ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ “የኢየሱስ ደቀ-መዛሙርት ለመሆን የእምነት አመክንዮ መከተል ያስፈልጋል!”
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ እለት በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በእለቱ በሚነበቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ላይ ተንተርሰው አስተንትኖ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህም መሰረት በጥር 26/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ እርሳቸው በእለቱ በሚነበቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ተንተርሰው የሚያደርጉትን አስተንትኖ ለመከታተል ለተሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ቅዱስነታቸው ባደረጉት አስተንትኖ እንደ ገለጹት “የኢየሱስ ደቀ-መዛሙርት ለመሆን የእመንት አመክንዮ መከተል ያስፈልጋል” ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል። ክርስቲያኖች በሚኖሩበት ዓለም ውስጥ ‘ነቢይ’ መሆን ይኖርባቸዋል ያሉት ቅዱስነታቸው የኢየሱስን የእምነት አመክንዮ በመከተላቸው ብቻ የተነሳ በዓለም ውስጥ ተገልለው ለሚኖሩ ሰዎች ብርታት እና ተስፋ መስጠት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጥር 26/2011 ዓ.ም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደርጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!
ባለፈው እሁድ የነበረው የአምልኮ ሥነ-ስርዓት ኢየሱስ በናዝሬት ሙክራብ ውስጥ ተገኝቶ በነቢዩ ኢሳያስ መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈውን አንድ ክፍል በማንበብ እና በመጨረሻም እነዚህ ቃላት "ዛሬ" ተፈጸሙ በማለት ተናግሮ እንደ ነበረ ማዳመጣችን ይታወሳል። ኢየሱስ የጌታ መንፈስ በእርሱ ላይ እንዳረፈ፣ መንፈስ ቅዱስ እርሱን እንደ ቀደሰው እና የሰውን ዘር ለማዳን መንፈስ ቅዱስ እርሱን ወደ እዚህ ምድር እንደ ላከው አድርጎ ራሱን ሲያቀርብ እናያለን። የዛሬው ቅዱስ ወንጌል (ሉቃ. 4፡21-30) የዚያ ታሪክ ቀጣይ ክፍል ሲሆን የእነርሱ የአገራቸው ተወላጅ የሆነው "የዮሴፍ ልጅ" (ቁ .22) ራሱን የአብ መልእክተኛ የሆነው ክርስቶስ አድርጎ ሲያቀርብ የመለከቱታል።
