተግባር መሆኑን በመጥቀስ፥ “በሃገሪቱ በጣም አስቸኳይ ነገር እስካልተፈጠረ ድረስ የአንድ ክልል መንግስት እና አስተዳደራዊ አሰራር በተለመደው መንገድ መከናወን እና ለዜጎች መታወቅ አለበት” በማለት ገልጿል።

ከዚህ በፊት ተከስቶ በማይታወቅ ሁኔታ ፕረዚዳንቱ ህዳር 24/2017 ዓ.ም. ማክሰኞ ምሽት 4 ሰዓት ላይ በሃገሪቱ ቴሌቭዥን በቀጥታ ባስተላለፉት ውሳኔ፥ “የሰሜን ኮሪያ ደጋፊ ኃይሎችን ማስወገድ እና ዲሞክራሲያዊ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን መጠበቅ” አስፈላጊነትን በመጥቀስ ማርሻል ሎውን ማወጃቸውን ገልጸዋል።

ብጹአን ጳጳሳቱ በመግለጫቸው በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ የሚታዩ የውጪም ሆነ የጦርነት ስጋቶች አለመኖራቸውን ጠቁመው፥ ሃገሪቱ በወታደራዊ ህግ እንድትተዳደር በፕረዚዳንቱ የተላለፈው ውሳኔ ትክክለኛ እንዳልሆነ ጠቁመዋል።

ፕሬዚዳንቱ ወታደራዊ ሕግን ለመደንገግ ካደረጉት ያልተሳካ ሙከራ ጋር በተያያዘ የአገሪቱ ሕግ አውጪዎች ክስ ለመመሥረት ሂደት ጀምረዋል።

ብጹአን ጳጳሳቱ በደቡብ ኮሪያ ለመጨረሻ ጊዜ ወታደራዊ ሕግ የታወጀው በአውሮፓውያኑ 1980 መሆኑን ጠቁመው፥ በወቅቱ አገሪቱን ለበርካታ ዘመናት የገዙት አምባገነኑ ፖርከ ቹንግ ሂ በመፈንቅለ መንግሥት መገደላቸውን ተከትሎ እንደሆነ እና ብዙ እልቂትን ያስከተለ እንደነበር አስታውሰዋል።

“ዴሞክራሲያችን በታላቅ መስዋዕትነት የተገነባ ነው” ሲሉ የገለጹት ጳጳሳቱ “በኮሪያ ያለችው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዲሞክራሲያችንን ለመጠበቅ ከኮሪያ ሕዝብ ጋር በመተባበር ትቆማለች” ብለዋል።

የኮሪያ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ ቃል አቀባይ እና የሱዎን ሊቀ ጳጳስ በሆኑት ብጹእ አቡነ ማትያስ ኢዮንግ-ሁን የተፈረመበት መግለጫው፥ ፕሬዘዳንት ዩን ህዝቡን እንዲያነጋግሩ በመጠየቅ፥ “ፕሬዝዳንቱ ወደ ህዝቡ በመቅረብ ስለጉዳዩ እንዲያስረዱ እና ህዝቡን ከልብ ይቅርታ እንዲጠይቁ፥ ብሎም ስለድርጊታቸው ሀላፊነት እንዲወስዱ” አሳስበዋል።

የኮሪያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያ ብጹአን ጳጳሳት በመጨረሻም፥ ተጠያቂነት እንዲሰፍን እና ውይይት እንዲደረግ ጥሪ በማድረግ፥ ፕሬዚዳንቱ እና መንግስት “የኮሪያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እና የኮሪያ ሕዝብ ጥያቄን በቅንነት እንዲመለሱ” አሳስበዋል።
 

06 December 2024, 15:34