ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ “የወንጌል ልዑክ የተጠራው የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ለመሆን ብቻ ነው።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘወትር እሁድ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከሚሰበሰቡት ምዕመናንና የሃገር ጎብኝዎች ጋር የሚያደርጉትን የእኩለ ቀን የብስራተ ገብርኤል ጸሎት በፊት በዕለቱ በሚነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ ተመርኩዘው አስተንትኖ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በእዚህም መሰረት በትላንትናው እለት ማለትም በሐምሌ 8/2010 ዓ.ም ያደርጉት የቅዱስ ውነጌል አስተንትኖ በዕለቱ መካርቆስ ወንጌል ከምዕራፍ 6፡7-13 ላይ ትወስዶ በተነበበው እና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ 12ቱን ደቀ መዛሙርት ቅዱስ ወንጌል እንዲያበስሩ ሁለት ሁለት አድርጓቸው እንደላካቸው በሚያወሳው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መስረቱን ያደረገ እንደ ነበረ ለመረዳት ተችሏል።
የዚህ ዜና አዘጋጅ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!
“በዛሬው ቀን የተነበበልን ቅዱስ ወንጌል (ከማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 6 ከቁጥር 7 እስከ 13 የተወሰደው ማለታቸው) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስራ ሁለቱን ሐዋርያት ለአገልግሎት እንዳሰማራቸው፣ እያንዳንዱን ሐዋርያ በስም እንደጠራቸው እንመለከታለን። ከጠራቸው በኋላም ለተወሰኑ ቀናት ከእርሱ ጋር በመሆን ትምህርቱን እንዲቀስሙ፣ የእርሱን የፈውስ አገልግሎትንም በቅርብ ሆነው እንዲመለከቱ ጠርቶአቸዋል። በምዕ. 6 ቁጥር 7 እንደተገለጸውም፣ ኢየሱስም ይህን ያደረገበት ምክንያት፣ ሐዋርያቱ ከትንሳኤው በኋላ፣ ከመንፈስ ቅዱስ በሚቀበሉት ሃይል በመታገዝ እነዚያን በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ሆነው፣ ለምሳሌ በበሽታ፣ በጭቆና እና ብዝበዛ፣ በደል የሚደርስባቸው በርካታ የገሊላ እና የአካባቢው ሰዎች በሙሉ ፈውስን፣ ነጻነትን እና ማሕበራዊ ፍትህን የሚያገኙበት አገልግሎቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ በማሰብ ነበር።
ይህ የወንጌል ክፍል፣ ሁለት ተኩረት የተሰጡባቸው መልዕክቶች እንዳሉበት እንገነዘባለን። የመጀመሪያው የወንጌል ተልዕኮ መነሻ እንዳለው፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የወንጌል ተልዕኮ የራሱ ይዘት፣ መልክ እና ስርዓት እንዳለው እንገነዘባለን።
አንድ ሐዋርያዊ ልዑክ፣ ከሁሉ አስቀድሞ ተጠሪነቱ ለማን እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋል። የሐዋርያቱን የአገልግሎ መነሻ የተመለከትን እንደሆነ፣ እያንዳንዱ ሐዋርያ የአገልግሎት ጥሪውን ያገኘው ወይም የተቀበለው ከኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በእርግጥም ሐዋርያትን ለአገልግሎት ያሰማራቸው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ በበርካት አገላለጾች፣ ለምሳሌ ‘ወደ ራሱ ጠራው’፣ ‘ወደ ዓለም ዙሪያ ላካቸው’፣ ‘ስልጣንን እና ሃይልን ሰጣቸው’፣ ‘ይህን እንዲያደርጉ አዘዛቸው’ በማለት ይገልጸዋል። አስራ ሁለቱ ሐዋርያት እነዚህን የመሰሉ ትዕዛዛትን መቀበላቸው፣ የሚያዛቸውም ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ሆነ፣ አገልግሎትን ለማበርከት፣ የታዘዙትንም ለማድረግ ሃይልና ብርታት የሚሆናቸው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ፣ በተልዕኮአቸው ጊዜም ለእርሱ ፈቃድ ራሳቸውን እንዳስገዙ እንረዳለን። ይህ ደግሞ በተጨማሪ የሚያሳየን፣ እነዚያ አስራ ሁለቱ ሐዋርያት፣ ከራሳቸው አንደበት አውጥተው የሚናገሩት ምንም ዓይነት የግል መልእክት እና ችሎታ እንደሌላቸው፣ ነገር ግን የመልዕክቱ ባለ ቤትና፣ ይህን መልዕክት በትክክለኛው መንገድ የሚያስተላልፉበትን ጥበብ እና ድፍረት ያገኙት ከኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ እንገነዘባለን።
ይህ የወንጌል ክፍል እኛንም ይመለከተናል። እኛን በምልበት ጊዜ ካህናትን ብቻ ሳይሆን፣ በጥምቀት የኢየሱስ ክርስቶስ አካል የሆኑትን፣ በማንኛውም የኑሮ ደረጃ ላይ ሆነን የኢየሱስን መልካም ዜናን ለሌሎች ልንመሰክር የተጠራንን በሙሉ ነው። ዛሬ እኛም፣ ለምንሰጠው እውነተኛ የወንጌል ምስክርነት ቋሚ እና ዘለዓለማዊ መሠረታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። የወንጌል ምስክርነታችን፣ የአንድ ምዕመን፣ ወይም የመንፈስዊ ማሕበራት ወይም የከፍተኛ የቤተ ክርስቲያን ባለ ስልጣን የግል ተነሳሽነት ሳይሆን የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ፣ ይህም ከኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠ የተልዕኮ ጥሪ መሆኑን በሚገባ መገንዘብ ያስፈልጋል። እያንዳንዱ ምዕመን ለወንጌል አገልግሎት ወይም ምስክርነት ሲነሳ ከሁሉ አስቀድሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ከመሠረታት እና የአገልግሎት ጥሪን ከተቀበለች ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተላከ መሆን ያስፈልጋል። ለዚህ ጥሪ እንድንበቃ የሚያደርገንም በምስጢረ ጥምቀት የተቀበልነው ጸጋ ነው። የጥምቀትን ጸጋ የተቀበለ አንድ ክርስቲያን ለወንጌል ምስክርነት ወይም ለወንጌል አገልግሎት መጠራቱ ካልተሰማው፣ ይህ ክርስቲያን ትጉ ክርስቲያን አይደለም።