ኢየሱስ አዕምሮንና ልብን ሰንጥቆ በመግባት ምን እንደ ሚያስቡ ማወቅ የሚያስችለውን ችሎታ ተጠቅሞ ወዲያው ወገኖቹ ምን እንደሚያስቡ መረዳት ችሎ ነበር። እርሱ ከእነርሱ አንዱ እንደሆነ አድርገው ስለቆጠሩት እርሱ በጎረቤት አገራት ውስጥ እንደ ፈጸመው ዓይነት ተዐምር በገዛ አገሩም ውስጥ ተዐምር እንዲፈጽም እንግዳ የሆነ “ጥያቄ” ማቅረባቸውን በግልጽ ተረድቶ ነበር። ይህ ጥያቄ ከእግዚአብሄር እቅድ/አመክንዮ ጋር የተጣጣመ ስላልነበረ ኢየሱስ ለዚህ ጥያቄ መልስ አልሰጠም ነበር፣ እግዚኣብሔር የሚፈልገው እመንት ነው፣ እነርሱ ደግሞ የፈለጉት ተዐምር ማየት ነበር፣ ምልክቶችን ማየት ፈልገው ነበር፣ እግዚኣብሔር ሁሉንም ሰው ማዳን ነው የሚፈልገው፣ እነርሱ ደግሞ የሚፈልጉት ለችግራቸው ጊዜያዊ የሆነ መፍትሄ የሚሰጥ መስህ ነበር የሚፈልጉት። በዚህም የተነሳ የእግዚአብሔርን አመክንዮ በሚገባ ለማብራራት በማሰብ እግዚኣብሔር ዕብራዊያን ያልሆኑ ወገኖችን፣ ነገር ግን በቃሉ የሚያምኑ ሰዎችን ሁሉ ለማዳን ወደ እዚህ ምድር የላካቸውን የሁለት ታላላቅ ቀደምት ነቢያት የነበሩትን የኤሊያስን እና የኤልሳዕ ምሳሌ ኢየሱስ ሲያቀርብ እንመለከታለን።
ልባቸውን እና አእምሮዎቻቸውን በነጻ ለሚሰጠው ደኅንነት እና ይህም በነጻ የሚሰጠው ደህንነት ሁለንተናዊ እንደ ሆነ፣ በዚህም ምክንያት ልባቸውን በመክፈት እንዲረዱት ላቀረበላቸው ግብዣ የናዝሬት ነዋሪዎች የሰጡት ምላሽ አመጽ የተቀላቀለበት እና እንዲያውም ይህ አመጽ ኃይለኛ ወደ ሆነ ሁከት ተለውጦ መቆጣጠር ስላልቻሉ “ተነስተው ኢየሱስን ለመጣል ይመቻቸው ዘንድ ከተማቸው ተሠርታበት ወደ ነበረው ወደ ተራራው አፋፍ ወሰዱት” (ሉቃስ 4፡29)ይለናል ቅዱስ ወንጌል። ቀደም ሲል እነርሱ ለእርሱ የነበራቸው አድናቆት ወደ ጠብ እና ወደ አመጽ ይቀየራል።
እናም ይህ የቅዱስ ወንጌል ክፍል የሚያሳየው የኢየሱስ የዚህ ምድር ይፋዊ አገልግሎት የተጀመረው በተቃውሞ እንደ ሆነ እና በተለይም ደግሞ ባልተለመደ ሁኔታ የእርሱ የሆኑ ወገኖች በእርሱ ላይ ባደረሱበት ከፍተኛ ተቃውሞ እና የመግደል ዛቻ እና ማስፈራሪያ በታከለበት መልኩ መጀመሩን ያሳያል። ኢየሱስ በአብ በሰጠው ተልዕኮ በመኖር እነዚህን ተቃውሞዎች፣ ስደትና የሽንፈት ስሜት መወጣት እንዳለበት በሚገባ ያውቃል። ልክ ትላንትና የነበረው እውነተኛ የነቢይነት ሚና እንደ ሚጠይቀው ሁሉ ዛሬም ቢሆን ዋጋ ለማስከፈል የቀረበ ጥያቄ ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ ከፍተኛ ተቃውሞ ኢየሱስን ተስፋ አላስቆረጠም ነበር ወይም የነቢይነቱን ሥራ በመጉዳት ፍሬያማ እንዳይሆን አላደረገውም ነበር። በአባቱ ፍቅር በመታመን መንገዱን ይቀጥላል።
ዛሬም ቢሆን ለሕዝቡ እና ለዓለም መልእክቱን ለማዳረስ የሚችሉ ዳፋር እና ቆራጥ የሆኑ ነብያት እና የጌታ ደቀ-መዛሙርት ውስጥ ይህንን ወኔ ማየት ይፈልጋል። በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት "በመገፋፋት" ተስፋን ለማወጅ እና ድሆችን ለማዳን እንዲያገለግሉ የላካቸው ሰዎች፣ እምነትን እንጂ የተዓምራት አመክንዮ አይፈልጉም፣ ለሁሉም ሰዎች አገልግሎት ለመስጠት የተላኩ፣ ማንንም ሳያገሉ እና ያለምንም ልዩነት የሚያገለግሉ ሰዎች መሆንም ይኖርባቸዋል። በአጭሩ የአብ ፈቃድ ለመቀበል የተዘጋጁ እና ይህንንም ፈቃድ ለሌሎች በታማኝነት ለመመሥከር የተጠሩ ሰዎች ናቸው ማለት ነው።